በአፋር ክልል ከ1.3 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለምግብ እጥረት መጋለጡ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, MSF
በአፋር ክልል በጦርነት እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለምግብ እጥረት መጋለጡ ተገለጸ።
የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በክልሉ የተከሰተው ድርቅ፣ ጎርፍ እና ጦርነት ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሕዝብን ለከፋ የምግብ እጥረት አጋልጧል።
ትናንት ሰኔ 2/2014 ዓ.ም. ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በአፋር ክልል እየጨመረ የመጣው የምግብ ቀውስ ስጋት ሆኖብኛል ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በመግለጫው፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መሠረታዊ የሚባሉ የጤና ማዕከላትን እንዲሁም ንጹህ የመጠጥ ውሃ በማያገኙበት ሁኔታ እየኖሩ እንደሆነ እና በርካታ ሕጻናት በከፋ የምግብ እጥረት ሕይወታቸውን እያጡ መሆኑን ገልጿ።
ምንም እንኳን አቶ መሐመድ በምግብ እጥረት ሕይወታቸው ያለፈ ሕጻናት ስለመኖራቸው "መረጃው የለኝም" ቢሉም፣ የምግብ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ከ1.3 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል ከመንግሥት እና ከዓለም ምግብ ፕሮግራም የምግብ እርዳታ እየደረሰው ያለው 900ሺህ ለሚሆነው ብቻ ነው ብለዋል።
“ለ340 ሺህ ሕዝብ በሃብት እጥረት ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ ማድረስ አልተቻለንም። የሰብአዊ እርዳታ ያልደረሳቸው ወገኖችን ለመድረስ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጥረት እንዲያደርጉ አሳውቀናል” ብለዋል።
“ከፍተኛ ድርቅ አለ። በሦስት ምዕራፍ የተከፈተብን ጦርነት አለ። ይህ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል” ያሉ ሲሆን፣ መንግሥት እና ሰብአዊ ድርጅቶች ችግር ላጋጠማቸው ሰብአዊ ድርጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።
“መንግሥት በተቻለ አቅሙ እርዳታ እያቀረበ ነው። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለ630 ሺህ ሕዝብ የዕለት ደራሽ ምግብ እያደረሰ ነው” ብለዋል።
ወደ 100 ሺህ ለሚጠጉ ሕጻናት አልሚ ምግብ እየቀረበላቸው መሆኑንም አቶ መሐመድ ተናግረዋል።
እንደ አቶ መሐመድ ገለጸ፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት መሠረተ ልማቶች በመውደማቸው እና ንብረት በመዘረፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም በመጠለያ ጣቢያዎች እንዲቆዩ ተገደዋል።
ኤምኤስኤፍ በትናንት መግለጫው፣ በአፋር ክልል ካሉ የጤና ማዕከላት አብዛኞቹ አገልግሎት ላይ እንዳልሆኑ ገልጾ፣ በሥራ ላይ ያሉት 20 በመቶ ብቻ ናቸው ብሏል።
ሆኖም በአፋር ክልል እየተከሰተ ያለው ቀውስ ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሞ፣ የረድኤት ማኅበረሰቡ አስቸኳይ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ እንደሆነ አሳስቧል።













