ሩሲያ በዩክሬን በተቆጣጠረቻቸው ከተሞች ፓስፖርት መስጠት ጀመረች

የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ከተሞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ በደቡባዊ ዩክሬን በተቆጣጠረቻቸው ሁለት ከተሞች ኬርሶን እና ሜሊቶፖል ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች የሩሲያ ፓስፖርት መስጠት መጀመሯንን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ዩክሬን በግዛቷ ላይ እየተከናወነ ያለው ተግባር የሩሲያውን ዜጎች መፈጠር ወይም “ሩሲፊኬሽን” ነው ስትል አውግዛለች።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሰራሩን በፍጥነት እየተከታተሉት እንደሆነም ተገልጿል።

የሩሲያው ታስ የዜና ወኪል እንደገለጸው ቅዳሜ እለት በተካሄደው ሥነ ሥርዓት የመጀመሪያዎቹ 23 የኬርሶን ከተማ ነዋሪዎች የሩሲያ ፓስፖርት አግኝተዋል።

የዜና ወኪሉ አክሎ እንደዘገበው በሺዎች የሚቆጠሩ የኬርሶን ከተማ ነዋሪዎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ነገር ግን ይህንን ከገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልተቻለም።

በኬርሶን የተሾሙት የሩሲያ ወታደራዊ አስተዳዳሪ ቮሎዲሚር ሳልዶ "ሁሉም የኬርሶናዊ ጓዶቻችን በተቻለ ፍጥነት ፓስፖርት እንዲሁም የሩሲያ ዜግነት መቀበል ይፈልጋሉ" ብለዋል።

ዩክሬን ይህ እርምጃ የግዛት ሉዓላዊነቴን የጣሰ ነው እንዲሁም ይህ የፕሬዚዳንት ፑቲን አዋጅ "ህጋዊነት የሌለው” ስትል አውግዛዋለች።

ሩሲያ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በኃይል የተቆጣጠረቻቸው ክሬሚያ እና አብዛኛው ዶንባስ የዩክሬን ግዛቶች ነዋሪዎች ፓስፖርት የሰጠች ሲሆን አሁንም የምታደርገው ያንን ፖሊሲ የተከተለ ነው ተብሏል።

ሩሲያ ክሬሚያን ወደ ራሷ ከቀላቀለች በኋላ በዶኔትስክ እና በሉሃንስክ በራሳቸው የሚተዳደሩ "የሕዝብ ሪፐብሊኮችን" ፈጠረች። ይህም ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘ እርምጃ ነው።

ዩክሬን አሁን በተፈጸመው ወረራ በሩሲያ ኃይሎች በተያዙ አካባቢዎች ተመሳሳይ ሂደት እየተካሄደ ነው የሚል ስጋት አለባት።

አንዴ ነዋሪዎቹ ሩሲያውያን ከሆኑ፣ ክሬምሊን እነርሱን "መከላከል" ይገባል የሚል መከራከሪያ ሃሳብ ልታቀርብ ትችላለች ይላሉ።

በኬርሶን ውስጥ የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ የሆነውን ሩብልን ከመጠቀም የዩክሬን ሂርቪንያን መጠቀም እንደሚመርጡና በዚህም ከሩሲያውን ባለስልጣናት ትእዛዝ እንደወጡ ሪፖርቶች ታይተዋል።

ሜሊቶፖል በደቡብ-ምስራቅ ዛፖሪዝዝሂያ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የአውሮፓ ትልቁ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ጨምሮ አብዛኛው ስፍራ በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ነው።

በክሬሚያ እና በሩሲያ ቁጥጥር ባለችው ዶንባስ (በዶኔትስክ እና በሉሃንስክ የተገነባው የኢንዱስትሪ ክልል) መገበያያቸውን ወደ ሩሲያ ሩብል የቀየሩ ሲሆን በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች የሩስያ ሥርዓተ ትምህርት እንዲከተሉ ግዴታ ሆኖባቸዋል።

እንዲሁም በዩክሬን የተሾሙ የአካባቢ ባለስልጣናትን ከስልጣን በማንሳት አዲስ በተያዙ አካባቢዎችም ከዚህ ቀደም የተወሰዱ እርምጃዎች ተደግመዋል።