ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ማስተናገድ የሚያስችል የተሟላ ስታዲየም የላትም ተባለ

የባህር ዳር ስታዲየም
የምስሉ መግለጫ, የባህር ዳር ስታዲየም

የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር (ካፍ) የባሕር ዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳያስተናግድ ማገዱን ተከትሎ አገሪቱ መሰል ውድድሮችን ማስተናገድ እንደማትችል ተረጋግጧል።

የብሔራዊ ቡድን ውድድሮችን ላለፉት ዓመታት ሲያስተናግድ የቆየው የባሕር ዳር ስታዲየም የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እና የአፍሪካ የክለብ ሻምፒዮና ውድድሮች እንዳይካሄድበት ማገዱን ካፍ አስታውቋ።

ካፍ ይህን ውሳኔውን ያስታወቀው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው ደብዳቤ ነው።

የባሕር ዳር ስታዲየም የካፍ የስታዲየሞች መመዘኛ መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ ባለማሟላቱ በገደብ ውድድሮችን ሲያስተናግድ መቆየቱ ይታወሳል።

ካፍ ከሳምንታት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በየትኛው አገር እና ስታዲየም ለመጫወት እንደምትመርጥ ኢትዮጵያ ከጥቅምት 10 በፊት በአስቸኳይ እንድታሳውቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ይህ ማድረግ ካልተቻለ ካፍ ጨዋታውን ወደ ተጋጣሚዋ አገር ጋና እንደሚወስድ አሳውቋል።

የባሕር ዳር ስታዲየም የጨዋታ ሜዳው እና ለጨዋታ ሜዳው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ባለሟሟላቱ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የቡድኖች እና የጨዋታ አመራሮች ማረፊያ ክፍሎች ስለሌሉ እንዲሁም የህክምና ክፍሉ የተሟላ ባለመሆኑ ውድድር እንዳይካሄድበት የታዘዘው።

በተጨማሪም የተመልካቾች መሠረተ ልማት ባለመሟላታቸው፣ የክብር እንግዶች መቀመጫ እና የመስተንግዶ አካባቢ በበቂ ደረጃ ባለመዘጋጀቱ፣ በስታዲየሙ ደረጃውን የጠበቀ የመገናኛ ብዙኃን ማዕከል አለመኖር እና የልምምድ ሜዳው ዝቅተኛ ደረጃ በመያዙ ለመታገድ በቅቷል።

የካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ ኃላፊ መሐመድ ሲዳት በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው የተለያዩ ስታዲየሞችን ገምግመዋል ተብሏል።

ኃላፊው በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከባሕር ዳር ስታዲየም በተጨማሪ የአበበ ቢቂላ እና የጅማ ዩንቨርሲቲ ስታዲየሞችን ተመልክተዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በርካታ ማሟላት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉት ገልጸው ስታዲየሙ የተጓደሉትን ነገሮች ካሟላ ወደፊት የገምጋሚ ቡድን እንደሚልኩ አስታውቀዋል።

ስታዲየሙ አሁን ባለው ሁኔታ ምንም አይነት ዓለም አቀፍ ውድድር ማስተናገድ እንደማይችል አሳውቀዋል።

የአበበ ቢቂላ ስታዲየም በታዳጊ ደረጃ የሚዘጋጁ ውድድሮችን እና የሴት የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በጊዜያዊነት ማስተናገድ እንደሚችል ገልጸዋል።

የሐዋሳ ዩንቨርሲቲ ስታዲየምን በተመለከተ መጫወቻ ሳሩ ደረጃውን ያልጠበቀ፣ ሜዳው አጠገብ ያለው መሮጫም መስተካከል እንዳለበት የገለጹ ሲሆን መልበሻ ክፍሎቹ በአዲስ መልክ ሊሻሻሉ እንደሚገባቸው አስታውቀዋል።