በ1 ቢሊየን ፓወንድ የታክስ ማጭበርበር በጥብቅ ስትፈለግ የነበረችው ግለሰብ ተያዘች

ሳራ ፓንቲዝክ

የፎቶው ባለመብት, HMRC

በማጭበርበር ወንጀል ለዓመታት በጥብቅ ስትፈለግ የነበረችው ግለሰብ ተይዛ የስምንት ዓመት እስር ተፈረደባት።

በዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛ የወንጀል ተፈላጊዎች ዝርዝር ውስጥ የነበረችው የ48 ዓመቷ ሳራ ፓንቲዝክ፣ ጉዳዩዋ በፍርድ ቤት እየታየ ሳለ እአአ በ2013 ጠፍታ ነበር።

ለፍርድ የቀረበችው አንድ ቢሊዮን ፓውንድ በስልክ በታገዘ የገንዘብ ማጭበርበር ድርጊት በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ ነው።

ከፍርድ ካመለጠች በኋላ ለስምነት ዓመታት ስትፈለግ ቆይታ ሳንታ ባርብራ፣ ስፔን ውስጥ ውሻዋን እያንሸራሸረች ሳለች ተይዛ ታስራለች።

ለዩናይትድ ኪንግደም ተላልፋ ከተሰጠች በኋላ ለንደን በሚገኘው ኪንግስተን ፍርድ ቤት ቀርባለች።

በ2010 ተጨማሪ እሴት ታክስ ከማጭበርበር ጋር በተያያዘ በሚሊዮን የሚቆጠር ፓውንድ አጭበርብራለች ተብላ ተከሳ፣ በ2013 በሌለችበት የስምንት ዓመት እስር ተፈርዶባት ነበር።

ይህ ውሳኔ ከተያዘችን ጊዜ አንስቶ እንደሚጸና ዳኛ ሳራ ፓልሽክስ ተናግረዋል።

ሳራ ፓንቲዝክ

የፎቶው ባለመብት, NATIONAL CRIME AGENCY

ግለሰቧ ከናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውጭ በተከፈቱ የባንክ ቁጥሮች አማካይነት የተካሄደ የገንዘብ ማጭበርበር ውስጥ እጇ እንዳለበት ተገልጿል።

ይግባኝ መጠየቅ የምትችለው ለአራት ዓመታት በእስር ላይ ከቆየች በኋላ ነው።

በ2016 ሳራ እጅ ላይ የሚገኝ 2.4 ሚሊዮን ፓውንድ እንድትመልስ ውሳኔ ተላልፏል።

ይህንን ገንዘብ በሦስት ወራት ውስጥ የማታመጣ ከሆነ ተጨማሪ ዘጠኝ ዓመታት በእስር እንደምትቆይም ተወስኗል።

ይህንን ገንዘብ ሳትመልስ በመቅረቷ በ2020 ገንዘቡ ከነወለዱ 3.4 ሚሊዮን ፓውንድ ደርሷል።

ገንዘቡ በየቀኑ 538 ፓውንድ እየወለደ እስካሁን ድረስ ሳይከፈል ቆይቷል።

የዩኬ ብሔራዊ ወንጀል መከላከል ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ቶም ዳውዳል፣ ለዓመታት ስትፈለግ የቆየችውን ግለሰብ በስተመጨረሻ በቁጥጥር ስር ማዋል “የዓመታት ጥረት ውጤት ነው” ብለዋል።

የማጭበርበር ወንጀል የሚመረምሩት ሳይመን ዮርክ፣ “ሳራ የማንይዛት መስሏት ነበር። ማንኛውም ግብር አጭበርባሪ ከእኛ አያመልጥም” ብለዋል።

ከእሷ በተጨማሪ ሌሎች ተባባሪዋቿ የነበሩ 17 ግለሰቦችም እስር ተፈርዶባቸዋል። የእስር ዘመናቸው በአጠቃላይ ሲደመር 135 ዓመታት ይደርሳል።