ኢትዮጵያ ግብፅን አሸንፋ ምድቡን መምራት ጀመረች

የኢትዮጵያ ቡድን ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, EFF

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብፅ አቻውን በማሸነፍ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የተደለደለበትን ምድብ መምራት ጀመረ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ማላዊ ላይ የግብፅ አቻውን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ነው ያሸነፈው።

ዋሊያዎቹ ፈርዖኖቹን 2 ለ 0 ያሸነፉት በመጀመሪያው አጋማሽ ዳዋ ሁጤሳ እና ሽመልስ በቀለ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ነው።

ዋሊያዎቹ በግብፅ ብሔራዊ ቡድን ላይ የበላይነትን ይዘው ባመሹበት ጨዋታ የፊት መስመር ተጫዋቹ አቡበከር ናስር እና አማካዩ ጋቶች ፓኖም ድንቅ ብቃታቸውን አሳይተዋል።

በጨዋታው ኢትዮጵያ 9 ሙከራዎችን ስታደርግ ግብፅ በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም አይነት የጎል ሙከራ አላደረገችም።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ይህን ጨዋታ ከሜዳዋ ውጪ በባዕድ አገር ሜዳ እንድታደርግ ብትገደድም: ዋሊያዎቹ ከአገሪቱ ዜጎች እና ትንሽ ከማይባሉ በስታዲየም ከተገኙ ኢትዮጵያውያን ተመልካቾች ድጋፍ ተችሯቸዋል።

ኢትዮጵያ ለ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫማጣሪያ ከማላዊ፣ ከጊኒ እና ከግብፅ ጋር መመደቧ ይታወቃል።

የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋን በማላዊ 2ለ1 የተሸነፈችው ኢትዮጵያ፤ ግብፅን ማሸነፏን ተከትሎ 3 ነጥብ አግኝታለች::

በዚህ ምድብ የሚገኙት ጊኒ እና ማላዊ ባደረጉት ጨዋታ ባለሜዳዋ ጊኒ ማላዊን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

በዚህ ምድብ የሚገኙት አራቱም ቡድኖች 3 ነጥብ ያላቸው ሲሆን ኢትዮጵያ በጎል ብልጫ አንደኛ ሆናለች።

ግብፅ ደግሞ በ1 የግብ ዕዳ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ካፍ የኢትዮጵያ ሜዳዎች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያን ለማካሄድ ብቁ አይደሉም ማለቱን ተከትሎ ነው ዋሊያዎቹ ግብፅን ማላዊ ላይ ለመግጠም የተገደዱት።

ከጨዋታው በፊት አሰልጣኙ እና አምበሉ ምን ብለው ነበር?

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከጨዋታ በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የጉዳት ስጋት ብዙም እንደሌለባቸው ይፋ አድርገው ነበር።

"ከምድባችን ለማለፍ ከግብፅ ጋር የምናደርገው ፍልሚያ ወሳኝ" ነው ብለዋል አሠልጣኙ።

ውበቱ፤ የግብፁ አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ በጨዋታ በጉዳት ምክንያት አለመሠለፉ እፎይታን ሰጥቷቸው እንደሆነ ተጠይቀው ነበር።

"ሞ ሳላህ ኖረም አልኖረም እኛ ወደሜዳ የምንገባው ድል ለመቀዳጀት ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል የነበረ ሲሆን ይህም ተሳክቶላቸዋል።

የሞ ሳላህ ተፅዕኖ የማይካድ እንደሆነ የገለጡት አሠልጣኙ "ነገር ግን እሱ የለም ብለን የምንቀይረው ነገር የለም" የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር።

ለግብፁ ኤል-ጉና የሚጫወተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል ሽመልስ በቀለም ለጨዋታው በፊት "አግዝፈን የምናየው ቡድን የለም" ሲል ተደምጧል።

"ዋናው ከስህተታችን ተምረን የተሻለ ውጤት ማምጣታችን ነው" ብሏል ሽመልስ።

በእርግጥም የኢትዮጵያ ቡድን ካለፈው ስህተቱ በመማር በርካታ ነገሮችን መለወጥ መቻሉን በጨዋታው አሳይቶ በሁሉም በኩል የበላይ በመሆን የአፍሪካ ኃያል ቡድን የሆነውን የግብፅ አቻውን ለማሸነፍ ችሏል።

በስታዲየም ችግር ምክንያት ከሜዳው ውጪ ከደጋፊዎቹ ርቆ ለሁለት ሳምንት ገደማ በባዕድ አገር የሰነበተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያስመዘገበው ውጤት በርካቶችን አስደንቋል።