እግር ኳስና ኮሮናቫይረስ፡ የኢትዮጵያን ስም በአውሮፓ ያስጠራችው ሎዛ

ሎዛ አበራ

የፎቶው ባለመብት, LOZA ABERA/FB

ሎዛ አበራ በማልታ በሴቶች ዘርፍ የ2019/2020 የውድድር ዘመን ምርጥ ተጫዋች በመሆን በማልታ የእግርኳስ ተጫዋቾች ማህበር ተሸልማለች።

ሎዛ ለቢቢሲ አዲስ አይደለችም። የማልታውን ቡድን ቢርኪርካራ እንደተቀላቀለች እንዴት ነው ሕይወት በአውሮፓ ስንል አናግረናት ነበር። ከዚያ ቃለ ምልልስ በኋላ ሎዛ ብዙ ታሪክ ፅፋለች። ሪከርድ ሰብራለች።

ሎዛ ለሌሎች አንጋፋ የስፖርት መገናኛ ብዙሃንም አዲስ አይደለችም። ከጎል ዶት ኮም ጀምሮ እስከ ካፍ ኦንላይን ስለሎዛ አውርተው አይጠግቡም።

ቡድኗ ቢርኪርካራ ተቃናቃኙ ሂበርኒያንስን በማልታ ታሪክ ከፍተኛ በሆነ ጎል 17 ለምንም ሲረታ ሎዛ 7 ጎል መረብ ላይ አሳርፋለች። የተወሰኑ ኳሶችንም ለጎል አመቻችታ አቀብላለች።

ሎዛ ከዚህ ታሪካዊ ጨዋታ በፊትና በኋላ በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር ቡድኗ የማልቲዝ ሊግ ዋንጫ አሸናፊ እንዲሆን አድርጋለች።

ሎዛአሁንየትነች?

ሎዛ አሁን ያለችው ትውድል ቀዬዋ ነው። ከምባታ ዞን የምትገኘው ዱራሜ ከተማ።

አጥቂዋ ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ በመጣችበት ነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተከሰተው። በዚህ ምክንያት ወደ ማልታ ተመልሳ ማቅናት አልቻለችም። ለነገሩ የማልቲዝ ሊግ በወረርሽኙ ምክንያት ተቋርጦ ነበር።

ሎዛ ኢትዮጵያ እያለች ቡድኗ ቢርኪርካራ የማልታ የሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ መሆኑ ይፋ ሆነ።

ኢትዮጵያዊት ተስፈኛ አጥቂ በማልታ ሊግ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታዋ በ12 ጨዋታዎች 30 ጎሎች በማስቆጠር ኮከብ ጎል አግቢ ሆናለች።

'ከቢርኪርካራ ጋር ባለድል በመሆኔ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉም ነገር በመልካም ሁኔታ ተጠናቋል' ትላለች ሎዛ።

ሎዛ አበራ

የፎቶው ባለመብት, MFPA Awards

የወደፊት ዕቅድ

የማልታ የሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ የቀጣዩ ዓመት ውድድር በመጪው ጥቅምት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአዳማ ከነማ ቢርኪርካራን መስከረም 2012 ላይ የተቀላቀለችው ሎዛ ከቡድኑ ጋር ያላት ውል ተጠናቋል። ለመሆኑ ውሏን ለማራዘም አስባ ይሆን?

'ከቢርኪርካራ ጋር የነበረኝ ውል የአንድ ዓመት ነው። እሱ ተጠናቋል። እርግጥ ነው ቢርኪርካራ ውሌን ለማራዘም ጥያቄ አቅርበዋል። እኔም ያቀረብኩላቸው ቅድመ ሁኔታ አለ። በእሱ የምንስማማ ከሆነ ልቀጥል እችላለሁ።'

ሎዛ ከቢርኪርካራ ጋር የነበረኝ ቆይታ በጣም መልካም ነበር ትላለች።

'እርግጥ ነው አንድ ነገር ሲጀመር ሊከብድ ይችላል። ነገር ግን የማይለመድ የለም። ቡድኑ የነበረው ጥንካሬ ነበር። እዚያ ላይ የሁላችንም ጥረት ሲታከልበት ውጤታማ መሆን ችለናል።'

እውን የማልታ የሴቶች ሊግ ለተጫዋቾች ጥሩ ክፍያ ይከፍላል ወይ የሚል ጥያቄ ከቢቢሲ የቀረበላት ሎዛ፤ ክፍያው እንኳ ቢቀር የማልታ ልምዱ ለወፊት የተሻለ ውድድር ውስጥ ራሷን እንድታገኝ እንደሚረዳት ትናገራለች።

'አንድን ነገር ለማሳካትስ ስታስብ ብዙ ነገሮችን ከግምት ታስገባለህ። እኔ ክፍያን እዚህ ውስጥ አልከተውም። የክፍያ ማነስ አለ እያልኩ ሳይሆን አላማዬ በዚህ ጉዞ ራሴን ለማሳየት፤ ወጥቼ መጫወት እንደምችል ለማሳየትና ፕሮፋይሌን ከፍ ለማድረግ ስለሆነ ተሳክቶልኛል ብዬ ነው የማስበው።'

'እርግጥ ነው የሃገሬ ምግብ ናፍቆኝ ነበር' ትላለች ከግማሽ ዓመት በላይ በአውሮጳዊቷ ትንሽዬ የጠረፍ ሃገር የቆየችው ሎዛ።

የአዲስ ዓመት ልዩ ጥንቅር

ኮሮናቫይረስና እግር ኳስ

ባለፈው ታኅሣሥ ድምፁ የተሰማው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሰው ልጅ ከጠበቀው በላይ ጥፋት አድርሷል፤ የተለመዱ የሕይወት መስተጋብሮችን እንዳይሆኑ አድርጓል።

ወረርሽኙ ካመሰቃቀላቸው መስኮች አንዱ እግር ኳስ ነው። ይህ ወረርሽኝ በሎዛ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወት ላይ ያመጣው ተፅዕኖ ምን ይመስላል?

'በጣም ከባድ ነው። እግር ኳስን ብቻ ሳይሆን ሌሎች መስኮችንም የጎዳና ለዓለም የመጣ ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም።'

ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ከውድድር ርቀው የነበሩ እግር ኳስ ተጫዋቾች አንዱ ፈተናቸው በያሉበት ሆነው የአካል ብቃታቸውን ጠብቀው መቆየት ነው። ሎዛስ?

'በአቅራብያዬ በሚገኙ ቦታዎች እየሄድኩ እሠራ ነበር። ሠፈር ውስጥም ቤትም ነው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የማደርገው። ራቅ ብሎ ሄዶ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጊዜው ስለማይፈቅድ በምችለው መልኩ በአቅራቢያዬ ነበር እንቅስቃሴ ሳደርግ የነበረው።'

ሎዛ እሷ ብቻ ሳትሆን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንና የቀድሞ ቡድኗ አዳማ ከነማ ተጫዎቾችን አልፎ አልፎ በስልክ እንደምታገኛቸው በታቻላቸው መጠን በአካባቢዎች እንቅስቃሴ እያደረጉ እንዳሉ ትናገራለች።

አልፎም ሎዛ 'እንቅስቃሴ ማድረግ ከወረርሽኙ ሊታደገን ስለሚችል ሁሉም ሰው በያለበት የተቻለውን ያክል እንቅስቃሴ ቢያደርግ' ስትል ምክሯን ትለግሳለች።

የሎዛ የዲስ ዓመት ምኞት

'ሁላችንም ከምንወደው ሙያ ርቀን በቤታችን ነው ያለነው። ፈጣሪ ይህን ዓመት በሰላም አሻግሮ ይህንን ወረርሽኝ ያርቅልን፤ እንዲሁም ሁላችንንም ወደ ሥራ ይመልሰን ብዬ እመኛለሁ።'

'ስፖርተኛውም በስፖርቱ፤ ሌላውም በተሰማራበት መስክ በአዲሱ ዓመት የተሻለ ነገር እንሠራለን ብዬ ነው የማስበው።'

ቢቢሲ፡ እናመሰግናለን ሎዛ፤ ለአንቺና ለቤተቦችሽ መልካም አዲስ ዓመት ማለት እንወዳለን።

ሎዛ፡ እኔም አመሰግናለሁ። ለእናንተም መልካም አዲስ ዓመት!