እግር ኳስ፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ መቼ ይመለሳል? በዝግ ስታድየም ወይስ...?

የፎቶው ባለመብት, STAFFORD ONDEGO
የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከተቋረጠ ወራት ተቆጥረዋል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሊጉ ክለቦች አዳዲስ ተጫዋቾች ማስፈረም፤ የነባር ተጫዎቻቸውን ውል ማራዘም ተያይዘዋል። ይህ ደግሞ ፕሪሚዬር ሊጉ ሊጀመር ይሆን የሚል ጥያቄ አጭሯል።
ለመሆኑ ፕሪሚዬር ሊጉ በቅርቡ ይመለሳል? ምላሹ አዎ ከሆነነስ በዝግ ሜዳ ወይስ በታዳሚ?
በኢትዮጵያ አግር ኳስ ፌዴሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ [ፈቃድ] ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቴድሮስ ፍራንኮ የእግር ኳስ ወድድሮች ወደ ሜዳ እንዲመለሱ ከመንግሥት ጋር እየተመካከርን ነው ይላሉ።
ዳይሬክተሩ፤ የክለቦች አስተዳዳሪው ኩባንያ ከጤና ሚኒስቴር ፈቃድ ካገኘ በኋላ ባሉት ሳምንታት [ከ6-8 ሳምንታት] ውስጥ ሊጉ ይጀመራል ይላሉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በዚህ ቀን ነው የሚጀመረው ብለን ቀን አልቆረጥንም ሲለ ያክላሉ።
ከክለቦች ምን ይጠበቃል?
«ክለቦች 'አሳይመንት' ወስደዋል። ያንን ልክ ሲጨርሱ የሚስማሙበት ነገር ካመጡ በኋላ ለጤና ሚኒስቴር እናቀርባለን። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፈቃድ ሲሰጠን ወደ ሥራ እንገባለን» ይላሉ አቶ ቴድሮስ።
ዳይሬክተሩ አክለው ክለቦች የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት የተጣለውን መመሪያ መከተል አለባቸው ይላሉ።
ክለቦች ጨዋታ ሲጀመር ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅድመ-ሁኔታዎች፡
- ተጨዋቾችና የክለቡ አባለት ከጨዋታ በፊት ከ48-72 ሰዓታት ባለው ጊዜ የተደረገ ምርመራ ውጤት ለአወዳዳሪው አካል ማቅረብ
- ከሜዳቸው ውጭ የሚጫወቱ ክለቦች የሚያርፉበት ሆቴል ይፈተሻል - የሆቴሉ ሠራተኞችም ይመረመራሉ
- የሚጠቀሙት አውቶብስ በእጥፍ መጨመር አለበት - አንድ አውቶብስ ላይ የሚሳፈሩ ሰዎች ቁጥር በግማሽ እንዲቀንስ
በዝግ ስታድየም ወይስ በታዳሚ?
አቶ ቴድሮስ፤ መንግሥት በዝግ ስታድየም ይሁን ወይስ ስለሚለው ጉዳይ እያዘጋጀ ያለው ስትራቴጂ (እቅድ) አለ ይላሉ። ነገር ግን ለጊዜው በይፋ የሚታወቀው ነገር ጨዋታዎቹ በዝግ ስታድየም እንደሚካሄዱ ነው ይላሉ።
«ጨዋታዎቹ በቴሌቪዥን እንዲሠራጩ በማድረግ ተመልካቾች የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን በቴሌቪዥን መስኮት እንዲከታተሉ ማስቻልና ክለቦች የቴሌቪዥን ገቢያቸውን በማሳደግ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ አስበናል።»
ከዚህ በተጨማሪ የሊጉ ጨዋታዎች በተወሰኑ ስታድየሞች እንደሚካሄዱ ዳይሬክተሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
«ጨዋታዎቹ የትኞቹ ስታድየሞች ላይ ነው የሚካሄዱት በሚለው ላይ እስካሁን ውሰኔ አላሰለፍንም። ሜዳዎቹን መርጠው ውሳኔ ማሳለፍ የሚችሉት አወዳዳሪ አካላት ናቸው። ግን ከተመረቱ በኋላ እንኳ የማሕበረሰብ ጤና መስፈርቱን ያላሟላ ስታድየም ጥቅም ላይ ላይውልም ይችላል።»
የዝውውር መስኮት...?
የፕሪሚዬር ሊጉ ክለቦች አዳዲስ ተጫዋቾች ማስፈረም፤ የነባር ተጫዎቻቸውን ውል ማራዘሙን ተያይዘውታል። ሲዳማ፣ ቡና፣ ሃዲያ ሆሳዕና፣ ሃዋሳና ባህርዳር የተጫዎቾችን ውል በማራዘም ከተጠመዱ ክለቦች መካከል ናቸው።
ፌዴሬሽኑ ግን እየተካሄዱ ያሉት ዝውውሮች እውቅና የሌላቸው ናቸው ይላል።
«ክለቦች ተጫዋቾችን እያስፈረሙ እንደሆነ ከመገናኛ ብዙኃን እንሰማለን። ነገር ግን የፌዴሬሽኑ የዝውውር መስኮት ገና አልተከፈተም። ሶስቱ አካላት [ፌዴሬሽን፣ ተጫዋችና ክለብ] የተፈራረሙት ውል ሲኖር ነው ሕጋዊ እውቅና ያለው የሚሆነው።»
አቶ ቴድሮስ አክለው ጨዋታ ይጀመራል የሚል ፈቃድ ሳይገኝ ክለቦች እንዲህ በፊርማ ሂደት ውስጥ መገኘታቸው ግራ የሚያጋባ ነገር ነው ይላሉ።
«የገንዘብ እጥረት አለብን እያሉ አሁን ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው ምንድነው የሚያመለክተው ስትል የሆነ ነገር እንዳለ ይነግርሃል።»
መጋቢት አጥቢያ ላይ የተቋረጠው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በኮሮናቫይረስ አማካይነት ነው የተቋረጠው ቢባልም ውሳኔው የሊጉ መሪዎች የነበሩት ፋሲል ከነማን ጨምሮ ሌሎች ክለቦችን አስቆጥቶ እንደነበር አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ለወትሮው ጥቅምትና ወር የሚጀመር ቢሆን የቀጣዩ ዓመት ወድድር መቼ እንደሚጀምር ቀን አልተቀመጠለትም።













