"እንዴት ለሴት ልጅ የወንዶች ክለብ ይሰጣል?' ተብሎ ነበር" ኢንስትራክተር መሠረት ማኒ

የፎቶው ባለመብት, MESERET MANI
ውልደቷ ድሬዳዋ ነው፤ ልዩ ስሙ አንደኛ መንገድ ከሚባል ሥፍራ፤ ደቻቱ ግድም ማለት ነው። ይህ ሠፈር ደግሞ ለአሸዋው ቅርብ ነው። ኳስ እያንቀረቀቡ ለማደግ የሰጠ ነው።
አንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በለገሃሬ፤ ሁለተኛውን ደግሞ በድሬዳዋ አጠቃላይ ትምህርት ቤት ተስተምራለች።
ፊፋ በ1983 የዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫን በይፋ ከማካሄዱ በፊት ሴቶቹ በይፋ እግር ኳስ እንዲጫወቱ አይፈቀድም [አይፈለግምም] ነበር። ነገር ግን ይህ ኳስ ከመጫወት አላገዳትም [በፕሮፌሽናል ደረጃ ባይሆንም]።
ማንም ከተጫዋችነት ወደ አሠልጣኝነት ወደ መምጣት የከለከላት አልነበረም፤ በኢትዮጵያ [በአፍሪካም] ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የወንዶች እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ከመሆን ሊመልሳት የቻለም አልተገኘም. . . እርሷም ማንም ወደኋላ እንዲጎትታት አልፈቀደችም. . . መሠረት ማኒ።
የአሠልጣኝነት ሕይወት
«አሠልጣኝነትን የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነው ። ልጅ እያለሁ ራሱ 'የሊደርሺፕ' ተሰጥዖ ነበረኝ። ከዚያ ጓደኞቼን ሰብስቤ 'ድል በትግል' የሚባል ቡድን መሠረትኩ። ከዚያ የሕንፃ ቡድን፤ ቀጥሎ የመድህን ድርጅት የተወሰነ ድጋፍ እያደረገልኝ ማሠልጠን ጀምርኩ። ከዚያ የ'ሴቭ ዘ ቺልድረን' የሴቶች እና ወንዶች ቡድንን መሥርቼ ማሠልጠን ያዝኩ።»
መሠረት የምታሠለጥነው የእግር ኳስ ቡድኖችን ብቻ አልነበረም። የቴኒስ እና መረብ ኳስ ቡድኖችንም ታሠለጥን ነበር። 'ማቴሪያል' ስለነበር ፍላጎቱ ያላቸው የድሬዳዋ ልጆች እንዲሠለጥኑ አደርግ ነበር።
1970 ዎቹ ላይ እነ ማክዳ፣ ታጠቅ፣ አየር ኃይል እና መሰል የሴት እግር ኳስ ቡድኖች፤ የሴቶች እግር ኳስ ሲቋረጥ በዚያ ከሰሙ። ከዚያ 1986 ላይ የመጀመሪያውን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በማቋቋም በታሪክ መዝገብ ስሟን አሰፈረች።
2004 ላይ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ሲጀመር መሠረት የከተማዋን ሴቶች ቡድን ይዛ ተቀላቀለች።
![መሠረት ማኒ ታሠለጥነው የነበረው የድሬዳዋ ከነማ መረብ ኳስ ቡድን [1977]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/D244/production/_107482835_whatsappimage2019-06-21at1.05.13pm.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, MESERET MANI
ድሬዳዋ ከነማ
2007 ላይ ድሬዳዋ ከነማ የፕሪሚዬር ሊጉ ታናሽ በሆነው የሊግ ውድድር ላይ ተሳታፊ ነበር። ይሄኔ ነው መሠረት ማኒ የወንዶቹን ቡድን ተረክባ ለፕሪሚዬር ሊግ ለማሰለፍ ቃል በመግባት ሥራ የጀመረችው።
«እርግጥ በጣም 'ቻሌንጂንግ' ነበር። ቢሆንም ለእኔ ብዙ ያልከበደኝ፤ ከልጅነቴም ጀምሮ ወንዶችን እያሠለጠንኩ ማደጌ ነው። ትላልቆቹም ሳሰለጥናቸው የሚሠጡኝ አክብሮትና ፍቅር እንዲሁም ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት መንገድ አቅም ሆኖኝ ነበር። በፆታ መለካቴ ግን አልቀረም። 'እንዴት ለሴት ልጅ የወንዶች ክለብ ይሰጣል? ቀልድ ነው እንዴ የያዙት?' ያሉ አልጠፉም ነበር። አንዳንዶቹም እንደውም ይሄ ለፖለቲካ 'ኮንሳምፕሽን' ነው ብለው ከንቲባው [የድሬዳዋ] ድረስ ይሄዱ ነበር። ነገር ግን ለኔ የበለጠ አቅም ነበር የሆነኝ። ምክንያቱም ይህንን መቀየር አለብኝ አልኩኝ፤ በምን? በውጤት።»
ከውጭ ብዙ ፈተና የገጠማት መሠረት ከውስጥም መንገዱ አልጋ 'ባልጋ አልሆነላትም። በዚያ ላይ የመጀመሪያው ዙር ለመሠረት ቀላል የሚባል አልነበረም፤ ሦስት ነጥብ ማግኘት።
«ተጨዋቾቼን ማሳመን አንዱ ፈተና ነበር። በሴት ሠልጥነው አያውቁም፤ ትልልቅ ተጨዋቾች ናቸው። 'እንዴት ነው አሁን እሷ እኛን የምትመራን?' የሚል ጥያቄ ነበራቸው። አንዳንዶቹ የመሥራት ፍላጎታቸው ውርድ ያለም ነበር። ነገር ግን ልጆቼን በሥራ ማሳመን ቻልኩኝ። በተለይ ሁለተኛው ዙር ላይ በውጤት በጣም አሪፍ ነበርን። እንደውም ከ12 ጨዋታ 11 አሸንፈን በአንዱ ብቻ ነው አቻ የተለያየነው።»
ጉዞ ወደፕሪሚዬር ሊግ
ድሬዳዋ ከነማ በአሠልጣኝ መሠረት ማኒ እየተመራ ፕሪሚዬር ሊግ ገባ። ሁሉም 'ሴት የወንዶች አሠልጣኝ?' ሲል መጠየቅ ጀመረ። አድኖቆት ጎረፈላት። ተጫዋቾች፣ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይ ደግሞ ድሬዎች ቆመው አጨበጨቡላት።
ፕሪሚዬር ሊግ ከብሔራዊ ሊግ ሲነፃፀር ከበድ [በጥራት] ያለ ቢሆንም መሠረትን የሚያቆም ግን አልተገኘም። ክለቧ ትልቁ ዓላማው የነበረው ከፕሪሚዬር ሊጉ ተመልሶ አለመውረድ ነበር። መሠረት ግን አለመውረድ አላስጨነቃትም፤ ውጤቱ የበለጠ እንዲያምር ጣረች።
«ስንጀምረው አራት ጨዋታ ማሸነፍ አልቻልንም ነበር። ከአምስተኛው ጨዋታ በኋላ ግን ሁሉንም እያስተካከልን መጣን። እንደውም በአንደኛው ዙር አምስተኛ ሆነን ጨረስን፤ ይሄ ደግሞ ትልቅ ድል ነው። በተለይ ከብሔራዊ ሊግ ለመጣ ቡድን ሊያውም በሴት አሠልጣኝ ለሚሠለጥን።»

የፎቶው ባለመብት, MESERET MANI
ፍቺ ከድሬዳዋ ጋር
ቢሆንም ሁለተኛው ዙር የድሬዳዋ ውጤት ዕለት ተ'ለት ያሽቆለቁል ያዘ። በመጀመሪያዎቹ አምስት ጨዋታዎች ጥሩ ውጤታ ማምጣት የቻለው ድሬዳዋ ከነማ ሦስት ነጥብ ብርቁ ሆነ።
ምን ተፈጠረ?
«እኔ እስከዛሬም ድረስ ሳስበው ግራ ይገባኛል። ምንድን ነው ነገሩ ብዬ ልጆቼን ጠየቅኩ፤ ግን አጥጋቢ ምላሽ አላገኘሁም። አንድ የማላውቀው እና ውጤታችንን እንዲያሽቆለቁል ያደረገ ነገር እንዳለ አሁንም ድረስ ይሰማኛል። አሁን ራሱ አንዳድንድ ተጨዋቾችን ሳገኝ እጠይቃለሁ፤ ግን ብዙም አይነግሩኝም። የሆነ ነገር እንዳለ ግን ይሰማኛል፤ ከውጭም ከውስጥም። ወደፊትም መጠየቄን አላቆምም።»
ከዚያ «በዚህ መንገድ መቀጠል አልቻልኩም ትላለች» መሠረት።
«ገንዘብ ፈልጌ አይደለም የመጣሁት እኔ። እኔ መሥራት ነው የምፈልገው። በዚህ መንገድ መቀጠል ደግሞ አልፈልግም። ጫናዎች በዝተዋል። እግር ኳስ ደግሞ ነፃነት ይፈልጋል። እኔ በቃኝ 'ቴንኪው' ብዬ፤ ልጆቼን እና 'ስታፉን' ተሰናብቼ ቡደኑን ለቅቄ ወጣሁ።»
ይህ የሆነው እንግዲህ 2008 ላይ ነው። መሠረት 2002 ላይ ሉሲዎችን ተረክባ ታሪክ ፅፋለች፤ ታሪኩ ምንድን ነው? ብሎ ለሚጠይቅ 'ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በሴት አሠልጣኝ የተመራበት ወቅት በመሆኑ [የተሰጣት ኮንትራት የ3 ወራት ብቻ ቢሆንም]' መልሷ ነው።
መሠረት ከዚያ በኋላ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴሬሽን በቀረበላት ግብዣ ወደ አሜሪካ አቀናች። ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ከአሜሪካ ኤምባሲ በቀረባለት ግብዣ አሜሪካ ደርሳ ተመልሳለች። ወደ አሜሪካ ከማቅናቷ በፊት ሉሲዎችን እንደገና ተረክባ ነበር [2009]። ስትመለስ ግን የአሠልጣኝነት ቦታው በሌላ ሰው ተይዞ ጠበቃት።
እንደገና ሉሲዎችን ተረክባ ወደ ኡጋንዳ አቀናች፤ በሴካፋ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ። ኳስ ይዞ በማጥቃት የአጨዋወት ስልት የምትታወቀው መሠረት ውድድሩን ሦስተኛ ሆና በማጠናቀቅ የነሃስ ሜዳሊያ ይዛ ተመለሰች [የራሳችን ድክመት ነው እንጂ ዋንጫ ማምጣት ይገባን ነበር ትላለች]። ቢሆንም ኮንትራቷ ከመጠናቀቁ በፊት ሉሲዎች ሌላ አሠልጣኝ ተሾመላቸው።
መሠረት አዲሱን መፅሐፏን ለማስመረቅ ጉድ ጉድ በማለት ላይ ትገኛለች። 'የስኬት ተምሳሌት' የተሰኘ ርዕስ ሰጥታዋለች። ያለፈችበትን ውጣ ውረድ የሚያትት 198 ገፆች ያሉት መፅሐፍ ነው። «ይሄኔ ነው ጀምሬው የነበረውን መፅሐፍ ልጨርስ ብዬ ትኩረቴን ወደዚያ ያደርግኩት» ብላናለች።
ክፍያ
መሠረት ድሬዳዋ ከነማ እያለሽ ምን ያህል ነበር የሚከፈልሽ? እንደው ፈቃደኛ ከሆንሽ ብትነግሪን?
«ኧረ በደንብ ነው ምነግርህ [ፈገግታ]. . . እንግዲህ እኔ ፕሪሚዬር ሊግ እያለሁ 14 ክለቦች ነበሩ። በወቅቱ ዝቅተኛው የአሠልጣኝ ክፍያ የኔ ነበር። ተቆራርጦ እጄ ላይ 'ሚደርሰኝ 13ሺህ 500 ብር ነበር። ያኔ የወረዱት ዳሸንና የሆሳዕና ቡድን አሠልጣኞች ከኔ የተሻለ ክፍያ ያገኙ እንደነበር አውቃለሁ። ምክንያቱም እኔ ብዙ ጊዜ በፆታዬ ነው 'ምለካው። እንጂ ባለኝ አቅም አልነበረም። ይሄን ሳስብ ያመኛል ግን በቃ ፍቅር ነው፤ ኳሱን እወደዋለሁ፤ እሠራዋለሁ።
ስፖርታዊ ጨዋነት
አሠልጣኞች እና ተጨዋቾች በድህረ-ጨዋታ መጨባበጥና ማልያ መቀያየር የተለመደ ነው። እርግጥ አሁን አሁን በሰላም ጨዋታን መጨረስ በራሱ ትልቅ ድል እየሆነ ቢመጣም።
እንደው በመሠረት እንዴት እንሸነፋለን ያሉ አሠልጣኞች እና ተጫዋቾች እጅ ነስተዋት ያውቁ ይሆን?
«የነፈጉኝን እንኳ ብዙም አላስታውስም፤ ግን እኔ አንድ ጊዜ በደስታ ውስጥ ሆኜ ሳልጨባበጥ በመቅረቴ ተከስሻለሁ። እዚሁ ድሬዳዋ ላይ ነው። ከሙገር ሲሚንቶ ጋር እየተጫወትን ነበር። ደርቢ በመሆናችን ጨዋታው ደመቅ ያለ ነበር። 0-0 ነበርንና ባለቀ ሰዓት አገባንና አሸነፍን። በቃ በጣም ደስተኛ ስለነበርኩ የሙገር አሠልጣኝን ሳልጨብጠው ቀረሁ። ከዚያ እስከ ክስ ደረጃ ደርሶ ነበር።»
እንዴት ይረሣል?
ሰዎች አሠልጣኝ መሠረትን ሲያስቡ ቀድሞ ትዝ የሚለቸው ከድሬዳዋ ከነማ ጋር የተጎናፀፈችው ስኬት ነው። እርሷም ከማትረሳቸው ድሎች መካከል አንዱ እርሱ ነው። ግን ከዚያም በላይ የማልረሳው ትላለች መሠረት. . .
«የማልረሳቸው ሁለት ቀናት አሉ። አንደኛው ከአዲስ አበባ ከነማ ጋር አራት ውስጥ ለመግባት የተጫወትነው ነው። 1 ለ 0 እየመራን ነበር፤ ከዚያ አቻ ሆንን። አንድ ጨምረን መምራት ያዝን፤ ግን መልሶ ተቆጠረብን። በስመዓብ አሁን በቃ 2 ለ 2 ሆነን ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ልንሄድ ነው። ከምክትሌ ጋር ተነጋገርኩና 'ቤንቹ' በረኛ 'ፔናሊቲ' ጎበዝ ስለሆነ ብለን አስገባነው። በረኛችን ሦስት ጎል አዳነልንና አሸነፍን።»
«ሁለተኛው ቅዱስ ጊዮርጊስን የረታንበትን ነው። እንግዲህ ጊዮርጊስ በጣም ትልቅ ቡድን ነው። እኔ ደግሞ ፕሪሚዬር ሊጉ አዲሴ ነው። እና በሜዳዬ ሊያውም በጨዋታ ብልጫ ማሸነፌ ፍፁም አልረሳውም። በጣም ልዩ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, MESERET MANI
2012. . .?
መሠረት አሁን ላይ የአዲስ አበባ ሴቶች እግር ኳስ ቡድንን በማሠልጠን ላይ ትገኛለች። አንደኛ ዲቪዚዮን ላይ እየተጫወተ የሚገኘው አ.አ. ስድስተኛ ደረጃን ይዞ የውድድር ዘመኑን አጠናቋል።
መሠረት ስለወደፊቱ ዕቅዷ እጅጉን እያሰበችበት እንደሆነ አልደበቀችንም።
«ብዙ ዕቅዶች አሉኝ። የሕፃናት አካዳሚም አለኝ [120 ሕፃናት ያሉት]። እሱን ከፍ ማድረግም ሕልሜ ነው። የአሠልጣኝነት ጥያቄዎችም ይመጣሉ። እውነት ለመናገር ብዙ 'ፍራስትሬት' የሚያደርጉ አጋጣሚዎች ገጥመውኛል። ሙያውን ለመተው ሁላ አስቤ አውቃለሁ፤ ግን ደግሞ ብዙ ሰዎች ይህን ውሳኔዬን ሲቃወሙ አያለሁ። በተለይ ያሠለጠንኳቸው ልጆች 'ኖ መቀጠል አለብሽ' የሚል አስተያየት ይሰጡኛል። ስለዚህ ቁጭ ብዬ ማሰብ አለብኝ ብያለሁ።»

የፎቶው ባለመብት, MESERET MANI
ምክር ለተተኪዎች
በኢትዮጵያም ሆነ በአህጉረ አፍሪካ ከመሠረት ሌላ ሴት የወንዶች እግር ኳስ ክለብ አሠልጣኝ እንዳለች አልሰማንም፤ አላየንም። ይህንን ክብር መጎናፀፍ ምን ዓይነት ስሜት ይሰጥ ይሆን?
«በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ሌላ ሴት አለመኖሯ ሳይሆን፤ ስኬታማ መሆን መቻሌ ደስ ያሰኘኛል። ሴት ልጅ ይህንን ማድረግ እንደምትችል ደግሞ ማሳየት መቻሌ እጅግ ያኮራኛል። እንጂ ብቸኛ ስለሆንኩኝ አይደለም፤ በቃ ይቻላል የሚለውን መንፈስ ማንገስ መቻሌ ነው። ሁሌም የምለው ሴቶች በፆታቸው ሳይሆን በአቅማቸው ቢለኩ ነው።»
«አንዲት ሴት አናጢም መሆን ትፈልግ፣ ኢንጅነር ወይም ኤሌክትሪሺያን ለዚያ ሙያ የሚሆን ዕውቀት ያስፈልጋታል። ይህ ደግሞ እንዲሁ አይገኝም፤ ልፋት ይጠይቃል፤ ጥረት ያስፈልጋል፤ ድካም ያስፈልጋል፤ በቀላሉ የሚገኝ ነገር የለም። እኔ ሴት ስለሆንኩ እንደው እንደ ገፀ-በረከት እንዲሰጠኝ አልፈልግም። በራሴ ልክ፤ ባለኝ አቅም እንጂ። የማይቻል ምንም ነገር የለም። ሕልም ይኑረን።»
እኛም ምክር ያፅና ብለናል፤ ለመሠረትም መልካም ዕድል!
















