የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሰሞኑ ውጥንቅጥ መንስዔው ምን ይሆን?

የኢትዯጵያ ፕሪሚዬር ሊግ

የፎቶው ባለመብት, STAFFORD ONDEGO

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጓጊ የሆነ ይመስላል። በቅርቡ ሊጉን የተቀላቀሉት ፋሲል ከነማ እና መቀለ 70 እንደርታ ዋንጫውን ለማንሳት አንገት ለአንገት ተናንቀዋል። ይህ አጓጊነቱ ግን የፕሪሚዬር ሊጉን አስቀያሚ ገፀታ መሸፈን የቻለ አይመስልም።

አሁን አሁን በአዲስ አበባም ሆነ የክልል ስታደዬሞች ገብቶ ኳስ መታደም የራስን ደህንነት አደጋ ላይ ከመጣል ጋር ይነፃፀር ጀምሯል። ጨዋነት የጎደላቸው ደጋፊዎች፣ ከዳኛ ጋር ቡጢ የሚገጥሙ ተጨዋቾችና የቡድን አባላት፣ እንዲሁም ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ውሳኔዎች የሊጉ መገለጫ ከሆኑ ሰነባብተዋል።

እሁድ ግንቦት 25/2011 ከቀኑ 10 ሰዓት። ብርቅዬው የአዲስ አበባ ስታድዬም ኳስ እንዲጫወቱ ቀጠሮ በተያዘላቸው ኢትዮጵያ ቡና እና መቀለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ጩኸት ደምቋል።

ኳሱ ሊካሄድ 60 ደቂቃ ገደማ ሲቀረው ግን ጨዋታው እንደተሠረዘና ለማክሰኞ እንደተላለፈ በመነገሩ ደጋፊዎች ተበትነው ወደ የመጡበት እንዲሄዱ ሆነ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግነኙነት ኃላፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ጨዋታው እንዲሠረዝ የሆነው ከፌዴራል ፖሊስ በደረሰን ትዕዛዝ መሠረት ነው ይላሉ።

«መጀመሪያ ላይ 'ፕሪ ማች' ስብሰባ ነበር 4 ሰዓት ላይ። የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች የት የት እንደሚሆኑ ተነጋገርን። ፕሪ ማቹ ላይ ቡና ኃላፊነት መውሰድ እንቸገራለን የሚል አቋም እንፀባርቆ ነበር። [ከመቀለ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት የተፈጠረው ነገር መፍትሔ ባለማግኘቱ፤ አሁን ለሚፈጠረው ነገር 'ሪስኩን' አንወስድም] የሚል ነገር ነበር የተቀመጠው። ከዚያ የፀጥታ ኃይሎች በሁሉም አቅጣጫ እንዲከታተሉት ለማድረግ ተወሰነ።»

ከዚያስ?

«ከዚያ ጨዋታው ሊጀመር አካባቢ የነበረው 'ቫይብ' ሙሉ በሙሉ አስፈሪ ነበር። ምናልባትም የሰው ሕይወት ሊያልፍ ይችላል የሚል ስጋትም ነበር። ፌዴሬሽኑ ጨዋታው ለማድረግ ዝግጁ የነበረ ቢሆንም ከፀጥታ ኃይሎች በፍፁም የሚሆን አይደለም የሚል ሃሳብ መጣ። በዚህ ምክንያት ውድድሩ ተቋረጠ።»

ከዚያም ሰኞ ዕለተ ፌዴሬሽኑ ጨዋታው ማክሰኞ 'ለት በአዳማ አበበ ቢቂላ በዝግ እንዲካሄድ መወሰኑን አስታወቀ። ቀጥሎ ደግሞ ወደ ሐሙስ መዛወሩ ተሰማ።

«በዓሉ ዕሮብ ይሆናል ብለን ነበር ያሰብነው። አሁን በዓሉ ማክሰኞ ላይ በመዋሉ ወደ ሐሙስ ልናሻግረው ወስነናል።» ይላሉ አቶ ባሕሩ።

ይህ ውሳኔ ለቡና የሚዋጥ ሆኖ አልተገኘም። ውሳኔውን በተመለከተ ቅዋሜያቸውን የሚገልፅ መግለጫ የሰጡት የቡና ፕሬዝዳንት መ/አለቃ ፍቃደ ማሞም ቡና አዳማ ድርሽ እንደማይሄድ ተናገሩ።

«ደጋግሜ የምነግራችሁ ኢትዮጵያ ቡና ነገ ወደ አዳማ በመሄድ የሚያደርገው ጨዋታ እንደማይኖር ነው። ፌዴሬሽኑ ይህን ውሳኔያችንን የማይቀበል ከሆነ ለክለቡ ህልውና ስንል ጉዳዩን ወደ ፊፋ እና ካስ ይዘነው እንሄዳለን» ብለዋል ፕሬዝደንቱ።

ቡና ውሳኔውን በመቃወም ባወጣው መግለጫ ''በእኛ በኩል ምንም ችግር ሳይኖር ጨዋታ ተሠርዟል፣ በሜዳችን ልናደርገው የሚገባ ጨዋታ በገልለተኛ ሜዳ ሆኖብናል፣ መቐለ ላይ የደረሰብን በደል ሳያንስ አሁን ደግሞ ተጨማሪ ወጭ አውጥተን ወደ አዳማ እንድንሄድ መወሰኑ አግባብ አይደለም'' የሚሉ አንኳር ሃሳቦች አንስቷል።

አቶ ባህሩ ማንኛውም ቡድን የፌዴሬሽኑን ውሳኔ የመቃመው መብት ቢኖረውም ፌዴሬሽኑ የአንድን ጨዋታ ጊዜ እና ቦታ የማመቻቸት ኃላፊነት እንዳለበት ያስታውሳሉ።

የመቀለ 70 እንደርታ ሥራ አስከያጅ አቶ ሽፈራው ተክለሃይማኖት እሁድ ያጋጠመው ችግር ቀድሞውንም ሊከሰት እንደሚችል ይታወቅ ነበር ይላሉ።

«የቡና ደጋፊዎች ማህበርም ችግር ሊያጋጠም ስለሚችል 'ኃላፊነት መውሰድ አልችልም' በሚል ለፌደሬሽኑ በደብዳቤ አሳውቆ ነበር። እኛም በበኩላችን ማሕበሩ በደብዳቤ ከገለጸው ስጋትና እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ጨዋታው ባይቀየር እንኳ በዝግ ሜዳ እንዲካሄድ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለፌደሬሽኑ ጽፈናል።»

አቶ ሽፈራው አክለው «ቀን 8 ሰዓት ላይ ስልክ ተደውሎ 'ወደ ሜዳ እንዳትመጡ' የሚል መልዕክት ደረሰን። የቡድናችን ደጋፊዎችም በሥርዓቱ ከሜዳ እንዲወጡ ተደረገ። ግጭቱ በፖሊስና በቡና ደጋፊዎች መካከል ስለነበረ በደጋፊዎቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት የለም» ይላሉ።

የተራዘመው ጨዋታ ለሐሙስ ከሰዓት ቀጠሮ ተይዞለታል። ኢትዮጵያ ቡና አሁንም በአቋሙ እንደፀና ነው። መቀለ 70 እንደርታ ግን አዳማ ገብቶ ዝግጅት እያዳረገ እንደሚገኝ አቶ ባህሩ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ቡና ለጨዋታው ወደ አዳማ የማያቀና ከሆነ የጨዋታው 3 ነጥብ በፎርፌ ለመቀለ ሊሰጥ እንደሚችል ግምት አለ። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ግን እሱን ጊዜው ሲደርስ እናየዋለን፤ በፕሪሚዬር ሊጉ ደንብ መሠረት ውሳኔው የሚተላለፍ ይሆናል ይላሉ።

የፕሪሚዬር ሊጉን ደረጃ እየመራ የሚገኘው ፋሲል የቡናና መቀለ ጨዋታ በዝግ ስታድዮም እንዲከናወን መወሰኑ አግባብ አይደለም የሚል መግለጫ አውጥቷል፤ ምንም እንኳ አቶ ሽፈራው ''በማይመለከት ጉዳይ እጅ እንደማስገባት ይቆጠራል'' በማለት ቢያጣጥሉትም።

የቡና እና መቀለ ጉዳይ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን አስቀያሚ ገፅታ አጉልቶ ያውጣው እንጂ ሌሎች ችላ ላይባሉ የሚገባቸው ጉዳዮች የኢትዮጵያን እግር ኳስ እግር ተወርች ወጥረው ይዘውታል።

ያለንበት ጊዜ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፈታኙ ወቅት ይሆን ወይ? «አይደለም!» ይላሉ አቶ ባህሩ። ፌዴሬሽኑ ግን ከወቀሳ አልዳነም። የኢትዮጵያ እግር ኳስም ከዓመት ዓመት አንድ ወደ ኋላ እንጂ ወደፊት እየሄደ አይመስልም።