እግር ኳስ: ካፍ የኢትዮጵያ ስታድየሞች "ይታረሱ" ያለው ለምን ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, KIDUS YOFTAHE
ዋሊያዎቹ በሜዳቸው ማድረግ ያለባቸውን ጨዋታ 'በባዕድ ሜዳ' ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የካፍን መመዘኛ የሚያሟሉ ስታድየሞች የላችሁም መባሉ ነው።
ኢትዮጵያ የሜዳ እጥረት የለባትም ቢባል ማጋነን አይሆንም።
በየክልሉ ቢያንስ አንድ 50 ሺህ ሰው የሚያስተናግድ ስታድየም ተገንብቷል። እና ካፍ ኢትዮጵያ "ደህና" ስታድየም የላትም የሚለው ለምንድነው?
ከቅርብ ጊዜ ክስተት እንነሳ።
ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ማጣሪያዋን ለማድረግ እየተሰናዳች ነው።
ግብፅ፣ ማላዊና ጊኒ ኢትዮጵያ ባለችበት ምድብ ይገኛሉ።
ዋሊያዎቹ በሕጉ መሠረት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጪ ከማላዊ ጋር ያደርጋሉ።
ነገር ግን ቀጣዩ ጨዋታቸው ከግብፅ ጋር በገዛ ሜዳቸው እንደሆነ የካፍ የጨዋታ መረሃ ግብር ያሳያል።
ቢሆንም ይህ ጨዋታ እዚያው ማላዊ እንዲደረግ የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪው አካል ካፍ ወስኗል።
የማላዊ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዝደንት ዋልተር ኒያሚላንዱ "በአገሬ ያላችሁ የሊቨርፑል ደጋፊዎች ሞ ሳላህ ሊመጣላችሁ ነው፤ እንኳን ደስ አላችሁ" የሚል መልዕክት በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
ብዙዎች ይህ "የግብፅ ሤራ ነው" ይላሉ። ለዚህም የሞሐመድ ሳላህ አገር የኢትዮጵያ ሜዳ አይመጥነኝም ብላ ቅሬታ በማቅረቧ ነው ይህ የሆነው የሚል አመክንዮ ያስደምጣሉ።
ነገሩ ግን ወዲህ ነው ይላል የኢትዮጵያን እግር ኳስ በቅርበት የሚከታተለው ፍሬው አሥራት።
"የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንና ስፖርት ኮሚሽኑ ካፍ 'ሜዳዬን አሻሽያለሁ፤ ምርመራ ይደረገልኝ' ብለው በጠየቁት መሠረት ነው ምርመራ የተደረገው" ይላል ፍሬው።
በዚህ ጥያቄ መሠረት የካፍ መርማሪ የሆኑት ግለሰብ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ ባሕር ዳር ስታድየም አቅንተው የሜዳውን ጥራት ተመልክተው ተመልሰዋል።
"ይህ ማለት ግብፅ ሜዳው ይመርመርልኝ አላለችም ማለት አይደለም" ይላል ፍሬው።
"በተመሳሳይ ሰዓት የግብፅ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለካፍ ደብዳቤ አስገብቶ ነበር። ነገር ግን ካፍ መልዕክተኛ የላከው በኢትዮጵያ ጥያቄ መሠረት ነው።"
ፍሬው የግብፅ ደብዳቤ አዲስ አበባ ያለችበትን ከፍታ ወይም "አልቲቲዩድ" በመፍራት የተፃፈ እንጂ የሜዳ ጉዳይን በዋነኛነት የሚዳስስ አይደለም ይላል።
"ሜዳው ይታረስ"
የካፍ መልዕክተኛ የባሕር ዳር ስታድየምን ከእግር እስከ ራሱ ከመረመሩ በኋላ ውጤቱን በጉጉት ሲጠባበቁ ለነበሩት ባለሥልጣናት የሰጡት ምላሽ አዎንታዊ አልነበረም።
መርማሪው "ምን አጎደልን?" በሚል ስሜት ውስጥ ለነበሩት የፌዴራልና የክልል ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ይህን ትዕዛዝ አስተላለፉ፡ "ሜዳው ይታረስ።"
መርማሪው የባሕር ስታድየም የካፍን ዝቅተኛ መመዘኛዎች እንኳ አያሟላም የሚል መርዶ ተናገሩ።
"እርግጥ ስታድየም የመገንባት ችግር የለብንም" ይላል ፍሬው።
ነገር ግን. . . ሲል ያክላል "ነገር ግን ስታድየሞቹ ካፍ የሚጠይቀውን ደረጃ ይዘው አይጠናቀቁም። ውጫዊ ቁመናቸው ያምርና አጨራረሳቸው ግን የሚያስከፋ ይሆናል።"
ካፍ "ሚኒመም ስታንዳርድ" ይላቸዋል። አማርኛው ቢያንስ ይህን እንኳን አሟሉልኝ መሆኑ ነው።
ፍሬው ካፍ ከሚጠይቃቸው በርካታ መመዘኛዎች ጥቂቱን እንዲህ ይጠቅሳል።
"አንደኛው የመጫወቻ ሜዳ ነው። አብዛኛዎቹ ስታድየሞች የመጫወቻ ሜዳቸው ዝናብ ሲዘንብ ውሃ ያቁራሉ። ብዙዎቹ ስታድየሞቻችን ይህን ለማስወግድ የሚያስችል የፍሳሽ ሥርዓት (ድሬይኔጅ ሲስተም) የላቸውም።"
"ከዚያ ውጪ ደግሞ መልበሻ ክፍሎቻችን መቀመጫ አልባ ናቸው። ይህ ደግሞ የካፍን መመዘኛ እንድንወድቅ ከሚያደርገን መካከል ነው።"

የፎቶው ባለመብት, KIDUS YOFTAHE
ፍሬው ይቀጥላል. . .
"አብዛኞቹን ሜዳዎች ተመልክተህ ከሆነ ለደጋፊዎች የተሠራ መቀመጫ የላቸውም። ይህ ደግሞ ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው። ካፍ ውድድሮቹ በመሰል ስታድየሞች እንዲደረጉ በፍፁም አይፈልግም።"
ፍሬው ጨምሮም አብዛኞቹ ሜዳዎቻችን በምሽት ጨዋታ እንዲደረግ የሚያስችል መብራት እንደሌላቸው ያወሳል።
"በተጨማሪ ካፍ ስታደየሞቹ ቢቻል ጣራ እንዲኖራቸው ይጠይቃል። የእኛ ስታድየሞች ደግሞ ጣራ አልባ ናቸው። ሌላው ደግሞ የተሟላ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት "ሚድያ ሩም" [የመገናኛ ብዙኃን ክፍል] ጉዳይ ነው። ይህንንም አላሟላንም።"
"አልፎም ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና ክፍል እንዲኖረን ካፍ ያስገድዳል።"
ፍሬው እንደሚለው ከላይ ከተጠቀሱት መመዘኛዎቹ የተወሰኑት እንኳ ቢሟሉ ጨዋታዎች እየተደረገ ማሻሻያ እንዲከናወን ይፈልጋል፤ ነገር ግን ባሕር ዳርን ጨምሮ ሁሉም ስታድየሞች ዝቅተኛውን መመዘኛ አላሟሉም።
"ካፍ ባሕር ዳር ስታድየምን ከተመለከተ በኋላ ሜዳው ድጋሚ ታርሶ ሣር ይተከልበት ነው ያለው። የፈሳሽ ውሃ ማሳለጫው [ድሬይኔጅ ሲስተም] እንዲስተካከልም ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ጥራት አለው ብለን የምንለው የባሕር ዳር ስታድየም መልበሻ ክፍልም ፈርሶ እንደ አዲስ መሠራት አለበት የሚል ግብረ መልስ ሰጥቷል።"
በቅርብ ጊዜ ከተሠሩና የተሻለ የምንለው የባሕር ዳር ስታድየም ይህን ካላሟላ ሌሎቹስ የሚል ጥያቄ ያነሳል ፍሬው።
የኢትዮጵያ ስታድየሞች የማን ናቸው?
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስታድየሞችን የመገንባትም ሆነ የማስተዳደር ኃላፊነት የለብኝም ይላል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ ባሕሩ ጥላሁን በየትኛውም አገር የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ስታድየም የመገንባትም ሆነ የማስተዳደር ሥልጣን የለውም ይላሉ።
"የእኛ ሥልጣን እግር ኳስን ማስፋፋት እንጂ መሠረተ ልማት መገንባት አይደለም። ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታት ናቸው።"
ዋና ፀሐፊው "ይህ ማለት ግን ፌዴሬሽኑ 'ቴክኒካል' ድጋፍ አይሰጥም ማለት አይደለም" ይላሉ።
"በዚህ ሥራ የተካኑ ባለሙያዎችን ከመንግሥት ጋር ማገናኘት፤ ኤክስፐርቶችን የማቅረብ ሥራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሊሆን ይችላል።"
አቶ ባሕሩ "እንደውም በፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ጥረት ነው ለበርካታ ጊዜያት ስታድየሞቻችን ሳይታገዱ የሰነበቱት" ይላሉ።
"ለበርካታ ጊዜያት ጨዋታዎችን በባሕር ዳር ስናደርግ የነበረው በገደብ ነበር። ይህ የእግር ኳስ ዲፕሎማሲው ውጤት ነው። አቶ ኢሳያሳ ጅራ [የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት] ያለንበትን ሁኔታ ለካፍ እያስረዱ ነው ይህ ሲሆን የቆየው፤ እንጂ ሙሉ በሙሉ ስታድየሞቻችንን ለማገድ ያሰቡት የዛሬ ሁለት ዓመት ነበር።"
ዋና ፀሐፊው ካፍ በየጊዜው የሚልክላቸውን ደብዳቤዎች ለአማራ ክልልና ለስፖርት ኮሚሽን በማቅረብ መፍትሔ ለማበጀት ይሠሩ እንደነበር ያወሳሉ።
"ምንም እንኳ የተወሰነ መሻሻል ብናሳይም ካፍ በሚፈልገው መልኩ ግን አልነበረም። ካፍም መሻሻል እንዳለ አምኗል፣ ነገር ግን በዚህ ደረጃ ጨዋታን ማካሄድ እንደማይችል ነው የነገረን።"
አቶ ባሕሩ ጨምረውም በሂደቱ ውስጥ መሻሻሎችን ማሳወቅና ባለሙያ ማቅረብ ነው ሲሉ የፌዴሬሽኑን ኃላፊነት ያብራራሉ።
"ለምሳሌ ግሪጎሪ ኢንተርናሽናል የተባለ አፍሪካ ውስጥ ከ20 በላይ ስታድየሞችን የገነባ ድርጅት አምጥተን ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር አገናኝተን፤ የአዲስ አበባ ስታድየም እድሳትን ተመልክቶ፤ የሚሠራበትን ዋጋ አቅርቦ ነው የሄደው።"
አቶ ባሕሩ ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጪ በመጫወቷ ዋጋ እየከፈለ ያለው ፌዴሬሽኑ ነው ይላሉ።
"ፌዴሬሽኑ ፊፋና ካፍ በሚመድቡለትና ከስፖንሰር በሚያገኘው ገቢ ነው የሚተዳደረው። ለብሔራዊ ቡድኑ ተብሎ ከመንግሥት የሚመደብለት ገንዘብ የለም።"
ዋና ፀሐፊው ብሐራዊ ቡድኑ ከማላዊ ቀጥሎ ከግብፅ ጋር ያለውን ጨዋታ በማላዊ ስታድዬም ለማድረግ የወሰነው ከወጪ አኳያ እንደሆነ ይገልጣሉ።
"ባለፈው በጋና ጨዋታ ተመልክተናል። አሁንም ደግሞ ማላዊ ላይ ግብፅን ለመግጠም አስበናል። ማላዊን የመረጥነው ወጪ ለመቀነስ በማሰብ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ተጫዋቾቻችን ከአገር አገር በመመላለስ እንዳይዳከሙ በማሰብ ነው። ታድያ ይህ የሚያሳፍር እንጂ ደረት የሚያስነፋ አይለም።"
"አሁን የምንቀሳቀስበት ገንዘብ ስላገኘን እየተሳተፍን ሊሆን ይችላል። ነገሩ እየከበደን ሲሄድ ግን ውድድር እስከማቋረጥ ልንደርስ እንችላለን። ይህ ደግሞ እንደአገር ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ነገር ግን ይህን ለማስወገድ ከባሕልና ስፖርት ጋር እየሠራን ነው።"
ያለው ተስፋ ምንድነው?
ፍሬውም ከዋና ፀሐፊው ሐሳብ ጋር ይስማማል። ስታድየም ገንብቶ ማጠናቀቅና ማስተዳደር ያለበት የፌዴራል መንግሥት አሊያም የክልል የስፖርት ቢሮዎች እንጂ የፌዴሬሽኑ አይደለም ይላል።
ለምሳሌ የአዲስ አበባ ስታድየም የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ንብረት ነው። የሚቆጣጠረውም ኮሚሽኑ ነው ይላል።
"ቢሆንም ግን የሚጠቀምበት ስታድዬም እስከሆነ ድረስ ስታድየሞቻችን ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ጫና የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት አምናለሁ።"
ምንም እንኳን ስታዲየሞቻችን ከካፍ ዝቅተኛው መመዘኛ በታች ቢሆኑም አሁን እድሳት ላይ ያለው የአዲስ አበባ ስታድየምና የአደይ አበባ ስታድየም ግንባት የተስፋ ስንቅ እንደሚሆኑ ፍሬው ይናገራል።
የድሬዳዋና የባሕር ዳር ስታድየሞችም የካፍ መመዘኛን ባሟላ መልኩ ቢያንስ በዚህ ዓመት ሊጠናቀቁ እንደሚችሉ ፍሬው ይጠቁማል።
"ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሆ ብሎ ስታድየሞችን በአንድ ጊዜ መጨረስ የሚከብድ ይመስለኛል" የሚለው ፍሬው አሁን የስፖርት ሚኒስቴር እያደረገ ያለው የተጀመሩ ስታድየሞችን በደረጃ የማጠናቀቅ እርምጃ አዋጭ እንደሆነ ያብራራል።
"እንደውም ቢርቅ በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ዋሊያዎቹ በሜዳቸው ሲጫወቱ ልናይ እንችል ይሆናል።"













