ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ከወንዶች ያነሰ ክፍያ ይገባቸዋል-አሜሪካ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ እግር ኳስ ተቋም የአገሪቱ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ከወንዶቹ ጋር ሲነፃፀር ብቃቱ ያነሰ፤ የሚጣልበት ሃላፊነትም ትንሽ እንደሆነ አስታውቋል።
28 ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ተቋሙ ላይ ከወንዶች እኩል ይከፈለን የሚል ክስ መስርተው የነበረ ሲሆን የተቋሙ ጠበቆች ከላይ የተጠቀሰውን ነጥብ በማስረጃነት ለፍርድ ቤት አቅርበዋል።
የጽሑፉ መከራከሪያ የብሄራዊ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን አባል መሆን "ፍጥነትና ጥንካሬ ላይ የመሰረተ ትልቅ የኳስ ችሎታ የሚጠይቅ ነው" ይላል።
ክሱ ግንቦት ወር ላይ መሰማት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ግልፅ የዖታ አድልኦ'
የአሜሪካ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን አንድም ዓለም አቀፍ ውድድር ሳያሸንፍ የሴቶቹ ቡድን ግን አራት ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። አምስት ጊዜ ደግሞ የኦሊምፒክ ሜዳሊያ አግኝቷል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደ ቡድን ገቢ በማስገኘትም የሴቶቹ ቡድን የወንዶቹን ጥሎት ሄዷል። እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 እና በ2018 የሴቶቹ ቡድን በትኬት ሽያጭ ከፍተኛ ገቢ አግኝቷል።
ይህ ቢሆንም ግን ሴት ተጫዋቾች ከወንዶቹ ያነሰ እየተከፈላቸው እንደሆነ የሴቶች ቡድኑ ጠበቆች ገልፀዋል።
ስለዚህም ሴቶቹ ተጫዋቾች በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በሚያደርጉት የወዳጅነት ጨዋታ የሚያገኙት ጉርሻ 4950 ዶላር ሲሆን የወንዶቹ ቡድን በተመሳሳይ ጨዋታ 13000 ዶላር ከማግኘቱ ጋር ሲነፃፀር ክፍያው ኢፍትሃዊ ነው የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ የግድ ብሏል።
የሴቶች ቡድኑ ቃል አቀባይ ሞሊ ሊቪንሰን " 'ወንድ ተጫዋቾች ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው' የሚለው መከራከሪያ ግልፅ የፆታ አድልኦ እንደሆነ የትም ዓለም ላይ ያለ ሰው በግልፅ ይረዳዋል" ብለዋል። ክሱን ለመመስረት የገፋቸውም ይህ የፆታ አድልኦ እንደሆነ ገልፀዋል።
የሴቶች እግር ኳስ ቡድኑ የዛሬ ዓመት ክስ የመሰረተው ሴት ተጫዋቾች ከወንድ ተጫዋቾች እኩል ይከፈላቸው፤ 66 ሚሊዮን ዶላርም ለእስከዛሬው ጥፋት ካሳ ይከፈለን የሚል ነበር።
ከዚህም ባሻገር የአሜሪካው እግር ኳስ ተቋምን የተቀናጀ ፆታዊ አድልኦን በአሰራሩ የሚከተል ነው ሲሉም ወንጅለውታል።
የሴቶች ቡድኑ ኮኮብ ተጫዋች የሆነችው ሜጋን ራፒኖይ "ከእኩል ክፍያ ያነሰ የምንቀበለው ምንም ነገር አይኖርም" ብላለች ከኤቢሲ ቴሌቪዥን ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ።
"ሁሌም ለጨዋታ እንዘጋጃለን፣ ብናሸንፍም፣ ብንሸነፍም እኩል እንዲከፈለን እንፈልጋለን በቃ ይኸው ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእኩል ይከፈለን ጥያቄ
የሴት ተጫዋቾቹ እኩል ይከፈለን ጥያቄ በአጠቃላይ ህዝቡ በወንድ ተጫዋቾችም ድጋፍ ያገኘ ነው። ባለፈው ወር የወንዶቹ ብሄራዊ ቡድን የእግር ኳስ ተቋሙን ነቅፎ መግለጫ አውጥቶ ነበር።
"እውነት ነው ከክፍያና ከስራ ሁኔታ አንፃር ፌደሬሽኑ ሴቶች ላይ አድሎ ያደርጋል" ይላል ቡድኑ በጽሑፍ የሰጠው መግለጫ።
አሜሪካዊቷ የስፖርት ጋዜጠኛ ክርስቲን ሼልዊትዝ ህዝቡ ለሴቶቹ ቡድን ጥሩ አመለካከት እንዳለውና ጥያቄያቸውንም እንደሚደግፍ ትናገራለች።
የአሜሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት ካርሎስ ኮርዴሮ የሴቶች ቡድኑ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተቋሙ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ እንደነበር በደብዳቤ አስታውቀዋል።
የሽልማት ገንዘብ ልዩነት
ተቋማቸው የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ እንዳለ የሚናገሩት የፌደሬሽን መሪው ካርሎስ ኮርዴሮ ተቋማቸው በራሱ ቁጥጥር ስር ባሉ ውድድሮች ላይ ብቻ እኩል ክፍያ ለመስጠት መስማማቱን ገልፀው ነበር።
ነገር ግን ፌደሬሽኑ ሴቶች እግር ኳስ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ከወንዶቹ እኩል የሽልማት ገንዘብ ላለማግኘቱ ካሳ የመክፈል ፍላጎት የለውም።















