ዋሊያዎቹ ከማላዊና ከግብፅ በሚያደርጉት ጨዋታ ምን ውጤት ይጠበቃል?

አቡበከር ናስር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አቡበከር ናስር

ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ በፈረንጆቹ 2023 በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞለታል።

የአህጉሪቱ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ከፍተኛ አካል ካፍ ዕጣ ደልድሎ አገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን ማድረግ ጀምረዋል።

ኢትዮጵያ በምድብ አራት ከግብፅ፣ ከጊኒ እና ከማላዊ ጋር ተደልድላለች።

ካፍ የኢትዮጵያ ሜዳዎች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ለማድረግ ብቁ አይደሉም በማለቱ ዋሊያዎቹ በገለልተኛ ሜዳ ይጫወታሉ። 

ዋሊያዎቹ በሜዳቸው ለመጫወት “ባለመታደላቸው” ከግብፅ የሚያደርጉትን የመጀመሪያ ዙር ፍልሚያ በባዳ ስታዲየም ሊያደርጉ ወስነዋል።

ነገር ግን በመጀመሪያ ጨዋታቸው ማላዊን የሚገጥሙ ይሆናል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ዋሊያዎቹን እየመሩ ወደ ማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንጉዌ ከማቅናቸው በፊት መግለጫ ሰጥተዋል።

አሠልጣኙ “ፈርዖኖቹን በገዛ ሜዳችን ብንገጥም ደስ ይለን ነበር” የሚል የቁጭት አስተያየት ሰጥተዋል። 

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከግንቦት 16 ጀምሮ ለማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

አሠልጣኝ ውበቱ መጀመሪያ 28 ተጫዋቾችን መልምለው ከሌሶቶ ብሔራዊ ቡድን ጋር አዲስ አበባ ላይ የወዳጅነት ፍልሚያ አድርገው የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን ለይተዋል።

እነማን ወደ ማላዊ ይጓዛሉ?

አሠልጣኝ ውበቱ የባሕር ዳሩ ፋሲል ገብረሚካዔልን፣ የኢትዮጵያ ቡናው ታዳጊ በረኛ በረከት አማረንና የሐዋሳ ከተማውን ዳግም ተፈራ በግብ ጠባቂነት ይዘው ወደ ማላዊ ይሄዳሉ።

አስራት ቱንጆ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ሄኖክ አዱኛ፣ ሱሌይማን ሃሚድ፣ ምኞት ደበበ፣ ያሬድ ባዬ፣ ጊት ጋትኩትና ሚሊዮን ሶሎሞን የተከላካይ መስመሩን እንዲቆጣጠሩ የተመረጡ ናቸው።

የአማካይ መስመሩን የሚመራው ጉምቱው ሽመልስ በቀለ ነው።

በተጨማሪ አማኑዔል ዮሐንስ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ በዛብህ መለዮና መስዑድ ሞሐመድ ተመርጠዋል።

የኢትዮጵያ ቡናው ፈርጥ አቡበከር ናስር የአጥቂውን መስመር እየመራ ወደ ሊሎንጉዌ ያቀናል።

አማኑዔል ገብረመድህን፣ ቸርነት ጉግሳ፣ ዳዋ ሆጤሳ፣ በረከት ደስታና ይገዙ ቦጋለ ሌሎች በአጥቂ መስመር ላይ የሚሰለፉ ናቸው።

ውበቱ እንደተለመደው በ4-4-3 አሰላለፍ ተጋጣሚዎቻቸውን እንደሚገጥሙ ይጠበቃል።

የፕሪሚዬር ሊጉን ኮከብ ጎል አግቢ ሰንጠረዥ በጥምር የሚመራው ነባሩ አጥቂ ጌታነህ ከበደ ከአሠልጣኙ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሳይመረጥ እንደቀረ ውበቱ ጠቁመዋል።

ጌታነህ በዘጠኝ ቁጥር ቦታ አለመኖሩ አቡበከር ናስር ስኬታማ በሚሆንበት መስመር በደንብ እንዲጫወት ዕድል ሊፈጥር ይችላል።

የጌታነህ ከበደን አለመኖር ተከትሎ ሽመልስ በቀለ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ማላዊ ያቀናል።

ሽመልስ በቀለ ሶከር ኢትዯጵያ ከተሰኘው የአገር ውስጥ የስፖርት አውታር ባደረገው ቃለ-ምልልስ ከሁለቱ ጨዋታዎች ቢያንስ አራት ነጥብ ለማግኘት እንደሚጫወቱ ተናግሯል።

ማላዊ

'ዘ ፍሌምስ' በተሰኘ ቅጽል ስሙ የሚታወቀው የማላዊ ብሔራዊ ቡድን ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ከምድቡ ማለፍ ችሎ ነበር።

ዘ ፍሌምስ በዙር 16 ጨዋታ በሞሮኮ ተርትተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

ኢትዮጵያና ማላዊ ከፈረንጆቹ 2003 ጀምሮ በተለያዩ ውድድሮችና በወዳጅነት ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል። 

ማላዊ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ ረትታለች። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

የማላዊ ብሔራዊ ቡድን ዘ ፍሌምስ መጋቢት በወጣው የፊፋ የዓለም የብሔራዊ ቡድኖች ሠንጠረዥ 120ኛ ላይ ተቀምጠዋል።

ዋሊያዎቹ ደግሞ ከዓለም 140ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 44ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የማላዊ ብሔራዊ ቡድን በአብዛኛው አገር ውስጥ በሚጫወቱ ተጫዋቾች፣ መቀመጫቸውን አውሮፓና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ባደረጉ እግር ኳሰኞች የተዋቀረ ነው።

አውሮፓ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች መካከል ለሞልዶቫው ሽሪፍ የሚጫወተው ቻርልስ ፔትሮ ይጠቀሳል።

ኢትዮጵያና ማላዊ እሁድ ግንቦት 26/2014 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በቢንጉ ብሔራዊ ስታድዬም ይጫወታሉ።

አቡበከር ናስር [ቀኝ] ሞሐመድ ሳላህ [ግራ]

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አቡበከር ናስር [ቀኝ] ሞሐመድ ሳላህ [ግራ]

ግብፅ

ሞሐመድ ሳላህ ፈርዖኖቹን ለመቀላቀል ወደ ግብፅ አቅንቷል።

ግብፅ በመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ፍልሚያዋ በሜዳዋ እሁድ ምሽት 4፡00 ሰዓት ጊኒን ታስተናግዳለች።

ፈርዖኖቹ ከምድብ በቀላሉ የማለፍ ግምት ተሰጥቷዋል።

በፕሮፌሽናል እግር ኳሰኞች ማኅበር (ፒኤፍኤ) የዓመቱ ምርጥ ዕጩ ሆኖ የተመረጠው ሳላህ ቡድን እየመራ ወደሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።

ግብ ጠባቂው ሞሐመድ ኤል-ሼናዊን ጨምሮ ሰባት የአል አህሊ ተጫዋች በብሔራዊ ቡድኑ ተካተዋል።

የአርሰናሉ ሞሐመድ ኤልኔኒ እንዲሁም የኢስታንቡል ባሼክሽር አማካይ ሞሐመድ ትሬዚጌ ለፈርዖኖቹ ተመርጠዋል።

ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረገውን ፍልሚያ መርታት የተሳናት ግብፅ አዲስ አሠልጣኝ ቀጥራለች።

ተሰናባቹን ፖርቹጋላዊ አሠልጣኝ ካርሎስ ኬሮዥን የተኩት የ54 ዓመቱ ኢሃብ ጋላል ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ቀዳሚው ዕቅዳቸው እንደሆነ ገልጠዋል።

ግብፅ ከጊኒ ጨዋታዋ ቀጥሎ ኢትዮጵያን በገልለተኛ ሜዳ ለመግጠም ወደ ማላዊ ታቀናለች።

ዋሊያዎቹ ከፈርዖኖቹ ሐሙስ ሰኔ 02/2014 በማላዊ ስታድዬም ምሽት 1፡00 ሰዓት ይፋለማሉ።

“ግብፅ ወጪያችሁን እንቻል ብላናለች”

ከአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ ባሕሩ ጥላሁን መግለጫ ሰጥተዋል።

“ፌዴርሽኑ ዋሊያዎቹን ለመደገፍ የታቸለውን ሁሉ እያደረገ ነው” ብለዋል ዋና ፀሐፊው።

ዋሊያዎቹ ከሌሶቶ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርጉ ፌዴሬሽኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን አቶ ባሕሩ ጠቅሰዋል።

እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋሊያዎቹ ግብፅ የሚያደርጉትን ጨዋታ ማላዊ ላይ እንዲያከናውኑ የወሰነው “ከወጪ አንፃር” መሆኑን ፀሐፊው ጠቅሰዋል።

አልፎም ተጫዋቾቹ ከማላዊ ጨዋታ መልስ እዚያው ሆነው እንዲያገግሙ በማሰብ እንደሆነም አስረድተዋል።

አቶ ባሕሩ “በማላዊ ስታድዬም ከግብፅ ጋር ለመፋለም ቢያንስ 50 ሺህ ዶላር ያስፈልገናል” ብለዋል።

ዋና ፀሐፊው አክለው “የግብፅ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወጪያችሁን እንቻልና ጨዋታው ካይሮ ይሁን” ብሎ እንደጠየቃቸው ይፋ አድርገዋል።

“ነገር ግን...” ይላሉ ዋና ፀሐፊው “... ነገር ግን ይህ ክብረ ነክ ነው ብለን አንቀበልም ብለናል።”

የመጀመሪያው ዙር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በሚቀጥለው ሳምንት ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለተኛው ዙር ጨዋታ በመጪው መስከረም ይካሄዳል።

መስከረም ላይ በሚደረጉት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ታደርጋለች።

ተንታኞ ከምድቡ ለኢትዮጵያ ዝቅተኛ ግምት ቢሰጡም አሠልጣኝ ውበቱና ተጫዋቻቸውን ግን ይህን ለመሻር አቅደዋል።