የስፖርት ውርርድ አዲሱ የወጣቶች ሱስ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA
ሄኖክ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚኖር ወጣት ነው። ከስድስት ወር በፊት በጓደኞቹ ገፋፊነት የጀመረው በስፖርት ውድድሮች ላይ ገንዘብ ማስያዝ መወራረድ ሱስ እየሆነበት እንደመጣ ይናገራል።
''ከገንዘብ ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን እራስን ለመቆጣጠር ትንሽ ይከብዳል። በሳምንቱ መጨረሻ በሚደረጉ በተለይ የእንግሊዝና ሌሎች የአውሮፓ ሊጎች ላይ ሳላስይዝ አላልፍም''ይላል።
በትንሹ ከ10 ብር ጀምሮ እስከ 200 ብር ድረስ በአንድ ጊዜ እንደሚያስይዝ የሚናገረው ሄኖክ የጨዋታዎቹን ውጤት ለማየትና ምን ያህል እንደበላ አልያም እንደተበላ ለማረጋገጥ ቁጭ ብሎ ሌሊቱን የሚያሳልፍበት ጊዜም እንዳለ ይናገራል።
ሌላው ቢቀር ይላል ሄኖክ ''ማህበራዊ ሚዲያዎችን በተንቀሳቃሽ ስልኬ በመመልከት የማጠፋውን ጊዜ እንኳን ቀንሻለው። አጋጣሚው ሲኖረኝ ሁሌም የአቋማሪ ድርጅቱን መተግበሪያ ከፍቼ ማየት ነው የሚቀናኝ።''
በስፖርት ውድድሮች ውጤት ላይ ተመስርቶ መወራረድ በኢትዮጵያ እምብዛም የተለመደ ነገር አልነበረም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንደ አቢሲኒያ፣ አክሱምና ሃበሻን የመሳሰሉ የስፖርት አወራራጅ ድርጀቶች የብዙ ወጣቶችን ቀልብ መሳብ ጀምረዋል።
ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የአቢሲኒያ አወራራጅ ድርጅት መስራችና ባለቤት የሆነው አሸናፊ ንጉሤ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ፈቃድ አግኝተው መስራት የጀመሩት ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ መሆኑን ይናገራል።
አሸናፊ "ብዙ ሰዎች ከስፖርታዊ ውርርዶች ጋር በተያያዘ የተሳሳተ አመለካከት አላቸው" ብሎ ያምናል። በስፖርታዊ ውድድሮች ገንዘባቸውን ለማስያዝ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናትን በጉጉት ከሚጠብቁት እንደ ሄኖክ ካሉ ተቋማሪዎች በተለየ ሱስ የማስያዝም ሆነ አላግባብ ወጪ ውስጥ አያስገባም ይላል።
''በስፖርት ውድድሮች ይሄኛው ቡድን ያሸንፋል ሌላኛው ይሸነፋል እያሉ መወራረድ የተለመደና ሁሌም የነበረ ነገር ነው'' የሚለው አሸናፊ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ፈቃድ አግኝቶ ተሳታፊዎች ልኩን ባላለፈ መልኩ እንዲወራረዱ ማድረጉ ከጉዳቱ ጥቅሙ እንደሚበልጥ ያስረዳል።
''በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች ከሚታሰበው በላይ የስፖርት እውቀታቸው ጨምሯል። በዚህም ምክንያት ገንዘባቸውን ሲያስይዙ እራሱ በእውቀት ላይ ተመስርተው ነው። ገንዘባቸውን ከማስያዛቸው በፊት ሬድዮና ስፖርታዊ ድረገጾችን ተከታትለው ስለሆነ የሚመጡት ከውርርዱ በተጨማሪ መረጃ ቶሎ ቶሎ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል'' ይላል።
በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቴድሮስ ነዋይ በበኩላቸው የስፖርት ውርርድ ድርጀቶች ተገቢውን ቅድመ ሁኔታዎች እስካሟሉ ድረስ ማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድሩት ጫና እንደሌለ ይናገራሉ።
እስካሁን አስተዳደሩ 28 የሚሆኑ አወራራጅ ድርጅቶችን በህጋዊ መንገድ የመዘገበ ሲሆን 23 የሚሆኑት ፍቃድ ባገኙበት ዘርፍ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው። ከነዚህ መካከል አራቱ በያዝነው 2012 ዓ.ም ፍቃድ ያገኙ ናቸው።
አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ባለፈው ዓመት ከአወራራጅ ድርጅቶች ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢም አግኝቷል።
''በመጀመሪያ መረሳት የሌለበት በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩትን ድርጅቶች አቋማሪ አንላቸውም። የስፖርት ውድድር አወራራጅ ድርጅቶች ብለን ነው የምንጠራቸው'' ይላሉ።
''ቁማር ሲሆን አንዱ የሚጎዳበት አንዱ ብቻ ደግሞ የሚጠቀምት ነው። ስለዚህ ምንም ማህበራዊ ፋይዳ ሊኖረመው አይችልም። እኛ ፈቃድ የምንሰጠው የስፖርት ውርርድ ባህሪው የሎተሪ ነው። ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቶች ጊዜያቸውን በሌሎች ነገሮች ላይ ከሚያሳልፉ እየተዝናኑ እድላቸውን የሚሞክሩበት ነው።''
''ማህበራዊ ፋይዳ ከሌለው እኛም ፈቃድ አንሰጥም'' የሚሉት አቶ ቴድዎሮስ ለዚህም ድርጅቶቹ ከውርርድ ከሚያገኙት ገቢ 20 በመቶውን በመረጡት ማህበራዊ የበጎ አድራጎት ተቋም ላይ እንዲያውሉ እንደሚገደዱ ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከድርጅቶቹ ገቢ 15 በመቶውን በኮሚሽን መልክ የሚወስድ ሲሆን ድርጅቶቹ ከደንበኞቻቸው ግብር ሰብስበውም ለመንግሥት ገቢ ያደርጋሉ። በተጨማሪ ዓመታዊ የግብር ግዴታቸውንም ይከፍላሉ።
እነዚህ ሁሉ ሂደቶች ድርጅቶቹ ብዙ ትርፍ እንዳይግበሰብሱና የሚገኘው ገቢ ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች መዋላቸውን ማረጋገጫ እንደሚሰጣቸው አቶ ቴድሮስ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, PASCAL GUYOT
ሌላኛው ያነጋገርነውና በስፖርት ውድድሮች ገንዘብ ማስያዝ ከጀመረ ብዙ ጊዜ እንዳልሆነው የሚናገረው አሰግድ በሳምንት ቢያንስ አምስት ጨዋታዎች ላይ ገንዘቡን እንደሚያስይዝ ይናገራል።
አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ዘመናዊ አሰራር ስለሌላቸው በአካል ሄዶ ገንዘብ ማስያዝና መቀበል አድካሚ መሆኑን ይገልጻል።
''ብዙ ጊዜ በስሜ ገንዘብ ለማስገባትም ሆነ ካሸነፍኩኝ ገንዘቤን ለመቀበል ወደ አቋማሪ ድርጅቶቹ ቢሮ ድረስ መሄድ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ወደ ቢሮው የሚሄድ ጓደኛዬ ካለ ለእኔም እንዲያስገባልኝ የማደርግብትም ጊዜ አለ'' ይላል።
ምንም እንኳን ውርርድን በተመለከተ ስለኢትዮጵያ በቂ የሆነ መረጃ ባይበኖርም በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ ወይንም በናይጄሪያ የሚገኙ እድሜያቸው ከ18 እስከ 40 የሚደርሱ ሰዎች በአማካይ በቀን እስከ 15 ዶላር ድረስ እንደሚያስይዙ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
በሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከሚስተዋለው በተለየ ሄኖክ ገንዘቡን የሚያስይዝባቸው ድርጅቶ የሀገር ውስጥ ውድድሮችን እምብዛም እንደማያካትቱና በብዛት የአውሮፓ ሊጎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ይናገራል።
እስከ 14 ሺህ ብር ድረስ ሁለት ጊዜ በውርርድ እንዳሸነፈ የሚናገረው ሄኖክ ገንዘቡን ከማስያዙ በፊት የተለያዩ መረጃዎችን እንደሚሰበስብና አማራጮቹን ለማብዛት እንደሚሞክር ነግሮናል።
በስፖርታዊ ውድድሮች መወራረድ ጋር አብሮ የሚነሳ አንድ ችግር አለ። እሱም እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችና ተማሪዎች በዚሁ ተግባር ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሊያጠፉ መቻላቸው ነው።
አሰግድ አብዛኛዎቹ አወራራጅ ድርጅቶች ለመወራረድ ከሚመጡት ሰዎች መካከል ምን ያህሉ "እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች መሆኑን የሚቆጣጠሩ አይመስለኝም" ይላል።
''እኔ በግሌ ገንዘብ ለማስያዝ ስሄድ ትንንሽ ልጆችን እመለከታለው። ልክ እንደ ማንኛውም ሰው ተስተናግደው ነው የሚሄዱት። በስልካቸው መተግበሪያዎችን አውርደው ሲጠቀሙም እምለከታለው" ሲል አሳሳቢ መሆኑን ይተቅሳል።
የአቢሲኒያ አወራራጅ ድርጅት ባለቤት አሸናፊ ንጉሤ ግን እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች በስፖርታዊ ውድድሮች እንዳይሳተፉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ይናገራል።
''ማንኛውም ሰው ገንዘብ ለማስያዝም ሆነ አባል ለመሆን ወደ ቢሮዎቻችን ሲመጣ መታወቂያ እንጠይቃለን። በድረ ገጽና በስልክ መተግበሪያዎች ለሚጫወቱት ደግሞ የገንዘብ ዝውውር ለማድረግ በባንክ በኩል የሂሳብ ደብተር መክፈት ስላለባቸው የእድሜያቸውን ነገር በዚው እንቆጣጠረዋለን።''
''ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንዲጫወቱ አንፈቅድም፤ አብረውት ሊመጡ የሚችሉትንም ጉዳቶች ጠንቅቀን እናውቃቸዋለን'' ይላል።
የስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የሚደረግ ውርርድ ዙሪያ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ድርጅቶቹ እንዳያጫውቱ የሚከለክል መመሪያ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ባይኖረውም ውርርዱ ላይ ህጻናት እንዳይሳተፉ ስምምነት እንዳላቸው የአስተዳደሩ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ገልጸዋል።
''እድሜያቸው ያልደረሰ ህጻናት የሚጫወቱ ከሆነ ተገቢውን እርምጃ ከመውሰድ ግን ወደኋላ አንልም። ጥቆማ ከደረሰንም የምንከታተል ሲሆን እስካሁን ግን ምንም የደረሰን ቅሬታም ሆነ ጥቆማ የለም'' ይላሉ።
ውርርድ ሱስ የማስያዝ ባህሪ ሊኖረው ስለሚችል ወደፊት የዘርፉን አካሄድ በመመልከትና ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን አቶ ቴድሮስ ገልጸዋል።
ለአሁኑ ግን በኢትዮጵያ ያለው የውርርድ ዘርፍ ገና ጀማሪ በሚባልበት ደረጃ በመሆኑ አካሄዱን መከታተልና ማህበረሰቡ እየተዝናና ሃላፊነቱን የሚወጣበትን መንገድ ማማቻቸት ላይ ትኩረት እንዳደረጉም አክለዋል።
ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ መወራረድ ሙሉ በሙሉ መከልክል የለበትም የሚለው ሃሳብ ያሚያስማማቸው አሰግድና ሄኖክ አወራራጅ ድርጅቶችም ሆነ መንግሥት ውርርድ ሱስ ሊያስይዝ እንደሚችል በደንብ መረጃ ቢሰጡና ዘርፉ ጠበቅ ያለ ክትትል ቢደረግብት መልካም እንደሆነ ግን ያምናሉ።
ከስፖርታዊ ውርርዶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ ለስፖርታዊ ውድድሮች ያለ ከፍተኛ ፍቅር፣ የላላ የቁማር ህግና ቀላል የተንቀሳቃሽ ስልክ ክፍያ መንገዶች መብዛት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሃገራት ትልቅ ፈተና ሊደቅኑ እንደሚችሉ አንዳንዶች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።












