ተክሌ አበራ፡ ዓይነ ስውሩ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የዘመናት ደጋፊ

የፎቶው ባለመብት, Fekadu Abebe /Natanim/
ካምቦሎጆና እና ተክሌ ከተዋወቁ አስርት ዓመታት ነጉደዋል። ከ1968 ጀምሮ የካምቦሎጆን መግቢያ መውጫውን አብጠርጥሮ ያውቀዋል።
"ያኔ በደርግ ዘመን 68 አካባቢ ነው። 50 ክለቦች ነበሩ። ሁሉንም ክለቦች እመለከት ነበር። የራሴ የሆነ የማውቀው ቡድን አልነበረኝም። ከኤርትራም የሚመጡ ቡድኖች ነበሩ። አዲስ አበባ በሚጫወቱበት ወቅት እመለከት ነበር" ሲል ያስታውሳል።
ያኔ 'ቡንዬ' አልነበረም።
ከፍተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ "እነ ጥጥ የድሬዎቹ፣ አዱሊስ የአሥመራዎቹ እነ አብዮት ፍሬ፣ ትግል ፍሬ በደርግ ዘመነ መንግሥት ናቸው የነበሩት" እንጂ ቡና የዚያን ጊዜ አልነበረም።
"ቡና በ19 77 ነው የተቀላቀለው። ማንም አያውቀውም የሠራተኛ ማኅበር ነው የነበረው።"
በወቅቱ የ50 ክለቦች ውድድር ይካሄድ ነበር።
ቡና እና ተክሌ አበራም የተዋወቁት የዚያን ጊዜ ነው። አጋጣሚውን ተክሌ አይረሳውም።
"ቡና ከአደይ አበባ ጋር ሲጫወት ተመለከትኩት። ውድድሩ በጣም ከባድ ነበር። [ቡና] የላቀ ቡድን ሆነብኝ። ምክንያቱም በጣም በራሱ የሚተማመን በሳል አሰልጣኝ ነበረው። ከነበሩት ቡድኖች የማረከኝ ቡና ብቻ ሆነ። በዚህ መልኩ ነው ቡናን የተዋወቅኩት" ይላል።
የእግር ኳስ ፍቅር ከቡና ጋር ተጀመረ።
በሠላማዊው ውጊያ በፍልሚያው ስፍራ
የቡና ፍቅር ስንቱን "ብዙ ሊገለጽ የማይችል" የሚለውን አጋጣሚ አጋፈጠው።
"የታሰርኩበት ጊዜ አለ። ብዙ መከራ እና ውጣ ውረድ የገመኝ ጊዜ አለ። ከስታዲም የታገድኩበትም ጊዜ ነበረ። ብዙ የራሴ የሆነ ነገር ያጣሁበት ጊዜ አለ። ቡናን በማየቴ የሥራ ዘመኔን ያባከንኩበት ጊዜ አለ። ብዙ የገጠሙኝ ነገሮች አሉ ሊቆጠሩ የማይችሉ መሰናክሎች አጋጥመውኛል" ይላል የኋሊት እያስታወሰ።
ስታዲም እንዳይገባ ከተደረገበት እንጀምር
በወቅቱ ወፖ (ወታደራዊ ፖሊስ) የሚባሉ ወታደሮች ነበሩ በስታዲየሙ ጨዋታ ሲኖር የሚጠብቁት።
ተደባዳቢ ነው በሚል ወደ ስታዲየም ዝር እንዳትል ተባልኩ። 'በቡና የተነሳ ከሰው ጋር ይደባደባል ብለው ነው' ላለማስጋባት የወሰኑት።
"ቡናን ስለምወድ በማስጨፍረበት ሰዓት ይቃወሙኝ ነበር" ይላል።
አንድ ቀን ወፖዎች ይዘውት ወደ ለገሃር አቀኑ። ለገሃር የማይሠሩ አሮጌ ባቡሮች ነበሩ። አንዱ ውስጥ የቆልፈውበት ይሄዳሉ። ረሱት።
ከቤትም የት ገባ? የት ጠፋ? የሚለው አጥቶ የት እንዳለ ሳይታወቅ ቆየ። ከእስሩ በላይ ረሃቡን አልቻለውም።
"በጣም ርቦኝ ስጮህ በመኪና የሚያልፉ ሰዎች መጥተው አስወጥተውኛል" ይላል።
ከእስር ቢወጣም ስታዲየም እንዳይገባ የተጣለበት እገዳ ግን አልተነሳም። ይህም ግን ኳስ ከመመልከት አላገደውም። ሌላ ዘዴ ይዞ ብቅ አለ።
"እነሱ አግደውኛል እንጂ እኔ በኤሌክትሪክ ገመድ ተስቤ ተደብቄም እግባ ነበር። በባሕር ዛፍ ላይ ተንጠላጥዬም፣ በገመድም ተስቤ እገባ ነበር" የሚለው ተክሌ በዚህ ምክንያት "ጨዋታ አያመልጠኝም ነበር" ይላል።
በድጋሚ ደግሞ አሁንም ታሰረ።
ይኼኛው ደግሞ በሌላ ምክንያት ነው።
"አንድ ጓደኛ አለኝ። አብደላ አህመድ ይባላል። ካታንጋ ሆነን ስንጨፍር የምድር ጦር ደጋፊዎች ዝም ብለው መጡ እና ሁለታችን ላይ ሽጉጥ አወጡ። ሽጉጥ ሲያወጡ አብሮኝ የነበረው በጣም ደንግጧል እና እንዳልነበረ ሆነ። እኔ ደሞ 'ምንድነው? በሰላም አገር ላይ ሽጉጥ ምን ያስፈልጋል መብታችን እኮ ነው። የማንንም መብት አልነካንም። ተኩስ ተኩስ' አልኩንና ሳፈጥበት ይዘውኝ ሄዱ እና ቆለፉብኝ" ይላል አጋጣሚውን እያስታወሰ።
"ሦስት ቀናትን በእስር አሳለፍኩ። ከፍተኛ ዱላም ቀምሻለሁ። እዚያ ካስገቡን በኋላ በጣም ጎድተውኛል።"
የቡና ደጋፊ ሆኖ ብዙ አሳልፏል። "በበኩሌ ሊቆጠር የማይችል ብዙ እንግልት ነው የደሰረሰብኝ" የሚለውም በምክንያት ነው። ለቡና የነበረው ፍቅር ግን እያበበ ሄደ። በዚህ መልኩ የተክሌ እና የቡና ፍቅር ዘለቀ።
የቡና ውጤት ከፍም ዝቅም ሲል ተክሌ አለ።
ቡና በዚህ ሁሉ አልፎ በታሪኩ የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫ ሲያነሳ እማኝ ለመሆንም በቅቷል።

የፎቶው ባለመብት, Fekadu Abebe /Natanim/
ለውብ ጨዋታ ቡና
ለኳስ እርካታ ቡና
ኢትዮጵያ ቡና የኛ የኛ . . .
በ2005 ተክሌ ህይወት እስከ ወዲያኛው ተቀየረ። የመኪና አደጋ አጋጠመው።
"2005 ላይ የመኪና አደጋ አጋጠመኝ። በቅርብ ነው 10 ዓመት አልሞላኝም። ዘጠኝ ዓመት ከምናምን ነው። የመኪና አደጋ አጋጥሞኝ የዓይን ብርሃኔን አጣሁ።"
ከደረሰበት አደጋ ለመዳን ሙከራ ቢያደርግም የሚሳካ አልሆነም።
"በወቅቱ እድናለሁ ብዬ ምኒልክ [ሆስፒታል] ሄድኩኝ። ሐኪሞቹ የሁለቱም የዓይኖቼ ብሌኖች እንደሌሉ ተናገሩ።"
አንድ አውራ ጣቱም በአደጋው ስብራት ደረሰበት።
"ከዚያ በኋላ ደግሞ ማገገም አልቻሉኩም" የሚለው ተክሌ ". . . አቅም አልነበረኝም። ይህን አደጋ መቋቋም አልቻልኩም። ተጎዳሁ፣ ብርሃኔን አጣሁ፣ አልጋ ያዝኩኝ" ሲል ሁኔታውን ይገልጻል።
አስፈላጊውን ህክምና ተከታትሎ አጠናቀቀ።
ማየት ባይችልም ድጋሚ ጉዞ ወደ ካምቦሎጆ ተጀመረ።
አደጋው ደርሶበት ህክምናውን ከተከታተለ በኋላ ምንም ጨዋታ እንዳላመለጠው በተደጋጋሚ ይናገራል።
"እኔ አደጋው ከደረሰብኝ በኋላም አቋርጬ አላውቅም። [ስታዲየም] እሄዳለሁ" ይላል ተክሌ።
ዋናው ጥያቄ ይሄኔ ይነሳል። እንዴት ጨዋታውን ይከታተላል? የሚለው።
"ጨዋታውን አነበዋለሁ። እንቅስቃሴውን በደንብ አውቀዋለሁ። ምክንያቱም በማጥቃት ከኋላ ጀምሬ የቡድኑን እንቅስቃሴ በደንብ አውቀዋለሁ። አካሄዱን በደንብ እረዳዋለሁ። በማጥቃት በኳሱ ፍጥነት አውቀዋለሁ።"
በደንብ እንዲያስረዳን ድጋሚ ጨዋታውን እንዴት እንደሚከታተል እና ስለ ጨዋታው ሂደት የሚነግረው ሰው ስለመኖሩ ጠየቅነው።
"እኔ ከሰው ጋር [ስታዲየም] አልገባም። አንድ ህጻን ልጅ አለኝ አልፎ አልፎ ትምህርት ከሌለው እሱን ይዤው እገባለሁ። እሱም ኳስ ይወዳል። በጣም በጣም የቡና ደጋፊ ነው። እኔ በራሴ እመለከታለሁ። ልጄ አጠገቤ ካለ ልጄ ይረዳኛል። ልጄም [ስለ ኳስ] ያውቃል። እሱም ከእኔ የበለጠ ስሜታዊ ነው። 14 ዓመቱ ነው። እንደ ልጅነቱም ሳይሆን ጨዋታ በደንብ ገምግሞ ያውቃል።"
ብዙ አገራት ለአካል ጉዳተኛ ደጋፊዎች የሚመቹ ስታዲየሞችን እና አሠራሮችን ዘርግተዋል። ሰዎችም ተባባሪ ናቸው። በኢትዮጵያ ግን ከዚህ እንደሚለይ ተክሌ ይገልጻል።
"ካምቦሎጆ በምትገባበት ጊዜ አንዳንዶች ሊረዱህ ቀርቶ በመግባትህ የሚገረሙ አሉ። አሁን ኑሮ ውድ ነው። [የስታዲየም] መግቢያ ውድ ነው። አንድ ብር ሳይከፍልልህ መግባትህ የሚደንቀው ሰው አለ። ለወሬ የሚሞት ሰው አለ" ይላል ተክሌ።
ይህ ግን የሁሉም መገለጫ አይደለም። በቅርቡ እንኳን የዓመት ቲኬት ገዝተው የሰጡት ሰዎች መኖራቸውን ይናገራል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የገጠመውን እንደሚከተለው አጫውቶናል።
አንድ ጊዜ የዓመት ቲኬት ይዞ ከልጁ ጋር ካምቦሎጆ ይደርሳል።
ስታዲየም ሊገባ ሲል አንዱ ደጋፊ ፖሊሱን 'ለምን ታስገባዋለህ? ለምን ታስገባዋለህ? መልሰው' ይለዋል። ተክሌ ቢሰማውም እሱን አልመሰለውም ነበር።
ፖሊስ፡ ተክሌ፣ ተክሌ
ተክሌ፡ አቤት
ፖሊስ፡ ስላንተ ነው የሚያወሩኝ ግን ሂድ ግባ።
ተክሌ ሊገባ ሲል በድጋሚ ፖሊሱ 'አሁንም መልሰው እያሉኝ ነው' ይላል።
ተክሌ፡ ለምን? ምን አድርጌው ነው የሚመልሰኝ? ይከፍልልኛል? ለመንኩት? ልመና ወጣሁ? ጉዳዩ ምንድነው?
ፖሊስ፡ 'ዱላ ይዞ ስለሚገባ ሰው ሊጎዳ ይችላል' በሚል ነው አለ። 'በዱላ ስለሚሄድ ወይ ዱላውን ውሰድበት ወይ ደግሞ መልሰው' እያለ ነው።
ይህን ሲሰማ ተክሌ በጣም አዘነ። ወደ አንድ ጥግ ፖሊሱን ጠርቶ 'ይህንን ያለህን ሰውዬ ሃሳብ ትጠቀምበታለህ እንዴ?' ሲል ጠየቀው።
ፖሊሱም 'ሂድ ግባ አልኩህ እኮ። ለምን እንደዚህ አይነት ጥያቄ ትጠይቀኛለህ። ሂድ ግባ ማንም አይከለክለውም ብዬዋለሁ' ብሎ መለሰለት።
ተክሌ ጨዋታውን ሊከታተል ሜዳ ሲገባ ፖሊሱም ወደ ሥራው አቀና።

የፎቶው ባለመብት, Fekadu Abebe /Natanim/
እንደዚህ የሚያስቸግር አጋጣሚ ካለ በራዲዮ ወይም በቲቪ መከታተል አይሻልም? እነዚህ ለተክሌ ጥሩ ምርጫዎች አይደሉም።
መልሱ ደግሞ ግልጽ ነው "ይለያያል" የሚል።
"ይለያያል። . . .አንተ ያየኸውን፣ የነበርክበትንና ሰው የሚነግርህን እኩል አታራምደውም። ኖረህ እንቅስቃሴውን፣ ፍጥነቱን በማጥቃቱም በጎሉም በምኑም ያየኸውን የነበረክበትንና ሰው የሚነግርህ ልዩነት አለው" ይላል።
ለዚህም ነው በአካል ተገኝቶ ጨዋታዎቸን መመልከትን የሚያስቀድመው።
በዚህም ቡድኑ በሚለማመድበትም ሆነ ግጥሚያ ሲኖረው ቦታው ድረስ እየሄደ ይከታተላል።
ወደ ፊትም ጨዋታዎችን መከታተሉ ይቀጥላል።
"ሁሌም ስታዲየም እሄዳለሁ። ለምን ጠንካራ እና ደካማ ጎኑን ለመገምገም እና እንቅስቃሴውን ለማንበብ ነው። እኔ የቡድኑን አቋም ለማወቅ እና እንቅስቃሴውን ለማየት ነው የምሄደው። ምክንያቱም አንተ ያላማረህን ነገር አትበላም አይደል? አሰልጣኙን ለመንቀፍም ሆነ በልጆቹ ለማዘን የቡድኑን አቋም ውጤቱንም ለማወቅ በሚዲያ መስማት ይቻላል። ስለዚህ እንቅስቃሴውን ለማንበብ በቦታው መገኘት ይበልጣል።"
ተክሌ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ብዙም አይከታተልም። "ከአገሬ እኩል አላይም። እኔ ከእነሱ [እግር ኳስ] የአገሬን ነው የማስቀድመው" ይላል።
ቢሆንም የባሕር ማዶ ጨዋታዎችን አልፎ አልፎም ቢሆን እንደሚከታተል ይጠቅሳል።
የእንግሊዙ አርሴናል ደግሞ የሚመርጠው ቡድን ነው።
"የእንግሊዙ አርሴናል በሚጫወትበት ጊዜ ከእኔ ክለብ ጋር እንቅስቃሴያቸው ተመሳሳይ ነው። አርሴናል ከምወደው ቡድን [ቡናን ማለቱ ነው] ጋር እንቅስቃሴው ተመሳሳይ ነው። ሁለቱም ኳሱን ይዘው መጫወትን ይመርጣሉ። እና አልፎ አልፎ እሱን እከታተላሁ" ይላል።
ዛሬስ ልዩ ናቸው
ባርሳም ቢመጣ አይችላቸው።
ለዓመታት ካምቦሎጆ የተመላለሰው ተክሌን የትኛው ተጫዋች ቀልቡን ይይዘዋል? ማንን ያስበልጣል?
"እንደዚያ አይደለማ" ሲል ምላሹን መስጠት ይጀምራል።
"እንደዚያ አይደለም፤ ልጅ ከውደድክ ከነምናምኑ ነው የሚባል የሃበሻ ተረት አለ። ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ የራሴ ነው። ክለቤ ነው። ያደኩበት ክለቤ ነው። እዚህ የደረስኩበት ክለብ ነው። ከጀርባዬ የቆመ ክለብ ነው። በእግር ኳስ ደግሞ ውጣ ውረድ አለ። አንዳንዴ ባልጠበከው መንገድ ታገኘዋለህ። አንዳንዴ መሰናክሎች ይኖራሉ።
"ገና ገና ብዙ መንገድ ይራመዳል ብዬ ነው የምጠብቀው። ምክንያቱም የራሴ ፍላጎት ከራሴ ጋር ነው ያለው። ለምሳሌ ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ እንዲወዳደር እመኝ ነበር። ደርሶ አይቼዋለሁ ተወዳድሯል። ሁለተኛ በሊጉ አንደኛ እንዲሆን እመኝ ነበር ሆኖ አይቸዋለሁ። ዘንድሮም ገና ጅምር ነው እንጂ አላለቀም። ከአንድ እስከ ሦስት ባለው ደረጃ ውስጥ ይገባል ብዬ እገምታለሁ" ሲል ምላሹን ያጠናቅቃል።
ተክሌ ባለትዳር ነው። አራት ልጆች አሉት-ሁለት ወንድ ሁለት ሴት። ሥራ የለውም።
'የሰው እጅ ከማየት ብሎ' ከሰል ቸርችሮ በመሸጥ ነው ኑሮውን የሚገፋው።
የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኅበር አባል ነው።
"ደጋፊ ማኅበር ማለት እንደ አቅምህ የተለየያ ከፍለህ ነው የምትገባው። እኔ ድሮ ከጤናዬ ጀምሮ አባል ነኝ።"
ማኅበሩ በተለይ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ድጋፍ አድርጎለታል።
"እኔን በደንብ ያውቁኛል። ብዙዎች ያውቁኛል ምክንያቱም ብርሃን ባጣሁ ጊዜ በጣም ረድተውኛል። በታመምኩ ጊዜ ለእኔም ለልጆቼም በተለያየ ጊዜ በጣም ረድተውኛል" ብሏል።
ተክሌ ኳስ ተመልካች ብቻ አይደለም የዓይን ብርሃኑን ከማጣቱ በፊት ይጫወትም ነበር።
ሆኖም "የዓይን ብርሃኔን ካጣሁ በኋላ ሁሉንም ነገር ተውኩት" ይላል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዓይነ ስውራን የሚሳተፉበት ውድድር አለ። እንዴት ለመጫወት አልሞከርክም ብለን ገፋ አድርገን ጠየቅነው።
"አሁንማ እንዴት አድርጌ ብርሃን የለኝም ዱላ ይዤ፣ በዚያ ላይ ደግሞ ልጆች አሉ። መብራት፣ የቤት ኪራይ፣ ውሃ እና ምግብ አለ። ይሄ ሁሉ ጭንቀት እና መከራ እያለ እንዴት አድርጌ እጫወታለሁ። ለልጆቼም ዳቦ እንኳን ለመግዛት በምታገልበት ሰዓት እንዴት እጫወታለሁ?" ይላል።
ወደ ቡና ቡድኖች እንመለስ። ደጋፊዎች በተለያዩ ወቅቶች ከነበሩ የቡና ስብስብ መካከል የራሳቸውን ምርጥ ቡድን ሲሰይሙ ይታያል። ይኼኛው ቡድን ምርጥ ነበር፤ ይኼኛው ይሻለኛል እያሉ። የተክሌስ ምርጡ ቡድን የቱ ነው ?
"ከ1983 አስከ 1989፣ በ1994 እንደገና በ1995 እንዲሁም በ2003 ዓመታት የነበሩት ቡድኖች ለእኔ በጣም በጣም ምርጥ የቡና ስብስቦች ነበሩ" ሲል በአጭሩ ይመልሳል።
ተክሌ ከሰሞኑ አንኳን ቡናን ሃዋሳ ድረስ ተጉዞ ሲከታተል በቴሌቭዥን መስኮት ታይቷል።
የዘንድሮውን ቡድን በተመለከተ ሃሳቡን ሰጥቶን ቆይታችንን አጠናቀቅን።
"ቡና ሁሌም ጣፋጭ ነው። ሁሌም ልዩነት የለውም። በእግር ኳስ ዓለም ውጣ ውረድ ያለ ነው። አንድ ቡድን አንዴ ይጠነክራል አንዴ ዝቅ ይላል። ውጤት ይቀንሳል እንጂ ሁሌም ቡና ጥሩ ነው።"















