የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በሳተላይት ቴሌቪዥን መተላለፉ ምን ለውጥ አመጣ?

የኢትዯጵያ ፕሪሚዬር ሊግ

የፎቶው ባለመብት, STAFFORD ONDEGO

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ እንደ አዲስ ተዋቅሮ መካሄድ ከጀመረ ሃያ አምስተኛ የውድድር ዘመኑን ይዟል። በዲኤስ ቲቪ መተላለፍ የጀመረው ደግሞ ባለፈው የውድድር ዘመን ነው።

25ኛው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ከጥቅምት 8/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተካሂደዋል።

የሳተላይት ማሰራጫው በበርካታ የአፍሪካ አገራት ይሠራል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን ዲኤስ ቲቪ የተሰኘው የሳተላይት ማሰራጫ በሚሠራባቸው ቦታዎች ሆነው መከታተል ያስችላል።

ከዚህ ቀደም ፕሪሚዬር ሊጉ የተለያዩ እንከኖች ተስተውለውበታል። ከእነዚህም መካከል የተጫዋቾችና ደጋፊዎች ሥነ ምግባር፤ የዳኞች እና ሊጉን የሚያስተዳድረው አካል ብቃትን መጥቀስ ይቻላል።

እነዚህን እንከኖች የተሸከመው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለየ መልኩ መነቃቃት አሳይቷል።

ለዚህ ምክንያቱ የዲ ኤስ ቲቪ ሽፋን ማግኘቱ ይሆን?

ፍሬው አስራት በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሹር ኩባንያ የሕክምና መኮንን [ሜዲካል ኦፊሰር] ሆኖ ያገልግላል። አልፎም ለተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ በመፃፍ ይታወቃል።

"ያው የሐዋሳ ልጅ እንደመሆኔ በእግር ኳስ ፍቅር የወድቅኩት ሐዋሳ ከነማን ከዚያም እነ ደቡብ ፖሊስ፣ ሲዳማ ቡና እንዲሁም ሌሎች ቡድኖችን በመመልከት ነው" የሚለው ፍሬው ሊጉ ሰፊ ሽፋን በማግኘቱ ደስተኛ ነው።

"ያለፉትን 23 ዓመታት ዲኤስ ቲቪ ከመምጣቱ በፊት ያለውንና አሁን እየተመለከትነው ያለውን ብታነፃፅር ገና በሁለት ዓመት ያየነው ልዩነት የሰማይና የምድር ነው" ይላል።

"ተጫዋቾቻችን ይታያሉ"

ፍሬው ሊጉ በአህጉር አቀፍ የሳተላይት ቴሌቪዥን አማካኝነት ሽፋን ማግኘቱ ዋነኛው ጥቅሙ ተደራሽነት ቢሆንም ከዚህ የዘለለ ብዙ አዎንታዊ ጎኖች አሉት ይላል።

"ያው ኢትዮጵያዊያን ኳስ እንወዳለን። ወደ ሜዳ ስንገባ ትንሽና ትልቅ ጨዋታ አንልም። ድጋፋችን የተለየ ቀለም ያለውና ውብ ነው። ሴቶች ወደ ሜዳ ይመጣሉ፤ ሕፃናት ይገባሉ። ዲኤስ ቲቪ ይህን ማሳየት ችሏል። ሌሎች አፍሪካ አገራት 'ኢትዮጵያውያን ለካ ኳስ ይወዳሉ' እንዲሉ ያደርጋል።

"ምንም እንኳ ያለፈው ዓመት ጨዋታ በዝግ ስታድየም ቢደረግም ዘንድሮ ግን የስታድየሙ አንድ አራተኛ መያዝ የሚችለውን ያህል ተመልካች እንዲገባ መደረጉ በጣም መልካም ነው።"

ፍሬው፤ አንዱ ፕሪሚዬር ሊጉ ሽፋን ማግኘቱ ጥቅሙ ተጫዋቾች የውጭ ዕድል እንዲያገኙ ማስቻል ነው ብሏል።

"ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ከአገራቸው ውጭ አይጫወቱም ተብለው ይታማሉ። ነገር ግን አሁን ተጫዋቾች ራሳቸውን ማሳየት ስለሚችሉ የተሻለ ሊግ ያላቸው ክለቦችና ተጫዋች መልማዮች የኛን ልጆች ማየት ይችላሉ። ለምሳሌ አምና የሊጉ ከፍተኛ ግብ አግቢ የነበረው አቡበከር ናስር እንዴት በደቡበና ሰሜን አፍሪካ ሊግ ክለቦች ዓይን መግባት እንደቻለ በክረምቱ ሰምተናል።"

አምና ከፋሲል ከነማ ጋር ዋንጫ ማንሳት የቻለው ሙጂብ ቃሲም ዘንድሮ ለአልጄሪያው ጄኤስ ካቢሌ ለመጫወት ወደ አልጄርስ ማቅናቱም የሚዘነጋ አይደለም።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ ባሕሩ ጥላሁንም የቴሌቪዥን ሽፋኑ "እግር ኳሱን እንድንሸጥ ያግዘናል" ይላሉ።

"ተጫዋቾች እንዲነቃቁ ያደርጋል። እግር ኳሳችንን መከታተል የሚፈልጉ ሰዎች አሁን በቴሌቪዥን መከታተል ይችላሉ። አልፎም ተጨዋቾቻችንን አይተው ማስፈረም ለሚፈልጉ የተንቀሳቃሽ ምስል ይኖራል።"

ግብ ላይ ያረፈ ኳስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የገንዘብ ጥቅም

በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች ከዲኤስ ቲቪ 'የብሮድካስትና የታይትል ኔም' በተሰኘ ማዕቀፍ የገንዘብ ጥቅም ያገኛሉ።

ለዚህም ነው ዋና ሥራ ፀሐፊው "ክለቦቻችን ምንም ገቢ ካለማግኘት ገቢ ወደ ማግኘት ተሸጋግረዋል" የሚሉት።

ነገር ግን ከዚህም አልፎ አሁን በቴሌቪዥን መታየት መቻላቸው አቅም ያላቸው ድርጅቶች ክለቦቹን 'ስፖንሰር' [የማስታወቂያ ስምምነት] እንዲያደርጉ ምክንያት ይሆናል ይላል ፍሬው በበኩሉ።

"ዓለም አቀፍም ሆኑ አገራዊ ድርጅቶች ከክለቦች ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በመግባት አብረው መሥራት ይችላሉ። ማሊያ ላይ ድርጅታቸውን በማስታዋወቅ ሰፊ ሽፋን ሲያገኙ፤ ተያይዞ ደግሞ ክለቦች የገንዘብ ጥቅም ያገኛሉ።"

ምንም እንኳ በጣም ጥቂት ቢሆኑም የተወሰኑ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከድርጅቶች ጋር የማስታወቂያ ውል እየገቡ መሆኑን መስማት ጀምረናል።

ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ቡና የስፖርት ውርርድ ኩባንያ ከሆነው ቤቲካ ጋር የአምስት ዓመታት 'የስፖንሰርሺፕ' ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።

ፍሬው "ክለቦች በቴሌቪዥን መታየታቸው የአጨዋወት ስታይላቸውንና የክለብ አደረጃጀታቸውን ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ ለማሳደግ ጥረት እንዲያደርጉ ይገፋፋል" ብሎ ያምናል።

የሳተላይት ማሰራጫ ጣቢያው በተለያዩ ጊዜያት ለአሠልጣኞችና ለምክትሎቻቸው እንዲሁም ለዳኞች የተለያዩ ሥልጠናዎች በመስጠት ላይ እንደሆነ ፍሬው ይጠቁማል።

"ከዚህ ባሻገር እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ክለቦች እንደ ቢዝነስ ተቋም አይንቀሳቀሱም ነበር። ከመንግሥት ብር ይወስዳሉ። እሱን ይጠቀማሉ። በቃ። አሁን ግን ገቢ ማስገባት ጀምረዋል። ይህ የሆነው በቴሌቪዥን በመታየታቸው ነው።"

ፍሬው አክሎ፣ የሊግ አክሲዮን ማኅበሩ ቀስ በቀስ እንደ ደቡብ አፍሪካ ፒኤስኤል፤ እንደ ታንዛኒያው ፉትቦል ቦርድ እንዲያድግ ያደርገዋል ይላል።

የሥነ ምግባር ጉዳይ

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን ወደኋላ ጎትቶታል ተብሎው ከሚታሰቡ ችግሮች መካከል የተጫዋቾችና ደጋፊዎች ሥነ-ምግባር ጉዳይ አንዱ እንደሆነ ይታመናል።

በተለይ ሊጉ የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ከማግኘቱ በፊት ባሉት ዓመታት የዳኛ ውሳኔን ባለማክበር እስከ አካላዊ ጥቃት የደረሰ ግጭት መመልከት የተለመደ ሆኖ ነበር።

ለመሆኑ ፕሪሚዬር ሊጉ የቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘቱ ይህንን ችግር ይቀርፈዋል?

ከዚህ በፊት ጥፋት ሲጠፋ የፕሪሚዬር ሊጉ አስተዳዳሪ የነበረው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅጣት የሚያስተላልፈው ከጨዋታ ኮሚሽነሮች በሚያገኘው መረጃ መሠረት እንደነበር ፍሬው ያስታውሳል።

"አሁን ግን ከጨዋታ ኮሚሽነሮች በተጨማሪ የተንቀሳቃሽ ምስል አለ። እንደቀድሞው ጥፋት አጥፍተህ ኮሚሽነሩ የኔ አካባቢ ሰው ነው፤ አሊያም በገንዘብ አልፈዋለሁ የምትልበት ጊዜ አይደለም አሁን። ሊግ ኮሚቴው ከኮሚሽነሮች ምስክርነት በተጨማሪ የተንቀሰቃሽ ምስል ተመልክቶ ስለሚወስን የዲሲፕሊን ጉዳይ ለውጥ አለው።"

ነገር ግን ይላል ፍሬው ". . .አፋችንን ሞልተን በጣም ቀንሷል ማለት አንችልም። ምክንያቱም ዲስኤ ቲቪ አምና ነው የመጣው። አምና ደግሞ ደጋፊዎች አልነበሩም። ቢኖሩም በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። ዘንድሮ ወደ 7 ሺህ አድጓል። ደጋፊዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሜዳ ሲመለሱ የዲሲፕሊኑም ጉዳይ ሊመለስ ይችላል የሚል ስጋት ይኖራል።"

ፕሪሚዬር ሊጉን የሚያስተዳደረው ሊግ ኩባንያ ደጋፊዎች ብሔር ተኮርና ፖለቲካ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን ወደ ስታድዬም ይዘው እንዳይመጡ የሚደነግግ ሕግ አውጥቷል።

ይህ ድንጋጌ ደጋፊዎቹ ወደ ሜዳ ሲመለሱ መሰል ድርጊቶችን እንዳይፈጽሙ፤ ከፈጸሙም የተንቀሳቃሽ ምስሎችን ተመልክቶ አጥፊዎች ላይ ቅጣት ለመጣል እንዲችል ያግዛል ይላል ፍሬው።

አቶ ባሕሩ "ስሜታዊነት ካሜራ ስላለ ላይቆም ይችላሉ" ይላሉ።

"የሚከታተልህ ሕዝብ እንዳለ ስታስብ ስሜታዊነትን ልትቀንስ ትችላለህ እንጂ ያን ያህል የጎላ የዲሲፕሊን ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም።"

ቢሆንም ጨዋታዎች በቴሌቪዥን መስኮት መተላለፋቸው፣ የተወሰነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ግን ያምናሉ።

የስታዲየም መቀመጫዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሳር ርዝመት ጉዳይ

የመጀመሪያው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም መተላለፍ ሲጀምር ከተስተዋሉ ጉዳዮች አንዱ የሜዳው ሳር ርዝመት ነው።

የተወሰኑ የሜዳው ክፍሎች ሳር እጅግ ከመርዘሙ የተነሳ የተጫዋቾችን ጫማ እስከመሸፈን ደርሷል። ይህ ጤናማ ነው?

እንደ አገር የተጀመሩ ስታድየሞችን የመጨረስ እንዲሁም የሜዳ አጠባበቅ ትልቅ ድክመት አለ ይላል ፍሬው።

"ኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ትላልቅ ስታድየሞችን ገንብታለች። ነገር ግን አልጨረሰቻቸውም። ለምሳሌ ሐዋሳ ውስጥ 50 ሺህ ሰው መያዝ የሚችለው ስታድየም አልተጠናቀቀም። ሌሎችም ቦታዎች እንዲሁ ነው" በማለት ክልሎችም ይሁኑ ክለቦች የተሻለ ሜዳ ማቅረብ ስላልቻሉ ሊግ ኩባንያው ፊቱን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ለማዞር መገደዱን ይጠቅሳሉ።

"የክልል መንግሥታት ከሚያቀርቡት ስታድየም በተለየ ዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ መሠረተ ልማት ዝርጋታ አላቸው። ለዚህ ነው ኩባንያው ፊቱን ወደዚህ ያዞረው።"

የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ ፀሐፊ አቶ ባሕሩ እንደ አገር ደረጃ የሚያሟላ ሜዳ አለመኖሩ በጣም ያሳዝናል ይላሉ።

"እንደሚታወቀው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሜዳ የለውም። አብዛኞቹ ሜዳዎች የክልሎች ናቸው። እኛ ሙያዊ እገዛ ከማድረግ በዘለለ የተለየ ነገር ማድረግ አንችልም። የክልል መንግሥታት ይህንን ለመቅረፍ መጣር አለባቸው፤ እኛም እገዛ ማድረግ ፍላጎታችንም ግዴታችንም ነው።"

መሻሻል የሚገባቸው

የዳኝነት ውሳኔ አሁንም ችግሮች ቢስተዋሉበትም ከአምናው ግን ተሻሽሏል የሚለው ፍሬው፣ በተጨማሪም "በሰዓት የመገኘት፣ ማሊያቸው ላይ ስማቸውን በትክክል መፃፍ የመሳሰሉ የፕሮፌሽናሊዝም ችግሮች አሉ። ነገር ግን ከአምና ዘንድሮ ይሻላል። ከዘንድሮ ደግሞ ቀጣዩ ዓመት ይሻላል ብዬ አምናለሁ። የብሮድካስት ዕድሉ ይህን ያሻሽላል የሚል እምነት አለኝ።"

እግር ኳስ ፌዴሬሽኑና ሊግ ኩባንያው ዳኞች ስህተታቸውን በምስል እንዲያዩና እንዲያርሙ በማድረጋቸው የተወሰነ ለውጥ አለ በማለትም "ከጨዋታ ውጭ ያልሆኑ ኳሶችን ይሽራሉ። ጥፋት ተፈፅሞ አልተፈፀመመም ይላሉ። ይህን ሁሉ የምታየው በመልሶ ምልከታ ነው።"

. . . ጨዋታዎች በቴሌቪዥን እየተላለፉ መሆናቸው ዳኞች ራሳቸውን ብቁ አድርገው እንዲገኙ ያደርጋል የሚል ዕምነት ያለው ፍሬው "ብዙ ነገር በጊዜ ሂደት የበለጠ ይስተካከላል የሚል እምነት አለኝ። ከአራትና አምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ 'ቪኤአር' [በቪዲዮ የታገዘ ዳንነትን] መጠቀም እንችል ይሆናል።"