ኢትዮጵያዊቷ የእጽዋት ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር መሠረት ተሰማ

ረዳት ፕሮፌሰር መሠረት ተሰማ

ለመጨረሻ ጊዜ ያያችሁት እንስሳ ምንድን ነበር? ቀለሙ፣ ቅርጹ ትዝ ይላችሁ ይሆን? ከሌሎች እንስሳትስ በምን ትለዩታላችሁ?

መልካም፤ አሁን ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ምግብ እና ሥነ መአዛ እንዲሁም መድኃኒት የሚሰጡን እና ህይወታችን ውስጥ በብዙ መልኩ አስተዋጽኦ ስላላቸው እጽዋት እናንሳ።

በቅርቡ - ምናልባት ትናንት ማታም ሊሆን ይችላል - ያያችሁት እጽዋት ምንድን ነው?

በዚህ መካከል፣ ከእጽዋቱ ምስል ይልቅ ወደ አእምሮአችሁ የእንስሳቶቹ ቀድሞ የሚመጣ ከሆነ ችግሩ የእናንተ ብቻ አይደለም።

አብዛኞቻችን አካባቢያችን ያሉ እጽዋትን የማስተዋል ችግር አለብን። ተመራማሪዎች ይህንን ‘plant blindness’ ብለው ይጠሩታል።

ረዳት ፕሮፌሰር መሠረት ተሰማ ግን ከልጅነቷ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ከአእምሮዬ አይጠፋም የምትለው፣ ሽታው ሳይቀር ውልብ የሚልባት አንድ እጽዋት አለ - ጠጅ ሳር።

ከአያቷ ነው የወረሰችው፤ ሽታው ስለሚያስደስታት ብቻ ሳይሆን ለጤናም ጠቃሚ ነው የሚል እምነት ስላላት ከጓሮ አትክልቶቿ መካከልም አንዱ ነው።

“አያቴ ልብሶቿን አጥባ ጠጅ ሳር ታደርግበት ስለነበር ሁሌም ‘ሎሚ ተሸክማ ነው እንዴ የምትዞረው?’ እል ነበር። አንድ ቀን ደግሞ ለእኔ ልብስ ሰርታ በጠጅ ሳር ጠቅልላ አመጣችልኝ። ሽታው እስከ ዛሬ ከህሊናዬ አልጠፋም” ትላለች።

ከዚያ በኋላ ግን፣ ሥራዋም ህይወቷም ከተለያዩ የእጽዋት ዓይነቶች ጋር ስለሆነ ለእሷ ‘ለመጨረሻ ጊዜ ያየሽውን እጽዋት ታስታውሺው ይሆን?’ ብሎ ማለት ቀልድ ነው።

መሠረት፣ የሁለት ልጆች እናት እና በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የእጽዋት ተመራማሪ ናት።

በዚህ ጊዜ በግብርና በተለይ ደግሞ ከድርቅ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የእጽዋት ዓይነቶች ድርቅ መቋቋም እንዲችሉ እንዴት ማድረግ ይቻላል በሚለው ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ነው።

መሠረት እጽዋት የውሃ እጥረት የሚፈጥረውን ውጥረት መቋቋም እንዲችሉ እና እንደ ማሽላ እና በቆሎ ያሉ ሰብሎች ደግሞ እንዴት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ማላማድ ይቻላል በሚል ላይ አተኩራ እየተመራመረች ነው። 

እንደ ሰው የሚፈሩት እጽዋት

“እኛ [ሰዎች] ይደክመናል፣ ይጨንቀናል፣ እንፈራለን። በተለይ ስንጨነቅ ጭንቀት የምንቋቋምበት ሆርሞን እናመነጫለን። እጽዋትም እንደዚያ ያደርጋሉ፤ ይጨነቃሉ። በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ሆርሞን ያመነጫሉ።”

እጽዋት የአየር ንብረትን ለመቋቋም ቁመታቸው እና ቅጠላቸውን በመቀነስ፣ ሥራቸውን በማብዛት፣ አንዲሁም ከሌላ ቦታ እርጥበት በመውሰድ እራሳቸውን ለማቆየት እንደሚጥሩ ታስረዳለች።

መሠረት ስለ እጽዋት ስትናገር አኗኗራቸው ራሱን የቻለ ምስጢር አለው በማለት ነው። “የሚያስፈልጋቸው ነገር በሚፈልጉት ጊዜ እና ቦታ ፕሮግራም አድርገው ነው የሚጠቀሙት።”

ለምሳሌም “ስራቸው ካየን እጽዋት መቼ ምን አይነት ስር እንደሚኖራቸው ይወስናሉ። ውሃ ሲያጥራቸው ደግሞ ወደ ጎን ሳይሆን ወደ ታች ነው የሚያድጉት። በዚህ ጊዜ ትላልቅ ሳይሆን ትናንሽ ስሮች በማውጣት ውሃ ወዳለበት ቦታ በመሄድ ውሃ ይወስዳሉ። በአጠቃላይ ግን እጽዋት ተጠንተው ያላለቁ ብዝሐ-ህይወት ናቸው” ትላለች።

በሌላ በኩል አፈር ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥቃቅን ነፍሳት መኖራቸውን የምትናገረው ረዳት ፕሮፌሰር መሠረት፣ እነዚህ አፈር ውስጥ የሚገኙ ነፍሳት ለእጽዋት የሚሰጡትን ጥቅም እያጠናች ነው።

“እነዚህ እጽዋት በቀላሉ ከአካባቢያቸው መዓዛ እንዲወስዱ፣ መዓዛዎቹ እንዲፈጠሩ፣ ውሃ በቀላሉ ከሌላ ቦታ እንዲያገኙ ያደርጋሉ። በተጨማሪም በሚያመነጩት ኬሚካል ምክንያት እጽዋት ያለውን የውሃ እጥረት እንዲያውቁ፣ ከዚህ በመነሳት እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ፣ እድገታቸው እንዲቀይሩ ያደርጋሉ። ስለዚህ ነፍሳቶቹ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ናቸው ብዬ ስለማምን በሰፊው እንድንጠቀምባቸው የሚያስችል ሥራ ላይ አተኩራለሁ” ብላለች።

‘ሕክምና ማጥናት ነበር የምፈልገው’

ለወላጆቿ የበኩር ልጅ የሆነችው መሠረት ለታናናሾቿ አርአያ እንድትሆን ይጠበቅባት እንደነበር ትናገራለች።

በምዕራብ ኢትዮጵያ ተወልዳ ያደገችው መሠረት፣ ይህንን ግዴታዋን ለመወጣት በትምህርቷ በርትታ ወደ ዩኒቨርስቲ መግባት ችላለች።

መሠረት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ አምጥታ ግብርና እንደደረሳት የሰማች ጊዜ ግን ፈጽሞ ደስ አላላትም ነበር።

“በወቅቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ የምንገባው በቁጥር ጥቂት ነበርን፤ እኔ ደግሞ ፍላጎቴ ሕክምና ማጥናት ነበር። አባቴ የእንስሳት ሐኪም ነው፤ ብዙ የሳይንስ መጽሐፍ እያስነበበ ነው ያሳደገኝ። ስለዚህ ሕክምና መማር ነበር የምፈልገው” ትላለች።

አክላም “ምደባዬን ያየው አጎቴ ነበር፤ ምን እንደሚፈልግ ያውቅ ስለነበረ ግን መጀመሪያ ለአባቴ ነገረው። አባቴ እንዳላዝን ከእናቴ ጋር በመምከር ዋናው ወደ ዩኒቨርሲቲ መሄድ ነው፤ ብለው ቁጭ አድርገው ነገሩኝ። ግን አዘንኩ።”

አያይዛም “ወደ ዩኒቨርሲቲ ስገባ [በወቅቱ የሐዋሳ ግብርና ኮሌጅ ይባል ነበር] ጥቂት ተማሪዎች ነበርን። እኔ ወደ ባዮሎጂ አዘነብል ስለነበረ የእጽዋት ምርትን [Plant production] መረጥኩ፤ ከዚያ በኋላ ጥሩ ውጤት እያመጣሁ ወድጄው ተማርኩ። አሁን በፍቅር የምሰራበት መስክ ነው” ትላለች።

በጎዴ ውሃ በጀርባዋ ተሸክማ የምትሄድ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሳይንስ ያለፈ ትስስር

መሠረት እጽዋትን ዘወትር ጸባያቸው መከታተል እና ማስተዋል ኑሮዋ ነው። ከዚያም ባሻገር “የመኖር ምክንያታችን ናቸው” ስትል ትገልጻቸዋለች።

እውነት ነው፤ በዋናነት የምንተነፍሰውን ኦክስጅን የሚሰጡን እጽዋት ናቸው። ሆኖም የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትላቸው ጫናዎች የእጽዋት መጥፋት እና የብዝሐ-ህይወት መቀነስ ያሰጋታል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ትልቁ ችግር ደግሞ ድርቅ እና ከባድ የውሃ እጥረት ነው።

“ሰዎች ፀሐይ ሲበረታብን ወይ ሲበዛብን እንንቀሳቀሳለን፤ እጽዋት ግን እንደዚያ አይደሉም። ባሉበት ሆነው ነው የሚቋቋሙት። ይሄንን በተፈጥሮ መቋቋም የሚችሉ አሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አይችሉም። ስለዚህ መቋቋም የሚችሉት፣ መቋቋም ከማይችሉት ጋር እንዲዳቀሉ እያደረግን ነው” ትላለች።

እጽዋት እንዴት ድርቅን መቋቋም ይችላሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ረዳት ፕሮፌሰር መሠረት በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ድርቅ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው የዝናብ እጥረት እና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጋር በተያያዘ የሚመጣ ነው ትላለች።

“ይህ ትልቅ ችግር ነው [የአየር ንብረት ለውጥ]፤ የሚቀጥልም ነው። በዚህ ምክንያት ተላላፊ በሽታዎች ይጨምራሉ የሚሉ ግምቶች አሉ። ስለዚህ ሁላችንም የአየር ንብረት ለውጥ መኖሩን ማመን፣ አካባቢያችን ላይ የሚከሰቱ ነገሮች ማስተዋል፣ ፖሊሲ የሚቀርጹ ሰዎች ደግሞ ይሄንን ግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ ሊሰሩ ይገባናል” ስትል ታስረዳለች።

ድርቅ የሚያስከትላቸው አደጋዎች ቀጣይ የሰው ልጅ ስጋቶች ሲሆኑ፣ እጽዋት ይሄንን እንዴት መቋቋም ይችላሉ? ድርቅ መቋቋም የሚችሉ እጽዋትስ ወደ ገበሬው እንዴት ማቅረብ ይቻላል? የሚሉ የምርምር ሥራዎች ላይ ማተኮሯንም ትናገራለች።

አክላም የምንኖርበትን አካባቢ ተላምደው የቆዩ የእጽዋት አይነቶች እንዳይጠፉም ለመከላከል ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ታነሳለች።

በኢትዮጵያ አርሶ አደሩ ጥገኛ መሆን የማይፈልግና ሁሌም የግብርና ሥራውን ማከናወን እንደሚፈልግ የሚናገሩት ረ/ፕሮፌሰር መሠረት፤ ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጥ የተለያዩ ችግሮችን እያስከተለበት ነው ይላሉ።

“ይሄንን አስቀድሞ መተንበይ ስለሚቻል፣ በተለይ ፖሊሲ አርቃቂዎች ተመራማሪዎች የሚያቀርቡትን መረጃ ተጠቅመው ገበሬውን አስቀድመው ሊያዘጋጁት ይገባል” ብላለች።

ይህም ሰዎች አካባቢያቸው ላይ የተለያዩ እጽዋት የመትከል ልምድ በማሳደግ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያላቸው ነገሮች በመቀነስ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነትም አላት።

“የአየር ንብረት ለውጥ መኖሩን ማመን አለብን፤ ከእጽዋት ውጪ ደግሞ መኖር አንችልም። ስለዚህ ጥንቃቄ የተሞላበት የአኗኗር ዘይቤ ካልተከተልን ወደ መጥፊያችን ነው የምንሮጠው” በማለት ያሳስባሉ።

እስካሁን የሰው ልጅ ብዙ ነገሮች ላይ ጥፋት መፈጸሙን የምትጠቅሰው ረ/ፐሮፌ. መሠረት፤ “ከአሁን በኋላ ግን መቆጠብ አለብን። በየቀኑ ቤት ውስጥ የምናፈሰውን ውሃ፣ የምንጠቀመውን የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችንን. . . ከማስተዋል መጀመር አለብን።”

ረዳት ፕሮፌሰር መሠረት ተሰማ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት አነስተኛ ገበሬዎችን ማገዝ የሚችሉ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ የግብርና ምርምሮች ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሰራበት የ'ዋን ፕላኔት ፌሌውሺፕ ሎሬት' በመሆን ተመርጣለች።