“የልጃችንን ገዳይ ሳናውቅ አናርፍም”

ወቅቱ እንደ አውሮፓውያኑ 1984 ነው።
የ15 ዓመቱ ማርክ ቢሊንግተር በእንግሊዟ በርሚንግሃም ቤቱ አቅራቢያ በአየር ላይ የሚበረውን ‘ካይት’ ይዞ ብስክሌቱን እያሽከረከረ ወጣ።
ያችም ዕለት በሕይወት የታየበት የመጨረሻ ቀን ነበረች። ከሳምንታት በኋላ አስክሬኑ ከዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ተገኘ።
በመጀመሪያ ራሱን አጥፍቷል ተብሎ ቢታይም ከዓመታት በኋላ ግን የግድያ ምርመራ ተከፈተ።
ሆኖም አሥርት ዓመታት የፈጀ ምርመራ ቢደረግም እስካሁን በታዳጊው ግድያ የተከሰሰ ሰው የለም።
የልጃችንን ገዳይ ሳናውቅ አናርፍም ያለው ቤተሰቡ ከ38 ዓመት በኋላ ገዳዩን ለማግኘት የራሳቸውን ምርመራ ጀምረዋል።
የማደጎ ቤተሰቦቹ ሮይ እና ዊንፍሬድ ቢሊንግተን ማርክን ወደ ቤታቸው ያመጡት ገና በጨቅላነቱ ነው። ጊዜው ረዥም ቢሆንም ትናንት የሆነ ይመስል ያስታውሱታል።
"እዚያ ተቀመጠ እና ክፍሉን ዘወር ዘወር ብሎ ተመለከተ። እጆቼን ለማቀፍ ዘረጋሁለት እሱም በምላሹ አቀፈኝ፤ የኔም መሆኑን አወቅኩ” ትላለች እናቱ።
“እኔ የማደጎ ልጅ ነኝ። እሱንም በማደጎ እንዳሳደግነው ያውቃል። ሁልጊዜም የተለየን ነን እላለሁ ምክንያቱም የተመረጥን ስለሆንን።
“እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ነገር በሕጻን ላይ ሲከሰት፤ በሱ ላይ ሊደርስ ይችላል ብለን በሕልማችንም ቢሆን የምናስበው አልነበረም” ትላለች።

ማርክ ለስላሳ ልጅ ነበር። ስሜቱ በቀላሉ የሚነካ፣ ዝምተኛ እንዲሁ ደስተኛ ነበር። እንስሳትን እና ምግብ ማብሰል ይወድ ነበር።
የትኛውም ጸብ ላይ ድርሽ አይልም። ጁዶ መማር ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ለኔ አይደለም ብሎ ተወው።
የአካል እድገት መዘግየት፣ የአእምሮ ውስንነት እንዲሁም በአንደኛው የሰውነት አካሉ በኩል ድክመት ነበረበት።
ሆኖም ጋዜጣ ያዘዋውር ነበር። እንዲሁም ጎረቤቶች እንዴት አሳና ቺፕስ ወይም የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ይገዛላቸው እንደነበር ለወላጆቹ ይነግሯቸው ነበር።
ለመጨረሻ ጊዜ ማርክን ያዩት በርሚንግሃም ቤታቸው ውስጥ ሲሆን አባቱ ጫማ ለመመለስ ከቤት ሲወጡ እናቱ ደግሞ ሁለቱን ልጆች ይዘው ከተማ ወጡ።
ወላጆቹ ከቤት ሲወጡ ማርክ የጥዋቱን ጋዜጣ ለጎረቤቶች የማዘዋወሩን ተግባር አጠናቆ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር።
አብሯቸውም አልሄደም። ወደ ማታ 11፡ 00 ሰዓት አካባቢ ሁለተኛውን ዙር ጋዜጣ ማዘዋወር ቢኖርበትም አልታየም። የዜና ወኪሉም ደውሎ እንዳልመጣ ነገራቸው።
ብስክሌቱን ከአትክልት ስፍራቸው ሲያጡ ቤተሰቦቹ ለፖሊስ ደወሉ። ከዚያም ፍለጋው ተጀመረ። ለዘጠኝ ሳምንታትም ያህል በይኖራል ተስፋ ቤተሰቡ ጠበቀ።
ከዚያም ያልጠበቁት ሆኖ ፖሊስ ደወለላቸው።
አባቱ ከመኖሪያ ቤታቸው 11 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ኮቨንተሪ አቅራቢያ በሚገኘው ሜሪደን ጠርዝ ላይ ባለው ዛፍ ላይ የልጃቸው አስከሬን ተሰቅሎ እንደተገኘ ሲነገራቸው ተብረክርከው እንደወደቁ ያስታውሳሉ።

አስከሬኑን ለመለየት ፖሊስ ጣቢያ እንደደረሱም ፖሊስ ልጃቸው ማርክ ራሱን እንዳጠፋ ነገራቸው።
ነገር ግን ራሱን እንደገደለ በፍጹም አላመኑም።
በተለይም አስከሬኑ እንዴት እንደተገኘ በዝርዝር ሲሰሙ ራሱን እንዳላጠፋ የበለጠ እርግጠኛ ሆኑ።
በተለይም ካለበት አካላዊ ውስንነትና ድክመት አንጻር የሞተበትን ገመድ ቋጠሮ ማሰር ይችላል የሚለውን አላመኑም። አስከሬኑም ወደተገኘበት ጫካ ነድቶ ሊሄድም አይችልም አሉ።
የፖሊስ ምርመራ ትክክልም አይደለም ብለው ተከራከሩ።
“ዛፍ ላይ አስከሬኑ ተንጠልጥሎ ሲያገኙት ፖሊሶች ራሱን እንዳጠፋ ወሰኑ። ነገር ግን ይህ ትክክልም፣ ፍትሐዊም አልነበረም” ትላለች እናቱ።
“እርዳታ ከተፈለገ ወደ ፖሊስ ነው የምንሄደው፤ እንዴት እንዲህ አይነት ነገር ይፈፀማል?" ስትልም ትጠይቃለች።
በጥልቅ ሐዘናቸው ላይ የፖሊስ ምርመራ እንዲሁም የሚዲያው ትኩረት በነሱ ላይ በማነጣጠሩ ሁለቱን ልጆቻቸውን ጓደኞቻቸው ጋር እንዲቆዩ ለማድረግ እንደተገደዱ ትናገራለች።
በአሁኑ ወቅት የሦስት ልጆች እናት የሆነችው እህቱ ሼሪል በዚያን ወቅት ማርክ ይመጣል በሚል ጉጉት ትጠብቅ እንደነበር ታስታውሳለች።
ሙሉ ሕይወታቸውንም ሐዘኑ አልተለያቸውም። ይባስ ብሎ ማርክ ከሞተ ከስምንት ዓመታት በኋላ የበኩር ልጃቸው ራስል በሞተር ሳይክል አደጋ ሲሞት ሌላ አሳዛኝ ሁኔታ አጋጠማቸው።
ማርክ ከሞተ ከአስራ ስምንት ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2002 ፖሊስ አዲስ መረጃ በማግኘቱ ግድያ ነው በሚል አዲስ ምርመራ ከፈተ።
ፖሊስ ምርመራውን በመጀመሪያ የያዘበት መንገድ የተሳሳተ ነው የሚሉት አባቱ፣ የግድያው ምርመራ ሲከፈትም ማርክን መልሶ በሕይወት ባያመጣውም ቢያንስ እፎይታ ተፈጠረላቸው።
በተለይም ብሪያን ፊልድ የተባለ ግለሰብ በአንድ ታዳጊ ግድያ በአውሮፓውያኑ 2001 መታሰሩን ተከትሎ ነው ፖሊስ እንደ አዲስ ምርመራውን የጀመረው።
አርሶ አደር የሆነው ግለሰብ ሮይ ቱቲል የተባለ የ14 ዓመት ታዳጊን በአውሮፓውያኑ 1968 መግደሉን ማመኑን ተከትሎ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።
የግለሰቡ የጥፋተኝነት ውሳኔ ፖሊስ ያልተፈቱ ግድያዎችን ከዚህ ግለሰብ ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል በሚልም ጥያቄ አጫረባቸው።

ሆኖም የማርክ ግድያ ምርመራ በተከፈተበት ወቅትም በሌላኛው ታዳጊ የተከሰሰው ፊልድ ስለ ማርክ አልተመረመረም።
ፖሊሶች ምርመራቸውን ያተኮሩት ማርክ ቤት ጀርባ በሚገኝ መናፈሻ ላይ የነበሩ ታዳጊዎች ላይ ነው። ማርክ መናፈሻው ላይ’ ካይቱን’ እያበረረ የነበረ ሲሆን በኋላም አንድ ሕንፃ ውስጥ ሲገባ ታዳጊዎች ከሕንፃው ውጭ ታይተዋል ተብሏል።
የግድያው ምርመራ ከተጀመረ ከ20 ዓመታት በኋላ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው የነበረ ቢሆንም በማርክ ግድያ ላይ ተጠያቂ የሆነ ሰው የለም።
ክስም ያልተመሠረተ ሲሆን ቤተሰቡም ምላሽ አላገኘም።
በአሁኑ ወቅት ገዳዩን ለማግኘት የራሳቸውን ዘመቻ የከፈቱ ሲሆን ኅብረተሰቡም እንዲረዳቸው በፌስቡክ ገጻቸው እየጠየቁ እንዲሁም እየተማጸኑ ነው።
እህቱ ሼሪል ጉዳዩን ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚሸፍኑ እና በቅርብ ዓመታት ውስጥ ደግሞ ሰዎች ያመጧቸው መረጃዎችን የያዙ ሰነዶች ማህደር አላት።
የፌስቡክ ገጹን የከፈቱት በጎ ፍቃደኛ መርማሪዎች ሲሆኑ መረጃዎችንም እየሰበሰቡ ይገኛሉ። በዚያን ወቅት ከነበሩ ሰዎችም ስለ ማርክ የሚያስታውሱትን ነገርም ይመዘግባሉ።
ባለፈው ዓመት የቻናል 4 ዘጋቢ ፊልም ምርመራው እንዲከፈት ምክንያት የሆነው የታዳጊው ገዳይ ፊልድ ከማርክ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል በተጨማሪም አስከሬናቸው ያልተገኘው የ11 እና 13 ዓመት የሆኑት ዴቪድ ስፔንሰር እና ፓትሪክ ዋረንም ጋር ያለውን ግንኙነት አጉልቶ አሳይቷል።
ቤተሰቡ አሁንም ፊልድ ዋነኛ ተጠርጣሪ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ከቤታቸው 10 ደቂቃ የእግር መንገድ ርቀት የሚኖረውና ማርክ ከተገደለበት አንድ ወር በፊት ከእስር የተለቀቀው ፊልድ ገድሎታል ብለው ያስባሉ።
ሆኖም እነሱ እንደሚያምኑት ፊልድ በቤታቸው አቅራቢያ ሳይሆን የሚኖረው ፖሊስ ማርክ በጠፋበት ወቅት ፊልድ የ90 ደቂቃ የመኪና መንገድ ርቀት ባላት ኦስዌስትሩ በምትባል ከተማ ነበር የሚኖረው ይላል።
ነገር ግን የግለሰቡን መኖሪያ በተመለከተ የሚጋጩ መረጃዎች በመውጣታቸው ጥያቄዎች አሁንም መመለስ አልቻሉም።
"ሙሉ በሙሉ ተሳስቼ ሊሆን ይችላል ነገር ግን እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ፊልድ ዋነኛው ተጠርጣሪ ነበር" ይላሉ አባትዬው።
ሆኖም የዌስት ሚድላንድስ ፖሊስ ከማርክ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ፊልድ ተመርምሮ እንደሆነ ሲጠየቅ “ባለፈው ምርመራዎቻችን የረዱን ወይም ያልረዱትን ወይም ሊረዱ የሚችሉ ሰዎችን ስም መጥራት ስህተት ነው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ሼሪል እንደምትናገረው ቤተሰቡ በቅርቡ ስለ ማርክ ጉዳይ በርካታ ጥያቄዎችን ለፖሊስ አቅርበዋል። ሆኖም ለአንዳንዶቹ ምላሽ መስጠት እንዳልቻሉ፣ እንዲሁም ማስረጃው ለምን ያህል ጊዜ መቀመጥ ነበረበት የሚሉ ፖሊሲዎችንም ጭምር ሊመልሱላቸው አልቻሉም።
ማርክ ራሱን አጥፍቷል የሚል የምርመራ ውሳኔ ላይ ፖሊስ መድረሱን ተከትሎ አሁን እንደ ማስረጃ ሊወሰዱ የሚችሉ ነገሮችን ማስቀመጥ አስፈላጊነቱ አልታየም ብሏል።
የማርክ ጉዳይ ለመጨረሻ ጊዜ የተገመገመው በአውሮፓውያኑ 2021 ነው ብሏል።
በዌስት ሚድላንድስ ፖሊስ የሆኑት ዴት ሱፕት ሻውን ኤድዋርድስ እንደሚሉት “ማርክ ከሞተ ከ38 ዓመታት በኋላም ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ እርማቸውን ማውጣት አልቻሉም”።
“ትኩረታችን ለማርክ ፍትሕ ማስገኘት ነው። ሐዘናችንና ሐሳበችን ማርክን ከማይረሱት ቤተሰቦቹና ከጓደኞቹ ጋር ነው። እንደ ሁሉም ያልተፈቱ ወንጀሎች፣ ማንኛውንም አዲስ መረጃ ለመከታተል ዝግጁ ነን" ብለዋል።
የማርክ እናት ቤተሰቡ አሁንም ገዳዩት የማግኘት ከፍተኛ "ተስፋ" እንዳደረባቸው ትናገራለች።
"ማርክ የሚገባውን ፍትሕ ልሰጠው እወዳለሁ፤ ይህም የሚሆነው ገዳዩ ሲገኝ ነው” ብላለች።












