በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወተውን ኮከቧን የማታውቀው አገር

የፎቶው ባለመብት, Onel Hernandez
ኩባ በዓለማችን የኮሚዩኒዝም ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ካልተወደገባቸው ጥቂት አገራት አንዷ ናት።
የኩባ ዜጎች ቀሪው ዓለም በስፋት የሚተቀምባቸውን መረጃና የግንኑነት ዘዴዎች በቀላሉ ኤኣገኙም። በዚህም በይነ መረብ እንደልብ ማግኘት አይታሰብም።
ቢሆንም አንድ እናት ግን ይህ አላገዳትም፤ በአንድ ዶላር የገዛችውን ካርድ ፍቃ ወደ ጉግል በመክፈት በመፈለጊያው ሳጥን ውስጥ 'ኦኔል ኸርናንዴዝ' ስትል ትተይባለች።
በፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ የመጀመሪያው ኩባዊ የሆነው ተጫዋች እናት እንዲህ ነው ስለልጇ ሁኔታ የምታጣራው።
የ27 ዓመቱ የኖርዊች ቡድን የክንፍ መስመር ተጫዋች ኸርናንዴዝ የተወለደው በኩባዋ ሞሮን ከተማ ውስጥ ነው። ከተማዋ 'ፌርማታ'ናት። ሰዎች ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ሲያቀኑ አረፍ የሚሉባትና ሻይ ቡና የሚቀማምሱባት።
ኸርናንዴዝም እትብቱን በቀበረባት ከተማ ብዙም መቆየት አልሻተም። ገና በስድስት ዓመቱ ነበር ይህችን ከተማ ጥሎ የወጣው።
እናቱ አንድ ጀርመናዊ ቱሪስት ተዋወቀች። ከዓመት በኋላ ጋብቻ ፈጽማ ልጆቿን ኩባ ውስጥ በመተው ወደ ጀርመን አቀናች። በኀወላም ከሁለት ዓመት በኋላ ኸርናንዴዝና እህት ወንድሞቹም ወደ ጀርመን ሄዱ። ይህ ውሳኔ የ21 ዓመቷን እናትና የስድስት ዓመቱን ኸርናንዴዝ ሕይወት ቀየረ።
የኸርናንዴዝ እንጀራ አባት የእግር ኳስ አሰልጣኝ ነበር። አንድ የሕፃናት ቡድን የተቀላቀለው በእናቱ የስፓኒስ ቁጣና ጩኸት እየታገዘ ኸርናንዴዝ ኳስ እየገፋ በክንፍ በኩል መብረሩን ቀጠለ።
በአውሮፓውያኑ 2010 የ17 ዓመቱ ኸርናንዴዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ጉዞውን 'ሀ' ብሎ ጀመረ። ለጀርመን ከ18 ዓመት በታች ቡድንም መመረጥ ቻለ።
የቀድሞው የባየርን ሚዩኒክ እና የሊቨርፑል ተከላካይ የነበሩት ክርስትያን ዚግ ታዳጊውን ኦኔልን አሰልጥነውታል። "ኦኔል ወጣት እያለ ጠንካራ ሠራተኛ ነበር" ይላሉ።
ኦኔል ኸርናንዴዝ ከጀርመኑ ኢንትራክት ብሮንሽዌግ በ2.5 ሚሊዮን ዩሮ ኖርዊችን የተቀላቀለው በመስከረም ወር በ2018 ነበር።
ኦኔል ለእንግሊዝኛ ባዕድ ነበር። ነገር ግን ልክ በልጅነቱ ከስፔንኛ ወደ ጀርመንኛ እንደተሸጋገረው ሁሉ እንግሊዝኛን መሽምደድ ያዘ።
በመጀመሪያው ዓመት ብቻ 8 ጎሎችን አስቆጠረ፤ 10 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀበለ። የቻምፒዮንሺፑ ክለብ ኖርዊች፤ በኦኔልና በቡድን አጋሮቹ ታግዞ ጉዞ ሽቅብ ወደ ፕሪሚዬር ሊግ አደረገ።
ኦኔል ኸርናንዴዝ ኖርዊች ከሊቨርፑል ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሮ ሲገባ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ኳስ የነካ የመጀመሪያው ኩባዊ ሆነ። ነገር ግን ኩባውያን ስለ ኮከቡ የሚያውቁት እምብዛም ነው።

የፎቶው ባለመብት, GARY
እናቱ፤ ኸርናንዴዝ ከልጅነቱ ጀምሮ ለኩባ ብሔራዊ ቡድን መጫወት ይሻ እንደነበር ትናገራለች። እናቱ የኦኔል ወኪል በመሆኗ ከኩባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ትወያያለች።
"ወደ ሃቫና ሄጄ ብዙ ጊዜ ስብሰባ አድርጊያለሁ፤ እስካሁን ድረስ ለምን ለብሔራዊ ቡድን እንዳልመረጡት ግን አይገባኝም።"
ኩባ ውስጥ ያሉ የስፖርት አፍቃሪዎች ስለ ኸርናንዴዝ ሰምተው አያውቁም።
ኩባዊው ኦስካልዶ ሱዋሬዝ ሊቨርፑል ከናርዊች ሲጫወት ተመልክቷል። ጨዋታ አድማቂዎቹ ተንታኞች ኸርናንዴዝ ፕሪሚዬር ሊግ የተጫወተ የመጀመሪያው ኩባዊ ነው ሲሉም ሰምቷል።
"ከዚያ በኋላ ግን አላየሁትም። ለትላልዎቹ ክለቦች ቢጫወት ኖር እናውቀው ነበር። እዚህ በይነ-መረብ ውድ ስለሆነ ዜና ከራድዮ እንጂ ከጉግል አይደለም የምናገኘው" ይላል።
"ለትልቅ ሊግ መጫወቱ ያስደስተኛል። ነገር ግን ኩባ ውስጥ ኔይማርና ሜሲ እንጂ እሱ ብዙም አይታወቅም" ይላል ኦስካልዶ ሱዋሬዝ።
ኸርናንዴዝ፤ እንኳን በኩባ ዋና ከተማዋ ሃቫና ይቅርና በትውልድ ስፍራው ሞሮንም ብዙም ታዋቂ አይደለም።
"ችግሩ ኩባ ውስጥ እግር ኳስ ይህን ያህል ተወዳጅ ስፖርት አይደለም። ነገር ግን እግር ኳስ የሚመለከቱ ሰዎች ልጄን እንደሚያውቁት እርግጠኛ ነኝ" ትላለች እናቱ።
ምንም እንኳ ኩባ ውስጥ ቡጢ እና ቤዝቦል ታዋቂ ቢሆኑም የእግር ኳስ አሰልጣኞች ስለኸርናንዴዝ ኦኔል መረጃው አላቸው። ሕፃናትን የሚያሰልጥነው ሉዊስ ኤንሪኬም ኳስ የሚወዱ ሰዎች ያውቁታል ይላል።
ኩባ፤ በ1938 የዓለም ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ነበረች። በውድድሩ ላይ ሮማኒያን መርታት ብትችልም በስዊድን 8 ለምንም ተሸንፋች።
የቀድሞው የኩባ ፕሬዝደንት ፊደል ካስትሮ የአርሰናል ደጋፊ ነበሩ የሚል ወሬ በሃቫና ጎዳናዎች ላይ ይሰማል። ነገር ግን ፕሬዝደንቱ ከክለቡ ስም እንጂ ለኳስ ይህን ያህል ፍቅር የላቸውምም ይባላል።
ኩባ ለእግር ኳስ ባትንገበገብም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እግር ኳስ እንደ አንድ መዝናኛ ይቆጠር ይዟል። ቡድኑ ኖርዊች ከፕሪሚዬር ሊግ እንዳይወርድ እየታገለ ያለው ኸርናንዴዝም አንድ ቀን በአገሩ ሰዎች ዘንድ በደንብ ታውቆ ይከበር ይሆናል።
















