ስለዛሬው ፍልሚያ የኢትዮጵያና የግብፅ አሠልጣኞች ምን አሉ?
![ሞ ሳላህ [ግራ] አቡበከር ናስር [ቀኝ]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/fe45/live/9dbbfbd0-e7cc-11ec-8935-4f1eb8b88d37.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ኮትዲቯር ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞለታል።
በዚህ የአህጉሪቱ አንጋፋ የእግር ኳስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ሃገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያካሄዱ ነው።
ከግብፅ፣ ማላዊና ጊኒ የተደለደሉት ዋሊያዎች በመጀመሪያው ጨዋታቸው ድል ርቋቸዋል።
ባለፈው እሑድ በማላዊ ሜዳ የተጫወቱት ዋሊያዎቹ በኳስ ቁጥጥር በልጠው ታይተዋል።
ነገር ግን በተከላካይ መስመር የተገኙ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶችን የማላዊው ምሃንጎ ያለርሕራሔ ወደ ጎል ቀይሯል።
በሁለተኛው አጋማሽ ወጣቱ የፊት መሥመር ኮከብ ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ጎል ቢያደርግም ዋሊያዎቹን ከሽንፈት ለመገላገል በቂ አልነበረም።
የዋሊያዎቹ አምበል ሽመልስ በቀለ ብሔራዊ ቡድኑ ከሁለት ጨዋታዎች "ቢያንስ አራት ነጥብ ይዘን ለመመለስ አቅደናል" ቢልም ይህ የሚሆን አይመስልም።
ኢትዮጵያ ዛሬ ምሽት 1፡00 ሰዓት ፈርዖኖቹን ትገጥማለች።
ዋሊያዎቹ
አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከዛሬው ጨዋታ በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የጉዳት ስጋት ብዙም እንደሌለባቸው ይፋ አድርገዋል።
አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው በገጠመው ጉዳት የዛሬው ጨዋታ እንደሚያመልጠው ገልጠዋል።
"ከምድባችን ለማለፍ ከግብፅ ጋር የምናደርገው ፍልሚያ ወሳኝ" ነው ብለዋል አሠልጣኙ።
ውበቱ፤ የግብፁ አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ በዛሬው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት አለመሠለፉ እፎይታን ሰጥቷቸው እንደሆነ ተጠይቀው ነበር።
"ሞ ሳላህ ኖረም አልኖረም እኛ ወደሜዳ የምንገባው ድል ለመቀዳጀት ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የሞ ሳላህ ተፅዕኖ የማይካድ እንደሆነ የገለጡት አሠልጣኙ "ነገር ግን እሱ የለም ብለን የምንቀይረው ነገር የለም" የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ከማላዊ ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ የሚታይ ለውጥ የፈጠረው ጋቶች ፓኖም በዛሬው ጨዋታ ቋሚ ተሰላፊ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።
አሠልጣኙ በተለመደው የ4-3-3 አሠላለፍ አሊያም በአዲስ መልክ ይገቡ እንደሆነ ጨዋታው አንድ ሰዓት ሲቀረው የሚለይ ይሆናል።
ለግብፁ ኤል-ጉና የሚጫወተው አምበሉ ሽመልስ በቀለም "አግዝፈን የምናየው ቡድን የለም" ሲል ተደምጧል።
"ዋናው ከስህተታችን ተምረን የተሻለ ውጤት ማምጣታችን ነው" ብሏል ሽመልስ።
ፈርዖኖቹ
ግብ ጠባቂው ኤልሻናዊና ትሬዝጌን ጨምሮ ሞሐመድ ሳላህ ለግብፅ አይሰለፉም ከተባሉ ተጫዋቾች መካከል ናቸው።
የፈርዖኖቹ አሠልጣኝ ኢሃብ ጋላል "እኒህን ተጫዋቾች ማጣታችን ቢያስከፋንም ሌሎች ድንቅ ብቃት ያላቸው እግር ኳሰኞች አሉን" ብለዋል።
"የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ አቋም ላይ ነው" ያሉት አሠልጣኙ ቡድናቸው ዋሊያዎቹን ለመፋለም እንደተዘጋጀ አሳውቀዋል።
ኢሃብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ማድረግ የሚገባውን ጨዋታ በባዶ ሜዳ ማድረጉ ጉዳት እንዳለው አልካዱም።
አምበሉ አምር ኤል ሶላያ በበኩሉ “ቀላል የሚባል ጨዋታ የለም” ሲል ከዋሊያዎቹ የሚያደርጉትን ጨዋታ አቅልለው እንደማይመለከቱ ጠቁሟል።
የዛሬውን ጨዋታ ቡሩንዲያዊ ጆርጅ ጋቶጋቶ እንደሚመሩት ታውቋል።
ካፍ የኢትዮጵያ ሜዳዎች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያን ለማካሄድ ብቁ አይደሉም ማለቱን ተከትሎ ነው ዋሊያዎቹ ግብፅን ማላዊ ላይ ለማስተናገድ የተገደዱት።
ኢትዮጵያ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ሳያካትት ባለፉት 11 ጨዋታዎች ድል ሊቀናት አልቻለም።
ግብፅ ደግሞ ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አራቱን ስታሸንፍ በሁለቱ ተረታለች።
የሁለቱ የአፍሪካ ዋንጫ መሥራች ሃገሮች ፍልሚያ ምሽት 1፡00 በማላዊ ሊንጉ ብሔራዊ ስታድዬም ይጀመራል።












