የአውስትራሊያ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች በወር 2 ሚሊዮን ብር ሊከፈላቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውስትራሊያ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን 'ማቲላድስ' ከወንዶች እኩል ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ሊያስገኝላቸው የሚችል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የአውስትራሊያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ በኋላ ሴቶች እና ወንዶች እኩል ነው የሚከፈላቸው ሲል ይፋ አድርጓል።
ማቲላድስ በሚል ቅጥያ የሚታወቁት የአውስትራሊያ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን አባላት በዓለም የሃገራት እግር ኳስ ሰንጠረዥ 8ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ወንዶቹ 44ኛ ናቸው።
በወንዶችና እና ሴቶች መካከል ያለውን የክፍያ ክፍተት ከመሸፈን አኳያ ይህ ትልቅ እርምጃ ነው ያሉት የፊፋ ሥራ አስፈፃሚ ዴቪድ ጋሎፕ ናቸው። የአውስትራሊያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ማሕበርም ውሳኔውን አድንቋል።
በስምምነቱ መሠረት ወንዶቹም ሆኑ ሴቶች ከማስታወቂያ የሚገኘውን 40 በመቶ ገቢ እኩል ይካፈላሉ። አልፎም ወርሃዊ ደሞዛቸው እኩል ይሆናል። ዋና ዋና ተጫዋቾች በወር 69 ሺህ ዶላር [2 ሚሊዮን ብር ገደማ] እንደሚከፈላቸውም ተሰምቷል።
አልፎም ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ከወንዶች እኩል ለሴቶች እንደሚደርሳቸው ታውቋል። ለምሳሌ ለወንዶች ብቻ ይፈቀድ የነበረው 'የቢዝነስ ክላስ' በረራ አሁን ለሴቶቹም ተፈቅዷል።
ቢሆንም አሁንም ወንዶቹ ከሴቶቹ የተሻለ የሚያገኙበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል ተብሏል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከውድድሮች በኋላ የሚከፈላቸው ገንዘብ ከሴቶቹ ላቅ ያለ መሆኑ ነው። አዘጋጆች ለወንዶች የሚከፍሉት ገንዘብ ከሴቶቹ ላቅ ያለ ነው።
ባለፈው ሐሙስ የተካሄደው የሴቶች ዓለም ዋንጫ በሴቶች እና ወንዶች መካከል ያለው የፍክያ ልዩነት እንደ አዲስ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጓል።
የዓለም ዋንጫ ባለድሎቹ የአሜሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አባላት የሃገራቸውን ፌዴሬሽን በዚሁ በክፍያ ጉዳይ መክሰሳቸው አይዘነጋም።
አውስታራሊያ፤ ከኒውዚላንድ እና ኖርዌይ ቀጥላ ሶስተኛዋ የሴቶች እና ወንዶች ክፍያ እኩሌታ የተከበረባት ሃገር ሆናለች።













