የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን አስታራቂ ለመሆን ጥያቄ አቀረበች

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

የፎቶው ባለመብት, EOTC

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በሰሜኑ የእርስ በእስር ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ለማስቻል የአስታራቂነት ሚናን ለመወጣት ጥያቄ ማቅረቧን አስታወቀች።

ቅዱስ ሲኖዶሱ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሲያካሂድ የቆየውን ምልዓተ ጉባኤ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ “ለቤተ ክርስቲያኒቱ እና ለአገሪቱ የሚበጁ” ያላቸውን ውሳኔዎችን ማሳለፉን አሳውቋል።

የቅዱስ ሲኖዶሱን መግለጫ በንባብ ያቀረቡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ የኢትዮጵያ የእርስ በእስር ጦርነት በንግግር ለመፍታት ቤተ-ክርስቲያኗ የአስታራቂነት ሚናን ለመወጣት ለፌደራሉ መንግሥት ጥያቄ ማቅረቧን ተናግረዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ “ጦርነት እና የእርስ በእስር ግጭት ተወግዶ አጠቃላይ ሰላም በሚሰፍንበት መልኩ ተነጋግሮ ችግርን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት እንዲቻል ቤተ-ክርስቲያናችን የአስታራቂነት ሚናዋን መጫወት እንድትችል ለማድረግ ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ እንዲቀርብ ተደርጓል” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤው ማጠቃለያ ላይ በትግራይ ክልል ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት ለአገር አንድነትና ሰላም በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቧል።

ከጥቂት ወራት በፊት በትግራይ ክልል የሚገኙ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካህናት በጦርነቱ ወቅት ማዕከላዊው ሲኖዶስ ከጎናችን አልቆመም በሚል፣ ተለይተው የእራሳቸውን ቤተክህነት ማቋቋማቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም በአገሪቱ በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያት በደረሰው የሰው ሕይወት ሕልፈትና የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የቤተ ክርስቲያኗ ካህናትና የምዕመናን ላይ በደረሰ ህልፈት ላይ አትኩሮ መወያየቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ተወስኗል።

የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ በቅርቡ ዋነኛ መነጋገሪያ የነበረውን የበዓል ማክበሪያ ቦታዎች ጉዳይንም አንስቶ በመነጋገር “አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ በቀጣይም በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግ” ጠይቋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ትልቁ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባውን በዓመት ሁለት ጊዜ ያካሂዳል።