ኢትዮጵያ ከግብፅ ለቀጣዩ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረግ ፍልሚያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ በአይቮሪ ኮስት አስተናጋጅነት በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ይካሄዳል።
ለዚህ የአፍሪካ አንጋፋው የእግር ኳስ ውድድር ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚያደርጉ ቡድኖች በምድብ ተደልድለዋል።
48 ሃገራት በ12 ምድብ ተከፋፍለው ፍልሚያ ካደረጉ በኋላ ከየምድቡ 2 ቁንጮ ሃገራት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።
ኢትዮጵያ በምድብ መ ከማላዊ፣ ጊኒ እና ግብፅ ተደልድላለች።
በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙ ሶስቱም ሃገራት ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የነበሩ ናቸው።
ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ጊኒ እና ማላዊ ከምድባቸው ሲያልፉ ግብፅ ደግሞ ለፍፃሜ ደርሳ መረታቷ ይታወሳል።
ይህ ምድብ ለኢትዮጵያ ቀላል ወይስ ከባድ የሚባል ነው?
"ከዚህ በፊት ከነበረው ይሄኛው ትንሽ ከበድ ያለ ይመስላል" ይላል የእግር ኳስ ተንታኙ ፍሬው አሥራት።
"ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ብቻ ናት ከምድቧ ያላለፈችው። ጊኒም ማላዊም ጠንካራ ነበሩ። ግብፅ ደግሞ ለፍፃሜ ደርሳለች" ሲል ሃገራቱ ያሉበትን አቋም ያስታውሳል።
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ላለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ካደረገቻቸው ጨዋታዎች አይቮሪ ኮስትን በሜዳዋ የረታችበት የሚዘነጋ አይደለም።
ከሶስቱ የምድቡ ሃገራት ለኢትዮጵያ ማን ይከብድ ይሆን?
"ግብፅ ያለችበት ወቅታዊ አቋም ጥሩ ነው። አልፎም ታሪካዊ ይዘትም ስላለው ኢትዮጵያ ከግብፅ የሚያደርጉት ፍልሚያ ከበድ ያለ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ" ይላል ፍሬው።
ኢትዮጵያ ከግብፅ በስተቀር ከጊኒም ሆነ ማላዊ በቅርብ ዓመታት ተፋልማለች።
"ጊኒና ማላዊ ቀላል ይሆናሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አይቮሪ ኮስትን መርታታችንን አንርሳ። እኛም የዋዛ እንሆናለን ብዬ አልገምትም።"
ዋሊያዎቹ
በበርካታ ወጣት ተጫዋቾችና በጥቂት ነባር አባላት የታጀቡት ዋሊያዎቹ ካሜሩን ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈው ከተመለሱ ጥቂት ወራት አስቆጥረዋል።
አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን ብዙ ልምድ የቀሰምንበት ውድድር ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ይህ የብሔራዊ ቡድን ውቅር ከበድ ያሉ ጨዋታዎችን የመቋቋም አቅም አለው ወይ ሲሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ።
"ብሔራዊ ቡድን ሽግግር ያለ ይመስለኛል" ይላል ፍሬው።
"እነ ጌታነህ፣ ሽመልስ፣ አስቻለው. . . ያሉ ነባር ተጫዋቾች አሉ። ደግሞ ከታች ብቅ ብቅ እያሉ ያሉ አዳዲስ ልጆች ደግሞ አሉ
አሁን ያለንበት ጊዜ የሽግግር ጊዜ ይመስለኛል። አዳዲሶቹ ልጆች አቅማቸውን አሳይተው አዲሱን ብሔራዊ ቡድን መቀላቀል ይችላሉ። ወሳኝ ጊዜ ላይ ነን ብዬ ነው የማምነው።"
አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ ኮሞሮስ አቅንተው ባደረጉት የወዳጅነት ፍልሚያ በወጣቶች የታጀበ ቡድን ይዘው ነው ያቀኑት።
"ብሔራዊ ቡድኑ በሊጉ ጥሩ በቃት ያሳዩ ተጫዋቾች ጎልተው የሚታዩበት ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ። ነገር ግን ጨዋታዎቹ ጠንከር የሚሉ ስለሆነ ነባር የሚባሉ አሁንም ጥሩ አቋም ያላቸው ልናይ እንችላለን።"
የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በፈረንጆቹ ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 14 ባለው ጊዜ ይጀመራሉ።
በዚህ ጊዜ ሃገራት ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ያደርጋሉ።
የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪው ካፍ ማን ከማን እንደሚፋለምና እንዲሁም ቀንና ቦታ በቅርቡ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ በአይቮሪ ኮስት አስተናጋጅነት በቀጣዩ ዓመት በወርሃ ሰኔና ሐምሌ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።












