ኢትዮጵያ ለመጀመር ያቀደችው ‘ስቶክ ማርኬት’ ምን ይዞ ይመጣል?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ የስቶክ ማርኬት ማስጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል።
‘ኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ’ (ESX) የተሰኘውን የአክሲዮን ገበያ በኢትዮጵያ ለማስጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የተፈረመው በኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በኤፍኤስዲ አፍሪካ መካከል ነው።
ስቶክ ገበያ ምንድነው?
አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የፌርፋክስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ሊቀ መንበር ናቸው። የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችም በቅርበት ይከታተላሉ።
ለስቶክ ማርኬት ‘የድርሻ ገበያ’ የሚል አቻ የአማርኛ ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን ይላሉ።
ኩባንያዎች የኩባንያውን የባለቤትነት ድርሻ ለገበያ ያቀርባሉ። ሰዎችም ይህን ድርሻ ከገዙ በኋላ ኩባንያው ትርፋማ በሆነ መጠን ያላቸውን ድርሻ መልሰው በመሸጥ ወይም ከትርፍ ክፍፍል ትርፋማ የሚያደርግ አሠራር ነው።
ስቶክ ማርኬት ለኢትዮጵያ ምን ይዞ ይመጣል?
አቶ ዘመዴነህ ኢትዮጵያ የስቶክ ገበያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ብትሆነም የስቶክ ገበያ ጽንሰ ሐሳብ ለአገሪቱ ገበያ አዲስ አይደለም ይላሉ።
በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ጥምረት የሚቋቋመው የስቶክ ገበያ በዋናነት የሚከተሉትን ጥቅሞች ለኢትዮጵያ ይዞ እንደሚመጣ ይገልጻሉ።
1. የካፒታል ገበያ
በርካታ የአገር ውስጥ ባንክ እና ኢንሹራንሶች ሲመሠረቱ እና ከምሥረታቸውም በኋላ የአክሲዮን ድርሻዎችን ሲሸጡ መቆየታቸውን በማስታወስ፤ የስቶክ ገበያን ከዚህ የተለየ የሚያደርገው፤ ይፋዊ በሆነ መልኩ ተደራጅቶ ቁጥጥር እየተገደረገበት በግልጽ መገበያየት ማስቻሉ ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ (ኢኤስኤክስ) እውን ሲሆን፤ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ሲቋቋሙም ሆነ ማስፋፋት ሲፈልጉ አክሲዮኖቻቸውን ለመሸጥ ይከተሉት የነበረውን ረዥም መንገድ እንደሚያሳጥርላቸው ያክላሉ።
“እነዚህ ኩባንያዎች ሲቋቋሙ ስቶክ ኤክስቼንጅ ስላልነበረ በጣም ረዥም ሂደት በማለፍ ለእያንዳንዱ ሰው እየዞሩ ነው ሼር የሚሸጡት። ይህ ረዥም ጊዜ እና ገንዘብ ይወስዳል። አዋጭም አይደለም” ይላሉ ዘመዴነህ።
የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ መመሥረት አንዱ ጥቅም አዲስ ለመሚሠረቱም ሆነ ለነባር ኩባንያዎች የካፒታል ገበያን መፍጠሩ ነው ይላሉ።
ካፒታል ማሰባሰብ ለሚፈልጉም ስቶክ ገበያ መልካም አማራጭ እንደሆነ አቶ ዘመዴነህ ያስረዳሉ።
“ጥሩ ሐሳብ ኖሯቸው የካፒታል እጥረት ላለባቸው ሰዎች ይጠቅማል። ዛሬ ላይ ከባንክ ብድር ማግኘትም ቀላል አይለደም። ለዘመድ ወይም ለጓደኛ ሼር የመሸጥ ሂደት ቀላል አይደለም። ስቶክ ማርኬት አዲስ ለሆኑም ይሁን መስፋፋት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች የካፒታል ገበያን ይፈጥራል።”
2. ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል
የስቶክ ገበያ፣ ፍትሐዊ እና ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ ሀብት ማከፋፈል የሚችል ሥርዓት እንደሆነ አቶ ዘመዴነህ ይገልጻሉ።
በአሁኑ ጊዜ ግዙፍ መንግሥታዊ ኩባንያዎች ወደ ግሉ ዘርፍ እየተሸጋገሩ እንደሆነ በማስታወስ፣ እነዚህ ከመንግሥት ወደ ግሉ የሚዘዋወሩት ግዙፍ ኩባንያዎችን ሲገዙ የቆዩት ጥቂት ግለሰቦች እና ኮርፖሬሽኖች መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ኢኤስኤክስ ሲመጣ ግን መንግሥት የሕዝብን ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማከፋፈል ይችላል።
“ስቶክ ማርኬት ላይ አንድ ሼር በአምስትም፣ በአሥርም ዶላር ሲሸጥ ሁሉም የየአቅሙን በመግዛት ኢትዮጵያ ያካበተችውን ሀብት ማከፋፈል ይቻላል” ሲሉ ያብራራሉ።
እነዚህ ወደ ግሉ ዘርፍ የሚዘዋወሩ ኩባንያዎች ወደ ስቶክ ገበያው ሲገቡ፣ ሁሉም የአቅሙን ያህል ባለቤት እንደሚሆንና ይህም የሀብት ክፍፍልን እንደሚያመጣ ያክላሉ።
3. ቁጠባ እና የኢንቨስትመንት አማራጭን ማስፋት
የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ እውን ሲሆን የቁጠባ ባህልን ከፍ እንደሚያደርግ አቶ ዘመዴነህ ይናገራሉ።
ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ኪሳራ አያስከትልም ብለው በሚያስቡት ዘርፍ ላይ ብቻ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ።
“ገንዘብ ያላቸው ሰዎች የቤት ልማት ላይ ብቻ ትኩረት ሲያደርጉ ይታያል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ደግሞ ተጎድቷል። ይህም ኢንቨስት የሚደረግባቸው ዘርፎችን ውስን በማድረግ የቁጠባ አለመመጣጠን ይፈጥራል። ስቶክ ማርኬቱ ግን ውጤታማ በሆነ መንገድ ካፒታል በሁሉም ዘርፎች ላይ ማሰራጨት ያስችላል” በማለት ያስረዳሉ።
4. ግልጽነት
ሌላኛው መልካም አጋጣሚ የድርሻ ገበያዎችን በቀላሉ፣ ግልጸኝነት በሰፈነበት መልኩ መግዛት እና መሸጥ ማስቻሉ ነው።
ምን ያህል ሼር በምን ያህል ዋጋ ለገበያ እንደቀረበ ግልጽ ነው።
“ሰዎች ስልካቸው ላይ በሚጭኑት መተግበሪያ በቀላሉ የገበያ ድርሻዎችን መግዛት እና የገዙትንም መሸጥ ይችላሉ” ይላሉ አቶ ዘመዴነህ።
የባንክ ባለ አክሲዮኖች ዓመት ጠብቀው ትርፍ ከመከፋፈል ውጪ በቀላሉ ያላቸውን አክሲዮን መሸጥ አይቻላቸውም።
ኢኤስኤክስ እውን ሲሆን ግን በቀላሉ አክሲዮን የመሸጥ ዕድል ይዘረጋል።
የኢትዮጵያን ስቶክ ገበያ የትኞቹ ኩባንያዎች ሊቀላቀሉ ይችላሉ?
ከበርካታ አሥርት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኬንያው ‘ናይሮቢ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ’ ወደ 60 ገደማ የአገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎችን ይዟል።
አቶ ዘመዴነህ የኢትዮጵያው ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ50 ያላነሱ ኩባንያዎችን በውስጡ ይይዛል የሚል ተስፋ አላቸው።
እሳቸው እንደሚሉት፣ የስቶክ ገበያውን ሊቀላቀሉ የሚችሉ ኩባንያዎችን ስናስብ በብሔራዊ ባንክ ጠንካራ ቁጥጥር የሚደርግባቸውን 18 ባንኮች እና ከ18 የማያንሱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መዘንጋት የለብንም ይላሉ።
“ሁሉም የስቶክ ገበያውን ላይቀላቀሉ ይችላሉ። . . . ቁጥሩን 30 ብለን እንያዘው። 20ው ከየት ይመጣል? ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ባለቤትነታቸው በቤተሰብ ደረጃ የሆነ ግዙፍ ኩባንያዎች ስቶክ ማርኬት ላይ ለመግባት ዝግጁ የሆኑ ይኖራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሆኑ የውጭ ኩባንያዎች አሉ። ኮካ ኮላ፣ ሃይኒከን፣ ዩኒሊቨር እና ቶታልን ማንሳት ይቻላል። የእኔ ግምት ከ40 አስከ 70 ነው” በማለት ሐሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ይህ ማለት ግን ሁሉም ኩባንያዎች በአንድ ቀን ይገባሉ ማለት አይደለም። ቁጥራቸው በጊዜ ሂደት የሚጨምር ይሆናል።
በስቶክ ገበያ ትርፍ እና ኪሳራ እንዴት ያጋጥማል?
ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ስቶክ ገበያ ምንድን ነው? እንዴትስ መሸጥ እና መለወጥ ይቻላል? የሚለውን እንመልከት።
ስቶክ ገበያን በቀላል ቋንቋ ለመረዳት የምጣሄ ሀብት ባለሙያዎች አዘወትረው የሚጠቀሙትን ቀላል ምሳሌ እንውሰድ።
'ሀ'፣ 'ለ' እና 'ሐ' የሚባሉ ሦስት ምናባዊ የሞባይል ስልክ አምራች ኩባንያዎችን አሉ አንበል።
እርስዎ 6 ዶላር አውጥተው ከእያንዳንዱ ኩባንያ የሁለት ዶላር የገበያ ድርሻ ይገዛሉ።
'ሀ' ለገበያ ያቀረበው ሞባይል ስልክ ባትሪው እየፈነዳ ሰዎችን ለጉዳት እየዳረገ መሆኑን የሚያመለክት ሪፖርት መውጣት ይጀምራል።
የ'ለ' ኩባንያ የሆነው ምርት ደግሞ ባትሪው በፍጥነት እያለቀ ከተጠቃሚዎች ቅሬታ ይደርሰዋል።
የ'ሐ' ምርት የሆነው ሞባይል ስልክ ግን በአግባቡ ይሠራል።
ይህ በገበያ ላይ ያጋጠመው ክስተት በሦስቱ ኩባንያዎች ስቶክ ገበያ ዋጋ ላይ ለውጥ ያመጣል።
የአንድ ኩባንያ ምርት ጥራት ሲወርድ የዚያ ኩባንያ ፈላጊዎች ይቀንሳሉ።
በተቀራኒው አንድ ኩባንያ ትርፍማ የሚያደርገውን ውሳኔ ወስኖ ትርፍ ሲያጋብስ፣ የትርፉ ተቋዳሽ መሆን የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከፍ ይላል።
በዚህ መሠረት ባትሪው እየፈነዳ ሰዎችን ለአደጋ እያጋለጠ ያለው የሞባይል ኩባንያ ድርሻ በከፍተኛ መጠን ሊወርድ ይችላል።
በሁለት ዶላር የገዙትን ድርሻ መልሰው መሸጥ ቢፈልጉ ከግማሸ ባነሰ ዋጋ እንኳን የሚገዛዎትን ላያገኙ ይችላሉ። ይህ ሞባይል አምራች ኩባንያ ሲከስር እርስዎም የኩባንያው ባለድርሻ እንደመሆንዎ ኪሳራ ያጋጥምዎታል።
ስለዚህ በኩባንያ 'ሀ' ላይ ያደረጉት ኢንቨስትመንት ኪሳራን ያስከትላል።
የ 'ሐ' ምርት የሆነው ስልክ ግን በገበያ ተፈላጊነቱ ሲጨምር የኩባንያው ዋጋም ከፍ ይላል።
ምናልባት በሁለት ዶላር የገዙትን የኩባንያውን ድርሻ፣ አሁን ላይ በ4 ዶላር ሸጠው ትርፍ ሊያገኙ ይችላሉ።












