የመጅሊስ ምርጫን ተከትሎ የተፈጠሩ ልዩነቶች እና መሠረታቸው

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
የ2014ቱ የረመዳን ወር ከተጠናቀቀ ወዲህ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) የሥራ አስፈጻሚ አመራር ለውጥን ጨምሮ በርካታ ሃሳቦች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሲንሸራሸሩ ሰንብተዋል።
ለረጅም ጊዜያት ሳይደረግ የቆየው የመጅሊሱ ጠቅላላለ ጉባኤ ለአራት ቀናት ተካሂዶ ግንቦት 18/2014 ዓ.ም በሸራተን አዲስ በተጠራ ጉባኤ ውሳኔዎቹን ይፋ አድርጓል።
ጉባኤው ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የቀድሞ የዑለማዎች ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚን በማንሳት ወደ ፈትዋ ኮሚቴ በመመደብ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን መምረጥን ይጨምራል።
አዲሱ የሥራ አስፈጻሚ አካልም 15 አባላትን የያዘ ሆኖ ተዋቅሯል።
እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ሳይጸድቅ የቆየውን የመጅሊሱን መተዳደሪያ ደንብ ይሄው ጉባኤ ያጸደቀ ሲሆን፣ ይህ ደንብ በመጪው መስከረም በሚደረግ ምርጫ ይመሰረታል ተብሎ ለሚታሰበው ቋሚው መጅሊስ መተዳደሪያ ይሆናል።
ሌላውይህ ጉባኤ ያጸደቀው ውሳኔ መስከረም ወር ውስጥ ለሶስት አመታት የቆየውን የሽግግር ግዜ ምክር ቤቱን የሚተካ ቐሚ መጅሊስ የሚያቋቁም ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል የምርጫ ኮሚቴ ማቋቋም ነው።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ፕሬዘዳንት ሆነው ለሶሰት አመታት ሲመሩ የቆዩት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ እና ምክትላቸውን ዶ/ር ጄይላን ከድር እንዲሁም ጸሃፊ በመሆን ያገለገሉትን ግለሰብ ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገው ጉባኤ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው ይፋ ተደርጓል። ይህ አንዱ የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ነው።
በምትካቸውም ሼሕ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ፕሬዘዳንት፣ ሼሕ አብዱልከሪም ምክትል ፕሬዘዳንት እንዲሁም ሼሕ ኑረዲን ደሊል ጸሃፊ ሆነው መሾማቸውን በሸራተን አዲስ በተደረገው ጉባኤ ላይ ይፋ ተደረጓል።
ይህው ሳኔ ግን በቀድሞው የስራ አስፈጻሚዎች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ይልቁንም ፕሬዘዳንቱ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ ምርጫው በተደረገ ማግስት ለመገናኛ ብዙሃን “ስብሰባውን መጅሊሱ አያውቀውም፤ ውሳኔውም ሕገ-ወጥ ነው’’ ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል። “በእኛም ሆነ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት የለውም’’ ሲሉም ተናግረዋል።
ይህንንልዩነት ለመረዳት አሁን ካለንበት የግንቦት ወር ወደ ኋላ 11 አመታትን ተጉዘን መመልከትን ይጠይቃል።
መፍትሔ አፈላላጊው ኮሚቴ
ከ11 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሊባኖስ ተቀድቷል የሚባልለትን የአህባሽ አስተምሮ ወደ ኢትዮጵያ ‘በገንዘብ ኃይል በማምጣት በሕዝበ ሙስሊሙ ላይ ለመጫን ሞክሯል’ በሚል የዕምነቱ ተከታይ የሆኑ በተለይም ምሁራን ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ።
ይህ ጥያቄ በመንግሥት እና በምዕመኑ መካከል የፈጠረው ፍጥጫ ሌሎች ጥያቄዎች ተጨምረውበት ወደ ጋለ ተቃውሞ ተሸጋገረ።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ተብሎ የሚጠራው እና በኡስታዝ አቡበከር አህመድ የሚመራው የምሁራን ቡድን መታሰሩን ተከትሎ 'ድምጻችን ይሰማ' የተሰኘው ንቅናቄ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተመስርቶ ወደ ጠንካራ ተቃውሞ አደገ።
በወቅቱ ኮሚቴው ሦስት ዋና ዋና ጥያቄዎችን በይፋ አንስቷል።
ጥያቄዎቹም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት (መጅሊሱ) በሕዝበ ሙስሊሙ በተመረጡ አመራሮች ይመራ፣ አህባሽ የተሰኘው አዲስ የሃይማኖት ምልከታ በግድ አይጫንብን እንዲሁም የአወሊያ ተቋም በመጅሊስ ሳይሆን በቦርድ ይተዳደር የሚል ነበር።
የመፍትሔአፈላላጊ ኮሚቴው 17 አባላት የነበሩት ሲሆን በቀረበባቸው የሽብር ክስ በሐምሌ 2007 ከ 7 እስከ 22 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው እንደነበረም ይታወሳል።
ከአራት ዓመት እስር በኋላ በ2008 የአዲስ ዓመት ዋዜማ መንግሥት ምህረት ማድረጉን በመግለጽ ከእስር እንዲለቀቁ ተደረገ።
ታዲያ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን የፖለቲካ አመራር ለውጥ ተከትሎ ሚያዚያ 23/2011 በተካሄደው ጉባኤ የተመሰረተው የሽግግር ምክር ቤት ለዓመታት ሲነሱ የቆዩትን የሕዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች የሚመልስ ይሆናል ተብሎ ታምኖም ነበር።
ከሽግግር ምክር ቤቱ ባሻገር ዘጠኝ አባላት ያሉት የተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት የሚረዳ ኮሚቴ ተቋቋመ።
ከዚህ ኮሚቴ ውስጥ ከቀድሞው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሦስት፣ ተቃውሞ ሲነሳበት ከነበረው ከቀድሞው መጅሊስ ሦስት እንዲሁም ገለልተኛ የተባሉ ሦስት አባለት ተካተውበት ዘጠኝ አባላት ያሉት ሆኖ ተዋቀረ።
ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እና ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ከመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ተወከሉ።
ከቀድሞው መጅሊስ ሼሕ መሐመድ አሚን፣ ሼሕ ኸድር እንዲሁም ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ ኮሚቴው ውስጥ አባል ተደርገው ተመረጡ።
ገለልተኛ ሆነው ደግሞ ፕሮፌሰር መሐመድ ሃቢብ፣ ዶ/ር ኢድሪስ መሐመድ እና ሼሕ መሐመድ ጀማል አጎናፍር ተመረጡ።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ ብሎም የወቅቱ የሰላም ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በሸራተኑ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ነበር።
በዚሁ ሸንጎ ላይ 500 የሚጠጉ ዑለሞች ከመላው ኢትዮጵያ ተወክለው የተገኙበት ሲሆን፣ አዲስ የተመረጠው ጊዜያዊ ጠቅላላ ጉባኤም እነዚህን ለዓመታት ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎችን ይመልሳል ተብሎ ተስፋ ተጣለበት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የመጅሊሱ የሽግግር መዋቅር
ከሸራተኑ ጉባኤ በመቀጠል በተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ ዱባይ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ። ይህ የዱባዩ ውሳኔን ቁልፍ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የሽግግር ምክር ቤቱን የሚያስተዳደር ደንብ የጸደቀበት መሆኑ ነው።
ይህ ደንብ የመጅሊሱን የሽግግር ጊዜ መዋቅር በግልጽ ያስቀምጣል። ይህም የሸግግር ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ የበላይ አካል ሲሆን የዑለማዎች ምክር ቤት ሁለተኛው ረድፍ ላይ ይቀመጣል። በሦስተኛ ደረጃ የሽግግር ጊዜ ሥራ አስፈጻሚ የተቀመጠ ሲሆን ቀጥሎም የሽግግር ጊዜ ቦርድ ይከተላል።
ከፍተኛው የሥልጣን ባለቤት የሆነው ጠቅላላ ጉባኤው 32 አባላት አሉት። አባላቱም የዑለማዎች ምክር ቤቱ ብሎም የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ናቸው። ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤው የሆነው የዑለማዎች ምክር ቤት 26 አባላት ያሉት ሲሆን ቦርዱ ደግሞ ሰባት አባላት አሉት።
የሽግግሩ ጊዜ የዑለማዎች ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚዎች ፕሬዘዳንት፣ ምክትል ፕሬዘዳንት እና ፀሐፊ ሆነው ይመረጣሉ።
ታዲያ ባለፈው ሳምንት ለተፈጠረው ውዝግብ መሰረት የሆነው ነጥብ ይህ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንቱን ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስን ጨምሮ ሌሎች አባላትን የመሻር መብት አለው ወይስ የለውም? የሚለው ነው።
በዚሁ በዱባይ በጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤው የሥራ አስፈጻሚ አባላትን የመሾም ብሎም የመሻር መብት እንዳለው ብሎም በዓመት ሁለት ጊዜ የመሰብሰብ ኃላፊነት አንዳለበት ተደንግጓል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ልዩነቱ ምን ላይ ነው?
ይህ ጠቅላላ ጉባኤ ከመጠራቱ በፊት ከዑለማዎች ምክር ቤት አባላት ውስጥ 19ኙን ብሎም 7ቱንም የቦርድ አባላት የመጅሊሱ ፕሬዘዳንት አባረው እንደነበረ፣ የታሪክ ምሁሩ እና ጉዳዩን ሲከታተል ቆየው ኢብራሂም ሙሉሸዋ ይናገራል።
የነባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው የቆዩት ሼሕ አሕመድ አወል ሰኢድ "ማንንም ሰብስበው ጠቅላላ ጉባኤ በሚል ቃለ ጉባኤ ይዞ አንዱን መሻር መሾም ተገቢ አይደለም’’ ሲሉ ይናገራሉ።
ከመላው አገሪቱ ዑለማዎች ተሰብስበው መሳተፍ ነበረባቸው የሚሉት ሼሕ አህመድ እርሳቸው የኡለማዎች ምክር ቤት አባል ሆነው ሳሉ ሳይሳተፉ መቅረታቸውንም ይናገራሉ።
በመጅሊሱ ውስጥ ሁለት ወገን እንዳለ እየታወቀ አንዱን ወገን ነጥሎ መሾም አግባብ አይደለም የሚሉት ሼሕ አህመድ፣ ሁለቱ ወገን ሱፊ እና ሰለፊ በሚል መሰረት መሆኑን ይናገራሉ።
የታሪክ አዋቂው ኢብራሂም ሙሉሸዋ እንደሚለው በሸራተን በተደረገው የመጀመሪያው ጉባኤ 26 ዑለማዎች ሲዋቀሩ 13 ከሱፊ 13 ከሰለፊ መወከሉን ይናገራል።
ነገር ግን አሁን የተመረጠው መጅሊስ እንዲሁም ላለፉት ሦስት ዓመታት ነበረው ልዩነት መሰረቱ ይህ አይደለም ይላል። ለአብይነትም ይሁን በምክትልነት እንዲሁም በፀሐፊነት የተመረጡት ሰዎች የታወቁ የሱፊ አይከኖች (ምልክቶች) መሆናቸውን ያክላል።
ሼሕ አሕመድ አወል "ሸራተን ሲመረጥም ትክክል የተሰራበት አይደለም። ሸፍጥ የተሰራበት ነው። ሁለቱንም ያጣጣመ እና እኩል ያደረገ አይደለም" ሲሉ ተችተዋል።
"ማንኛውም ተቋም የሚወስነው ውሳኔ ሁሉንም ሰው ያስማማል ማለት አይደልም። ነገር ግን አብዛኛው አባል የመረጠው ይሆናል። በዚህ ጊዜ መንግሥት ሥርዓት ያስከብራል" ሲሉ ኢብራሂም አዲስ የተመረጠው ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ይረከባል የሚል ተስፋቸውን ይገልጻሉ።
አክለውም ልዩነቱ በሱፊ እና በሰለፊ መካከል የተፈጠረ መሆኑን ይናገራሉ። እርሳቸው የሱፊ ሙስሊም መሆናቸውን በማከል አሁን በተካሄደው ምርጫ ቢመረጡም "አንዱን ወገን ወክዬ እና ተገንጥዬ ብሄድ ማነው የሚቀበለኝ" ሲሉም ይጠይቃሉ።
በዚህ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ሼሕ አብዱላዚዝ ሼሕ አብዱል ወሊ በበኩላቸው በሸራተኑ ጉባኤ ከ26 ዑለማዎች መካከል አባል ሆነው ተመርጠው ነበር። አሁንም በዑለማዎች ምክር ቤት ብሎም አዲስ በተመሰረተው ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ምክትል ፀሐፊ ሆነው ተመርጠዋል።
ሼሕአብዱላዚዝ ጠቅላላ ጉባኤው ምልዓተ ጉባኤ የተሟላበት ብሎም ሕጋዊ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ይህም ከ32ቱ አባላት ውስጥ 22 ሰው በመገኘታቸው ጠቅላላ ጉባኤው የተሟላ መሆኑን ያስረዳል ይላሉ።
"መጅሊሱ የሱፊ አመለካከት ባላቸው ሰዎች ብቻ መያዝ አለበት፣ ሌላውን አይመለከትም የሚሉት ጥቂት ሰዎች ናቸው" ሲሉም ይናገራሉ። "ሰፊው ሕዝበሙስሊም እና ሊቃውንቱ አሁን የምንጠቅሳቸው ስሞች ጉዳዩ እና ክርክሩ አይደሉም። በማንኛውም ተቋማት ያለ ዓይነት የአመለካካት ልዩነት ቢኖርም ግን በመሠረታዊ እና በሚያስማማ ነገር ላይ ነው የሚገናኛው" ሲሉም ይናገራሉ።
በተደጋጋሚ እየተነሳ ያለው የሱፊ እና ሰለፊ ልዩነት ምንድነው? ስንል ለኢብራሂም ጥያቄ አቅርበንለታል። ልዩነት የተወሰኑ የአምልኮ ልዩነቶች እንጂ መሠራታዊ አለመሆኑን ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተጨማሪም ከሰላት በኋላ የሚደረጉ እና ድምጽ ከፍ ተደርጎ የሚደረግ የጋራ ሶላት አንዱ የልዩነት መሰረት እንደሆነ የሚናገሩት ኢብራሂም ልዩነቶቹ መሠረታዊ እንዳልሆኑ አጽንኦት ይሰጣሉ።
ኢብራሂምም በበኩላቸው ልዩነቱ የአስተዳደር እንጂ እንዲህ ያሉ ልዩነቶች እንዳልሆነ በመጥቀስ ይህንን ውድቅ ያደርጋሉ።
የተጠራው ጉባኤ ሕጋዊ ነው የሚሉት ኢብራሂም በዱባይ በተፈረመው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ፕሬዘዳንቱ ጠቅላላ ጉባኤውን መጥራት ካልቻሉ ምክትሉ እንደሚጠራ ባስቀመጠው መሰረት የተጠራ ብሎም ከ 50 በመቶ በላይ አባላት የተሳተፉበት በመሆኑ ሕጋዊነቱ የጸና ነው ይላሉ።
ስለብዝሃነት የሚነሳው ጥያቄም ከአንድ ብሔር በዝቷል የሚለው ጥያቄም ከ15 ሥራ አስፈጻሚ በዝቷል የሚባለው ብሔር አራት ሰው ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ።
"እንዲህ አይነት ነጥቦች የሚነሱት ብቃትን በመሰል የማንነት ነጥቦች ለመሸፈን ነው" ሲሉም “ከሥርዓት ውጪ የመሆን አካሄድ ነው’’ ሲሉ ይወቅሳሉ።
በኃላፊነትላይ የቆየው መጅሊስ ከኃላፊነቱ ለመልቀቅ በማይፈልግበት ብሎም አዲስ የተመረጠው ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነቱን ለመረከብ በሚጠብቅበት ሁኔታ ቀጣይ የመጅሊሱ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል ስንል ኢብራሂምን ጠይቀናቸዋል።
መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ መግባት ባይችልም ነገር ግን እንዲህ አይነት ልዩነቶች ሲመጡ ሥርዓት የማስከበር ኃላፊነት አለበት ይላሉ።
"ማንኛውም ተቋም የሚያሳልፈው ውሳኔ ሁሉንም ሰው ያስማማል ማለት አይቻልም። ነገር ግን አብዛኛው አባል የሰጠው ውሳኔ ይጸናል። በዚህ ጊዜ መንግሥት ሥርዓት ያስከብራል" ሲሉ ኢብራሂም አዲስ የተመረጠው ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ይረከባል የሚል ተስፋቸውን ይገልጻሉ።












