በባዕድ አገር እንግዳ ሆኖ እንግዶቹን 'ለማስተናገድ' የተገደደው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

የፊፋን መመዘኛ የሚያሟሉ የሚባሉ ስታዲየሞች በአገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች ተገነቡ፣ እየተገነቡ ነው ሲባል ተደጋግሞ ተሰምቷል።
ስታዲየሞች በባሕርዳር፣ ነቀምቴ፣ ወልዲያ፣ አዲስ አበባ፣ ሐዋሳ እና ሌሎች አካባቢዎችም ባለፉት ዓመታት ተገንብተዋል። እየተገነቡም ነው።
ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተጠናቀቀው የወልዲያው ሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲን ስታዲየም ነው። አንዳንዶቹ ጨዋታ ማስተናገድ ቢጀምሩም በተለያየ የግንባታ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ።
አዲስ አበባ ስታዲየም ከሰባት አስርታት በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል።
ስታዲየሙ በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥቅምት 23 ቀን 1940 ዓ.ም የመሠረተ ድንጋይ የተጣለለትና እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ "ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም" ይባል ነበር። ከደርግ መንግሥት መምጣት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም ተቀይሯል።
የስታዲየሙ ግንባታ በመዘግየቱ ምክንያት በ1953 ሊደረግ የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ በአንድ ዓመት ለመራዘሙ አንድ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
ዕድሜ ጠገቡ ስታዲየም ሦስት የአፍሪካ ዋንጫዎችን (3ኛ፣ 6ኛ እና 10ኛውን) ጨምሮ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናን አስተናገዷል።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ባስተናገደችው ሦስኛው የአፍሪካ ዋንጫ ስታዲየሙ ያለ መብራት የአህጉሪቱን ትልቁን የፍጻሜ ጨዋታ ተከናውኖበታል። ለምሽት ጨዋታዎች የሚያገለግለው መብራት የተተከለለት በ1959 ዓ.ም ነው።
በነገራችን ላይ የሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኢትዮጵያ ነበረች። ብቸኛው የውድድሩ ዋንጫዋም ነው።
ከዚህ በብቸኝነት ስፖርታዊ ውድድሮች በተጨማሪ ሐይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ እና የሙዚቃ ድግሶችን ሲያስተናግድ ከቆየው ስታዲየም በኋላ ሌሎችም መገንባት ቀጠሉ።
አዳዲሶቹ ስታዲየሞች ምን ገጠማቸው?
በተለይ በቅርብ ዓመታት የሚሠሩት ሲጀመሩ 'የፊፋን እና/ወይም የካፍን መመዘኛ የሚያሟሉ' ተብለው ነው። የኋላ ኋላ ግን እንቅፋት እየገጠማቸው ነው።
በተባለላቸው ጊዜ አይጠናቀቁም። ሲጠናቀቁም አነስተኛውን መመዘኛ አያሟሉም ይባላል። ቀጥሎ ውድድር እንዳያዘጋጁ ከካፍ እና ከፊፋ እገዳ ይጣልባቸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተገንብተው 'የካፍ መመዘኛ የሚያሟሉ' ተባሉትን ስታዲየሞች በመተማመን የቻን 2020 የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ አቅርባ ዕድሉ ተሰጥቷት ነበር።
ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማስተናገድ ስትመረጥ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ኢእፌ) ውድድሩን አዘጋጅበታለሁ ብሎ አምስት ስታዲሞችን መርጦ ነበር።
ነገር ግን ካፍ ገምጋሚ ቡድን በመላክ የአዲስ አበባ፣ የመቀለ፣ የሐዋሳ፣ የባሕር ዳር እና የድሬዳዋ ስታዲየሞቹን ከተመለከቱ በኋላ ውድድሩን ለማዘጋጀት ብቁ አይደሉም ብሎ በመወሰኑ፣ ጨዋታው ከኢትዮጵያ ተነጥቆ ካሜሮን እንድታዘጋጀው ተወሰነ።
አንዳንድ ሁኔታዎችን በማጤን ውድድሮች እንዲካሄዱበት ፈቃድ ተሰጥቶት የነበረውን የአዲስ አበባ ስታዲምም በተመሳሳይ እገዳ ተጥሎበታል።
የአዲስ አበባ ስታዲየም ሙሉ እድሳት ካልተደረገለት ምንም ዓይነት የካፍ ጨዋታዋችን እንዳያስተናግድ ነው የተባለው።
ከእገዳው በተጨማሪ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች በአስቸኳይ የማይሻሻሉ ከሆነ በካፍ የተመዘገቡ ሁሉም ጨዋታዎች ወደ ጎረቤት አገር እንደሚዘዋወሩም አስታውቆ ነበር።
ማስጠንቀቂያውን ተከትሎ የስታዲየሞቹን ደረጃ የማሻሻል ሥራዎችን ተጀመሩ። በዚህም የባሕርዳርና የመቀለ ስታዲየሞችን ቀሪ ሥራም መከናወን ቀጠለ።
በተለያዩ ጊዜያት ካፍ ከሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ጎን ለጎን ጊዜያዊ ፈቃድ በመስጠት የባሕር ዳር እና መቀለ ስታዲየሞች እንዲሠሩ ፈቀደ።
ፈቃዱም በተለያየ ጊዜ ሲታደስ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ በአህጉር ደረጃ የሚወዳደሩ የአገሪቱ ክለቦች በእነዚህ ሜዳዎች ላይ ጨዋታዎችን ሲያደርጉ ነበር።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭት በእግር ኳሱም ላይ ጥላውን አሳርፎ፣ የትግራይ ክልል ክለቦች ከሊጉ ውድድር ውጭ ሆኑ።
ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኒጀር ጋር ኅዳር 2013 የመልስ ጨዋታ ባሕር ዳር እንደሚካሄድ ተወስኖ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ላይ ነበር።
በወቅቱ የባሕር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰበትን ጥቃት ተከትሎ ለተወሰኑ ቀናት ሥራ በማቆሙ ጨዋታው የሚደረግበት ስታዲየም እንዲቀየር ሆነ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጠየቀው መሠረት ካፍ ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታዲየም በዝግ እንዲካሄድ ወሰነ። ይህም ጨዋታ ከረዥም ጊዜ በኋላ በአዲስ አበባ የተካሄደ የመጀመሪያው የካፍ ጨዋታ ለመሆን በቃ።
አውሮፕላን ማረፊያው ሥራ ሲጀምር ሁሉም ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የክለቦች እና የብሔራዊ ቡድን ውድድሮች በባሕር ዳር ስታዲየም መካሄዳቸው ቀጠሉ።
ባሕር ዳር ስታዲየምም ብዙ አልተጓዘም።
የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር የባሕር ዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳያስተናግድ በማገዱ አገሪቱ መሰል ውድድሮችን ማስተናገድ እንደማትችል ተረጋገጠ።
የብሔራዊ ቡድን ውድድሮችን ላለፉት ዓመታት ሲያስተናግድ የቆየው የባሕር ዳር ስታዲየም የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን እና የአፍሪካ የክለብ ሻምፒዮና ውድድሮች እንዳይካሄድበት ማገዱን ካፍ ያስታወቀው ሰኞ ነው።
የባሕር ዳር ስታዲየም የጨዋታ ሜዳው እና ለጨዋታ ሜዳው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ባለማማላቱ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የቡድኖች እና የጨዋታ አመራሮች ማረፊያ ክፍሎች ስለሌሉት እና የህክምና ክፍሉ የተሟላ ባለመሆኑ እግድ ተጥሎበታል።
በተጨማሪም የተመልካቾች መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ፣ የክብር እንግዶች መቀመጫ እና የመስተንግዶ አካባቢ በበቂ ደረጃ ባለመዘጋጀቱ፣ በስታዲየሙ ደረጃውን የጠበቀ የመገናኛ ብዙኃን ማዕከል አለመኖር እንዲሁም የልምምድ ሜዳው በዝቅተኛ ደረጃ በመያዙ ለመታገድ እንዳበቃው ተጠቅሷል።

የፎቶው ባለመብት, Weldya communication
ክልሉ ምን አለ?
በአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባንተ አምላክ ሙላት ክልሉ በተቻለው አቅም ለሦስት ዓመት ከተለያዩ በጀቶች በመቀነስ ስታዲየሙን ሲያሟላ መቆየቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአጭር ጊዜ ማሟላት የሚችለውን አሟልተው ጨዋታዎች መካሄድ መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል።
"በ2013 በጀት ዓመት ክልሉ ያለበት ይታወቃል። ከአንድ ሚሊየን በላይ ሕዝብ የተፈናቀለበት እና የህልውና ዘመቻ ውስጥ በመሆናችን በጀቱ ወደዚያ በመመደቡ ክልሉ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ በጀት ይመደበልን ብሏል" ሲሉ ተናግረዋል።
ካለው የበጀት እጥረት በተጨማሪ አቶ ባንተ አምላክ በካፍ ግምገማ አካሄድ ላይም ደስተኛ አይመስሉም።
"የካፍ ኢንስፔክሽን ቡድን ከጉብኝቱ በኋላ የሰጡን ሃሳብ እና አገራቸው ሆነው የላኩት አስተያት የተለያዩ ናቸው። በእኛ በኩል የካፍ እና ፊፋ ዝቅተኛ መመዘኛ መሟላት አለበት የሚለውን እናምናለን። አሁን የቀረበው ግን ከዚህ በፊት ያልተካተቱ ሃሳቦችን የያዘ ነው" ብለዋል።
ለዚህም እንደማሳያ ቀደም ሲል ሙሉ መልበሻ አራት ክፍሎች አዘጋጁ ተብሎ ቢዘጋጅም አሁን እሱን ጭምር ቀይሩ መባሉን ጠቅሰዋል።
የመኪና መቆሚያን በተመለከተም "ስታዲየሙ ሲጠናቀቅ ጀምሮ አብሮ የተጠናቀቀ እና በሺህዎች የሚቆጠሩ መኪናዎቸው የሚያቆም በቂ ቦታ አለው። ይህ አስተያት ትክክል አይደለም። አንቀብልም" ብለዋል።
"የስታዲየሙ ሁለት መለማመጃ እና ዋናው ሳር ከዚህ በፊት ምንም አስተያየት አልተሰጠውም። ያ ማለት ጥሩ ሳር ነው ማለት ነው። ይህን የሚከታተል ድርጅትም ውል ይዞ ይከታተለዋል። እዚህ ሜዳ ላይ ብዙ ውድድር መካሄዱ አይካድም። በዚህ ምክንያት ሳሩ የተወሰ መጎዳት እንጂ የሚያስቀይረው አይደለም" ሲሉ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
በገምጋሚ ቡድኑ ቀደም ሲል የተሰጠው አስተያየት ሳሩ መጎዳት እንጂ እንዲቀየር የሚል እንዳልሆነ አቶ ባንተአምላክ አስታውሰው "ሙሉ ለሙሉ የአውሮፓ ዘር አምጥታቸውሁ ትከሉ ነው ያሉት። በአገር ደረጃ ይህ ሊሆን አይችልም። ከዚህ ውጭ ያሉት በተባለው ጊዜ አልተሟላም። ይህም በበጀት እና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
እንደዚህም ሆኖ ከዚህ በፊት የተሰጡ አስተያቶች ላይ ምላሽ ለመስጠት እየሠሩ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ባንተ አምላክ ጠቁመዋል።
"በዚህም መሠረት ካፍ ከሰጠን የማሟላት ሥራዎች ከ70 በመቶ በላይ ሥራ ተጀምሯል እስከ በአራት ወር ውስጥ ይጠናቀቃል። የተጎዱት ሳሮችም ተከላ ተምሯል። ሳሩን በአደዲስ የማስተካከል ሥራ እየተሠራ ነው። በእኛ አቅም መሠራት ያለበትን ሥራ እንሠራለን" ያሉት ዳይሬክተሩ ሌሎች ሥራዎችም ደግሞ የስታዲየሙ የጣሪያው ሥራ ሲሠራ አብሮ የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን ጨምሮ ሁሉንም ሥራዎች ለማጠናቀቅ ከፌደራል መንግሥት የተጠየቀው ሁለት ቢሊዮን ብር ከተገኘ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ብለዋል።
"በካፍ አስተያት መሰጠቱ መልካም ነው። ጦርነት እና ኮቪድ ባለበት እና ሌሎች አሸዋ ላይ እየተጫወቱ ስታዲየሙ መታገዱ ተገቢ አይደለም። የተለያየ የአስተያየት መስጠትም ተገቢ አይደለም" ብለው መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲይደርግም ጠይቀዋል።
ፌደሬሽኑስ ምን አለ?
ካፍን ውሳኔ ብዙ ጊዜ ሲፈሩት የነበረው መሆኑን ጠቅሰው "እንደማይቀር የምናውቀው ውሳኔ ነው የተወሰነው" ያሉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ናቸው።
ፌደሬሽኑ ስታዲየም እንደማይሠራ እና እንደማያስተዳደር ያስታወቁት አቶ ባሕሩ ጥላሁን ፌደሬሽኑ በተለያየ ጊዜ ስለ ስታዲየሞቹ ከካፍ የሚደርሱትን መረጃዎች ለሚመለከታቸው አካላት ሲያስተላልፍ መቆየቱን አስታውቀዋል።
"ጫናዎችን በተለያየ መንገድ ለማድረግ ሞክረናል። . . . ፌደሬሽኑ ከዚህ በላይ ማድረግ አይችልም። የራሱ ሜዳ ስለሌለው ማሳወቅ የሚገባንን አሳውቀናል። ከካፍ ጋር ደግሞ አንገት ለአንገት ተናንቀን ከዚህ በፊት እንዳንቀጣ ለማድረግ ብዙ ጊዜ ሞክረናል አሁን ግን ጠንከር አድርጎ በመሄዱ ተወስኗል" ብለዋል።
ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎችም በካፍ በኩል ስለመነሳታቸው የተጠየቁት አቶ ባሕሩ የባሕር ዳር ስታዲየም መልበሻ ክፍል የተሟላ ቢሆንም "ካፍ የሚጠይቀው የተሟላ ብቻ ሳይሆን ምችቾት ያላቸው የመልበሻ ክፍሎችን ነው። እንደዚህ አይነት ጥያቄ የሚጠይቅ ቢሆንም አብዛኛውን ሃሳብ እንቀበላለን። ስታዲየሙ ላይ ያሉ ክፍተቶች ናቸው ብለን እንወስዳለን" ይላሉ።
የካፍን ደረጃ የሚያሟላ ስታዲየም እንዲኖር በሚሰጠው ትኩረት እና በጀት ላይ ይወሰናል ያሉት ዋና ጸሐፊው በዚህ ረገድ ከተሠራ "ከሰባት እስከ ስምንት ወሮች" ባለው ጊዜ ማጠናቀቅ ይቻላል ሲሉም ገልጸዋል።
"አደይ አበባ ስታዲየም ካፍን ደረጃ የሚያሟላ ነው። አደይ አበባ ስታዲም ሁለት እና ሦስት ዓመት ይፈልጋል። አዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ላይ ነው። በቶሎ የሚጠናቀቅ ከሆነ ትልቅ ዕድል ይሆናል።"
ለዚህ ደግሞ የክልሎችን ጨምሮ የፌደራል መንግሥት ጋራ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።
እስከዚያ ግን የወንዶች ብሔራዊ ቡድን እና በአህጉር አቀፍ ደረጃ የሚካፈሉ ቡድኖች በሌላ አገር የሚጫወቱ ይሆናል።
በቀጣይ ብሔራዊ ቡድኑ የት ይጫወታል ተብሎ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ለኬንያ፣ ለዚምባብዌ እና ለደቡብ አፍሪካ ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል። ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ፈቃድ ሰጥተዋል። ቢዘገይም በተመሳሳይ ዚምባብዌ ጥያቄውን ተቀብላለች።
"ፌደሬሽኑ ሌላ ገቢ የለውም። ከአገር ውጪ መጫወቱም ሌላ ወጪ እንዲያወጣ ያደርገዋል። በካፍ እና በፊፋ ድጋፍ ላለ ፌደሬሽን እና ለቡድኑ ሥነልቦናም ጥሩ አይደለም። እንደ አገርም ስታዲም የለንም ብለን ወደ ሌላ አገር መሄድም የራሱ ተጽእኖ ይኖረዋል" ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ 7 ተደልድሎ ነበር። የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ባይጠናቀቁም ቡድኑ ከወዲሁ ለዓለም ዋንጫው እንደማያልፍ ተረጋግጧል።
በቀጣይ ከጋና እና ከዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ቀሪዎቹን የምድብ ጨዋታዎች ያከናውናል።
በዚህም ፌደሬሽኑ ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኦርላንዶ ስታዲየም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጋና አቻው ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ እንደያስተናግድ መርጦታል።
እንደ ፌደሬሽኑ ከሆነ ደቡብ አፍሪካ የተመረጠችው የመጨረሻ ጨዋታው ዚምባቡዌ ሐራሬ ላይ ስለሆነ የጉዞ እና ተያያዥ ወጪዎችን ለመቀነስ ነው።













