ከዋንጫ ባለቤትነት ወደ ፀጉር ሥራ - የኦካፎር ጉዞ

ቺኔኔ ኦካፎር
የምስሉ መግለጫ, ቺኔኔ ኦካፎር

'በአገሪቱ አለ ለተባለ ክለብ እየተጫወትሽ ቡድንሽ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የዋንጫ ባለቤት ስታደርጊ ሁሉም ነገር አልጋባ’ልጋ ይሆናል ብለሽ ታስቢያለሽ።'

ቺኔኔ ኦካፎር ህልሟ ይህ ነበር። ዋንጫ ላይ ዋንጫ ማንሳት። ሜዳልያ ላይ ሜዳልያ መደረብ።

ኦካፎር የፔሊካን ስታርስ አምበል ነበረች። የተከበረች፤ የተፈራች።

ከሐምሌ በኋላ ግን ሙያ ቀይራለች። ከእግር ኳሰ ተጫዋችነት ወደ ፀጉር ሥራ። ይህን የሆነው ለአንድ ዓመት ያክል ደመወዝ ሳይከፈላት ኳስ መጫወቱን ከቀጠለችበት በኋላ ነው።

ምንም እንኳ ለዚህ ምክንያቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቢሆንም የክለቡ ኃላፊዎችም የብዙ ሴት ተጫዋቾች ሕልም እንዲከስም አሉታዊ አስተዋፅዖ ነበራቸው።

"ለሰዎች እግር ኳስ ተጫዋች ነኝ ብዬ መናገር ይከብደኛል። እሸማቀቃለሁ። 22 ዓመት ሙሉ በፍቅር የተጫወትኩት እግር ኳስ በስተመጨረሻ ሲክደኝ ጊዜ ምን ላድርግ?" ትላለች ናይጄሪያዊቷ።

"አሁን ፀጉር ሠሪ ነኝ። ከ2፡30 እስከ አመሻሽ 11፡30 እሠራለሁ። ከሰኞ እስከ ቅዳሜ። ከባድ ቢሆንም ፈጣሪ ይመስገን እየለመድኩት ነው።"

ኦካፎር በናይጄሪያ ታዋቂውን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የመራች ነበረች። ለዚያውም የሊጉን ዋንጫ 8 ጊዜ የበላው የኃያሉ ፔሊካን ስታርስን።

ፔሊካን ቡድን ስድስት ጊዜ የሊጉን ዋንጫ የበላችው በዘጠኝ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው። ነገር ግን የክለቡ ጉዞ ከድል አድራጊነት ወደ ኪሳራ ማምራት የጀመረው በጥቂት ዓመታት ውስጥ ነው።

"አንዳንድ ጊዜ ጠዋት ተነስቼ ምንድነው የምበላው እያልኩ እጨነቅ ነበር" ትላለች ኮከቧ።

ከቡድን አጋሮቿ ጋር

የሰመረ ጅማሬ

ኦካፎር ፔሊካን ስታርስን የተቀላቀለችው በፈረንጆቹ 2018 ነው። ነገር ግን ክለቡ በዚህ ዓመት እንኳን ዋንጫ ሊያነሳ ይቅርና በዋናው ሊግ መቆየት አቅቶት ወደታች ወረደ።

ነገር ግን ውድቀትን እሺ ብለው መቀበል ያልሻቱት ኦካፎርና ጓደኞቿ ጠንክረው ሠርተው ክለቡን ወደ ፕሪሚዬር ሊግ መለሱት። ድሉ ጣፋጭ ነበር።

ወደ ፕሪሚዬር ሊግ እንደገና ካደጉ በኋላ ግን ነገሮች ቅርፃቸውን መቀየር ያዙ። በወር ከ78 እስከ 182 ዶላር ለተጫዋቾቹ ይከፍል የነበረው ክለብ በዓመቱ አጋማሽ ደመወዝ ማዘግየት ጀመረ።

ነገሮች መክፋት የጀመሩት የካቲት ላይ መከፈል የነበረበት ደመወዝ መጋቢት ላይ ሲመጣ ነው። ሰኔ ሲገባ ደግሞ ጭራሽ ደመወዝ መከፈል አቆመ። ይህ የሆነው ባለፈው ዓመት ነበር።

የጨለመ ተስፋ

የጠበቁት ደመወዝ ውሃ ሲበላው የክለቡ ተጫዋች ጩኸት ማሰማት ጀመሩ።

ገና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሁሉንም በር አንኳኩቶ ምጣኔ ሃብት ማቃወስ ከመጀመሩ በፊት ኦካፋርና አጋሮቿ ሲያሻው በሚመጣ ሲያሻው በሚቀር ደመወዝ መንገላታት ጀመሩ።

"ትዝ ይለኛል ወረርሽኙ ከመስፋፋቱ በፊት የክለቡ ምክትል ኃላፊ እሽግ ሩዝ ገዝቶ አከፋፈለን። አንዳንድ ጊዜ ካምፕ ውስጥ ምግብ እንጋራ ነበር። ግድ ሲሆንብን ደግሞ ተበድረን ምግብ እንገዛ ነበር።"

ኦካፎርና ሌሎች ተጫዋቾች እጅግ ያበሳጫቸው የክለቡ ኃላፊዎች የወንዶቹን ቡድን እየደጎሙ ለእነሱ ግን ሩዝ በመግዛት ብቻ ሲደልሏቸው ሲመለከቱ ነው።

"የወንዶቹ ቡድን ደመወዝ ይከፈለው ነበር። ምን እነሱ ብቻ ታዳጊዎችም ይከፈላቸው ነበር። የእኛ ደመወዝ ግን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ተነፍጎን ነበር።"

ባለፈው ሚያዚያ የክለቡ ተጫዋቾች በክለቡ ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ።

ኳስ ስትጫወት

"መሥሪያ ቤቱን የሚጠብቁ ሰዎች የጦር መሣሪያ አውጥተው አካባቢውን ለቀን እንድንሄድ አስፈራሩን። ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስላል እዚህ መሆን አትችሉም አሉን።"

"በጣም ተሸማቀቅኩ። የቡድናችን ልጅ ታማ ነበር። የምትበላው አልነበራትም። በዚህ ምክንያት አሁን ኳስ መጫወት የምትችል አይመስለኝም።"

የቡድኑ አባላት ለሁለተኛ ጊዜ ተቃውሞ ሲያደርጉ የክለቡ አስተዳዳሪዎች በሚያዝያ ወር መጨረሻ ሁሉም ይስተካከላል የሚል መልዕክት አስተላለፉ።

ነገር ግን ኦካፎርና ጓደኞቿ ጉሮሯቸውን ለማርጠብ ሲሉ ወደ ሌላ ሙያ ለመሠማራት ሥር ፍለጋ ላይ ነበሩ።

"አንዳንዶቻችን ፀጉር ሥራ ላይ ነን። ልብስ መስፋት የጀመሩም አሉ። ከቤተሰቦቻችንና ከሌሎች ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች እርዳታ ተችሮንም ያውቃል።"

በመሃሉ የናይጄሪያ ሴቶች ሊግ ፔሊካን ስታርስ ለተጫዋቾቹ ደመወዝ ካልከፈለ በሊጉ መጫወት አይችልም ሲል ወሰነ። ቢሆንም እስከዛሬ ድረስ ክለቡ ለተጫዋቾቹ ቤሳቤስቲን አልሰጠም።

ቺኔኔ ኦካፎር አንድ ቀን ወደ እግር ኳስ እመለሳለሁ የሚል ሕልም አላት።

በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል መቀመጫውን ካደረገው ክለብ ለቃ አሁን ቤተሰቦቿ ወደ ሚገኙበት ሌጎስ መጥታለች።

"አንድም ቀን ፀጉር ሥራ ላይ እሠማራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፤ ነገር ግን አሁን ምንም አማራጭ የለኝም። ቀስ በቀስ እየለመድኩት ነው። አንድ ቀን የራሴ የውበት ሳሎን ይኖረኝ ይሆናል።"

ይሁን እንጂ አሁንም ለሌሎች ክለቦች ለመጫወት የመሞከር ፍላጎት እንዳላት አትሸሽግም።

"አሁንም ከሥራ ስወጣ ልምምድ አደርጋለሁ። ራሴን ሁልጊዜም ብቁ ማድረግ እፈልጋለሁ። ሕልሜ ለብሔራዊ ቡድኑ መጫወት ነው። ሕልሜ አንድ ቀን እውን እንደሚሆን ደግሞ አልጠራጠርም። እግር ኳስ ደስታዬ ነው፤ ሕይወቴ ነው። ሁሉ ነገሬ ነው። መታገሌን እቀጥላለሁ።"