አምስት ጊዜ ለኬንያ ፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው ያልተሳካላቸው ራይላ ኦዲንጋ አረፉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ዝነኛው ኬንያዊ ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የቤተሰባቸው ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።
የኦዲንጋ መሞት የተገለጸው ሕክምና ለመከታተል ሕንድ ውስጥ ሳለ ነው።
የሕንድ ፖሊስ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገረው ኦዲንጋ ከቤተሰባቸው አባላት እና ከግል ዶክተራቸው ጋር እያሉ "በድንገት መውደቃቸውን" ተከትሎ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።
ባለፉት ሳምንታት የኦዲንጋን ጤንነት በተመለከተ ያልተረጋገጡ ወሬዎች ሲናፈሱ የነበረ ሲሆን፣ የቤተሰብ አባሎቻቸው እና የፖለቲካ አጋሮቻቸው በጽኑ ስለመታመማቸው የሚነገረውን ዜና ውድቅ አድርገውት ነበር።
የራይላ ኦዲንጋ ሞት ዜና ከተሰማ በኋላ የኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ፖለቲከኞች እና መሪዎች የሐዘን መግለጫዎችን እያወጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የተሰማኝን ሐዘን እገልጻለሁ፤ ነፍሳቸው በሰላም ትረፍ" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
ራይላ ኦዲንጋ በኬንያ ታዋቂ ከሆነ ቤተሰብ ነው የተወለዱት።
ለአሥርታት የዘለቀው የፖለቲካ ሕይወታቸው ቤተ መንግሥት አላደረሳቸውም።
ኬንያ ከእንግሊዝ ነፃ ስትወጣ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ያገለገሉት አባታቸውም ዋናውን መንበር ማግኘት አልቻሉም።
አዲንጋ አምስት ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረዋል። መራጮች ግን ፊታቸውን እንዳዞሩባቸው ቆይተዋል።
ለመንበሩ የቀረቡት እአአ በ2008 ጠቅላይ ሚንስትር የሆኑበት አጋጣሚ ነው።
ኦዲንጋን የሚከተሉ ብዙ ደጋፊ ነበሯቸው።
ወዳጅ እና አድናቂዎቹ “ባባ” (አባት)፣ “አግዋምቦ” (የአምላክ ሥራ) እና “ቲንጋ” (ትራክተር) በሚል ቅጽል ስም ይጠሯቸዋል። ስሞቹ እአአ በ1997 ምርጫ ከፓርቲያቸው ምልክት የተወሰዱ ናቸው።
ራይላ በሰልፎች ላይ ከደጋፊዎቸቻው ጋር በሬጌ ዘፈኖች መድረኮች ላይ ሲደንሱ ማየት የተለመደ ነበር። ፈጣን ያልሆነው ዳንሳቸው የ“ራይላ ዳንስ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
ኦዲንጋ እግር ኳስ ይወዱ ነበር። የእንግሊዙ አርሴናል ደጋፊም ነበሩ። ኦዲንጋ ምርጫ በመጣ ቁጥር የፖለቲካ ጥምረት በመመስረት ይታወቃሉ።
ለመጨረሻ ጊዜ በተወዳደሩበት የኬንያ ምርጫ 'አዚሚዮ ላ ኡሚጃ' በሚል መሪ ቃል ነበር የተወዳደሩት። ይህም የስዋሂሊ ቃል ሲሆን ‘የአንድነት ቃል ኪዳን’ የሚል ግርድፍ ትርጉም አለው።
ኦዲንጋ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ የኬንያን ትልልቆቹን ሁለት ፖለቲካ ሥርወ መንግሥታት ይወክላሉ።
በአውሮፓውያኑ 2017 በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው ተወዳድረዋል። በቀጣዩ ዓመት 'ዘ ሃንድ ሼክ' ተብሎ በተሰየመው ውል በጋራ ለመስራት ተስማሙ።
ኦዲንጋ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ የኡሁሩ ኬንያታን የልማት ዕቅዶች ለማስቀጠል ቃል ገብተው ነበር። ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ኬንያውያንን በገንዘብ ለመደገፍም ቃል ገብተዋል።
6000 የኬንያ ሽልንግ (50 ዶላር) በየወሩ ሊሰጡ ቃል የገቡ ሲሆን፤ ገንዘቡም ከአዲሱ የማኅበራዊ ጥበቃ ፈንድ ይገኛል ተብሏል።
ኦዲንጋ “ባባ ኬር” የሚል ሐሳብም አቅርበው ነበር።
ሐሳቡ የጤና አገልግሎት በተመጣጠኝ ዋጋ ለመስጠት ያለመ ነው። ከ56 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ላላት አገር ራሳቸውን የአባት ባህሪን እንደተላበሰ መሪ ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'የመጨረሻ ሙከራ'
እአአ በ2022 የተካሄደው ምርጫ ለኦዲንጋ የፕሬዚዳንትነት ሙከራ የመጨረሻ ዕድል ተብሎ ነበር።
ከዚያ በፊትም በ2017ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ “የመጨረሻ ሙከራቸው” መሆኑን ገልጸው ነበር።
እአአ መጋቢት 2022 ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ግን ሐሳባቸውን ቀየሩ።
ኬንያውያን “በእሳቸው ላይ ባላቸው ትልቅ እምነት” እንደገና ለፕሬዝዳንትነት እንዲወዳደሩ መጠየቃቸውን በመግለጽ ውሳኔውን የቀለበሱበትን ምክንያት ተናግረዋል።
ኦዲንጋ የቀድሞ የፍትሕ ሚንስትሯ ማርታ ካሩአን ለምክትል ፕሬዝዳንትነት አብረዋቸው እንዲወዳደሩ መምረጣቸው ታሪካዊ አጋጣሚ ተብሏል።
አንድ ለፕሬዚዳነት የሚወዳደር ዕጩ ምክትሉ ሴት እንድትሆን ሲመርጥ የመጀመሪያው ነበር።
የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸው ይህንን ውሳኔ ከቀድሞው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ጋር ሲያነጻጽር ተደምጧል።
ኦዲንጋ ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ለማግኘት ቁልፍ ያሏቸው ቦታዎች ላይ ቢሠሩም ምርጫውን አላሸነፉም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አባት እና ልጅ በኬንያ ፖለቲካ
ኦዲንጋ የአባታቸው ጃራሞጊ ኦዲንጋ የፖለቲካ አልጋ ወራሽ ተደርገውይወሰዳሉ።
ጃራሞጊ ከነፃነት በኋላ የመጀመሪያው የኬንያ ምክትል ፕሬዝደንት ነበሩ። በወቅቱ ፕሬዝዳንት ከነበሩት ጆሞ ኬንያታ ጋር ባለመግባባታቸው ከመንግሥት ኃላፊነታቸው እአአ በ1966 ለቀቁ።
ጃራሞጊ ኦዲንጋ ከሶቪየት ኅብረት እና ከቻይና ጋር መቀራረብን መረጡ።
ጆሞ ኬንያታ ደግሞ ከአሜሪካ እና ከሌሎች ምዕራባውያን ኃያላን መንግሥታት ጋር ኅብረት መፍጠርን መርጠዋል።
አለመግባባቱ ተባብሶ ቀጥሎ፤ ጃራሞጊ ኦዲንጋ ለ18 ወራት ታስረው በ1971 ተፈቱ።
ራይላ ኦዲንጋም የፖለቲካ እስረኛ ነበሩ። በኬንያ ለረዥም ጊዜ በእስር ላይ በማሳለፍ ይታወቃሉ።
ከአንድ ፓርቲ አምባገነን አገዛዝ ጋር ባደረጉት ትግል ሁለት ጊዜ (ከ1982 እስከ 1988 እና ከ1989 እስከ 1991) ታስረዋል። የታሰሩት ደግሞ የጆሞ ኬንያታ ተተኪ በሆኑት ዳንኤል አራፕሞይ ዘመን ነው።
በ1982 መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክረዋል በሚል ነውለእስር የተዳረጉት አጋጣሚው ወደ አገር አቀፍ መድረክ ያሸጋገራቸው ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ስመ ጥር የቅስቀሳ እና የስትራቴጂ መሪ
ከአሥስታት በኋላ በኬንያ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ተጀመረ።
ኦዲንጋ ዋናውን መንበር ለመያዝ በተደጋጋሚ ያደረጉት ሙከራ ፍሬ አላፈራም። በርካታ ጊዜም ምርጫው ተጭበርብሯል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት የነበሩት ምዋይ ኪባኪ የ2007 ምርጫን አጭበርብረዋል ማለታቸው ኬንያን ወደ ከፍተኛ ቀውስ ያመራት ነበር።
ከምርጫው በኋላ በተነሳው ብጥብጥ 1 ሺህ 200 ሰዎች ተገደሉ። ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቤታቸውን ተፈናቅለዋል።
በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን የተመራ ቡድን ባደረገው ጥረት የጥምር መንግሥት ተቋቋመ።
ኦዲንጋም የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቦታ ይዘው ነበር። ከኪባኪ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት "የበላይነት ጦርነት" ሲሉ ገልጸውታል።
ኦዲንጋ በ2017ቱ ምርጫ በኬንያታ ተሸንፈዋል። የምርጫውን ሽንፈት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ድል ቀልብሰውታል።
ፍርድ ቤቱ በሰፊው ባብራራው የሕግ ጥሰቶች ምክንያት የምርጫ ውጤቱን ውድቅ አድርጎታል።
ምርጫው ሲደገምም ኦዲንጋ ራሳቸውን አገለሉ። ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ መፍጠር አለመቻሉን ጠቅሰው ነው ራሳቸውን ያገለሉት።
ይህም ኬንያታ በድጋሚ እንዲመረጡ መንገዱን ከፈተ።
ስመ ጥር የቅስቀሳ እና የስትራቴጂ መሪ መሆናቸው የሚነገርላቸው ኦዲንጋ፤ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በተካሄደ ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ራሳቸውን "የሕዝብ ፕሬዝደንት" ብለው አወጁ።
በኬንያታ ዳግም መመረጥ ንዴታቸውን ለማሳየት በኬንያታ ቤተሰብ ባለቤትነት ከተያዙት በርካታ የንግድ ድርጅቶች እንዳይጠቀሙ ያቀረቡትን ጥሪ ደጋፊዎቻቸው ተቀብለዋል።
ይህም የፖለቲካ እና የምጣኔ ሃብት ቅሬታቸውን ለማሳየት ካደረጉት በርካታ ተቃውሞዎች አንዱ ነበር።
ከተቃውሞዎች ጥቂቶቹ ወደ ሁከት ተቀይረው የሰው ሕይወት ጠፍቷል። ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ውድቀትም አስከትለዋል።
በ2018 በኦዲንጋ እና በኬንያታ መካከል ዕርቅ ወረደ። ከዚያ ወዲህ ሕዝቡ በኑሮ ውድነት የተነሳ ከፍተኛ ቁጣ ቢያሳይም ኬንያ ትልቅ ተቃውሞ አላስተናገደችም።
ሁለቱ ፖለቲከኞች የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታን መመለስን ጨምሮ በሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፊ ለውጦችን ለማድረግ “ቢውልዲንግ ብሪጅ ኢኒሼቲቭ" የተባለ የለውጥ ሐሳብ ይዘው ቀርበው ነበር።
በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለውን ፉክክር ለማቆም፤ ኦዲንጋን ለፕሬዝዳንትነት በመደገፍ ኬንያታ ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩን ቦታ ለመያዝ ያሰቡበት ዕቅድ ነው የሚል ሰፊ ግምት ነበር።
ዕቅዳቸው ግን ከግብ ሳይደርስ ቀረ። ፕሬዝዳንቱ ለውጡን ያስኬዱበት መንገድ ሕገ ወጥ ነው በሚል ነው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውድቅ ያደረገው።
ኦዲንጋ እና ቤተሰባቸው
ኦዲንጋ ከማማ አይዳ ጋር ትዳር መሥርተው አራት ልጆችን አፍርተዋል። በሕይወት የሌለው ፊደልን ጨምሮ ሮዝሜሪ፣ ጁኒየር እና ዊኒ ይባላሉ ልጆቻቸው።
ፊደል ስሙን ያገኘው ከኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ ነው።
ኦዲንጋ ስሙን የመረጡት ልጃቸው በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በመወለዱ እንደሆነ እና “በቬትናም ጦርነት ወቅት ካስትሮ አሜሪካን በመቃወማቸው” ነው ብለው ነበር።
ኦዲንጋ የበኩር ልጃቸውን ተተኪ አድርገው ሲያዘጋጁ ቢቆዩም፤ ፊደል በ2015 በ41 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
እአአ በ2017 ሴት ልጃቸው ሮዝሜሪ በአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚገርለትን የድሆች መንደር ኪቤራን በመወከል ለሕዝብ እንደራሴነት ለመወዳደር ፍላጎት አሳይታ ነበር።
አባቷ አካባቢውን ለ20 ዓመታት በሕዝብ አንደራሴነት ወክለዋል። ልጃቸው በጤና ምክንያት ራሷን ከውድድሩ አግልላች።
ኦዲንጋ በኬንያ መስፈርት ከበርቴ የሚባሉ ናቸው።
የጋዝ ሲሊንደር አምራቹ ኢስት አፍሪካ ስፔክተር እና መቀመጫውን ኪሱሙ ያደረገው ሞላሰስ ፕላንት በኩል የኤታኖል ዘርፍ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰዋል።
የዘር ሐረጋቸው በኬንያ በትልቅነቱ አራተኛ ከሆነው ሉኦ ይመዘዛል።












