ፑቲን፣ ‘ምዕራቡ ዓለም ያለኛ የኃይል አቅርቦት ብዙም አይዘልቅም’

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ምዕራቡ ዓለም የለ አገራቸው የኃይል አቅርቦት ብዙም አይዘልቅም ሲሉ ተናገሩ።
ፑቲን ይህን ያሉት የአሜሪካ ባለሥልጣናት የሩሲያ ነዳጅና ጋዝ አቅራቢ ኩባንያዎችና አገሪቱ ማዕቀብ ከተጣለባት በኋላ የበለጠ አትራፊ እየሆኑ መምጣታቸውን ባመኑ ማግስት ነው።
የአውሮጳ ኅብረት አሁን ላይ 40 ከመቶ የሚሆነውን የጋዝ ፍላጎቱን የሚያሟላው ከሩሲያ ነው።
ኅብረቱ ከሩሲያ የኃይል ጥገኝነት ራሱን ለማውጣት እያደረገ ባለው ከፍተኛ ተጋድሎ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ 90 ከመቶ ከሩሲያ የሚገባን ኃይል ለማስወገድ እየሠራ ነው። ይሁንና ይህን ዕቅዱን በነዳጅ ላይ እንጂ በጋዝ ላይ ሊያሳካ እንደማይችል ከወዲሁ ተረድቶታል።
አሜሪካ በሁሉም የሩሲያ የኃይል አቅርቦቶች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ይህ ማዕቀብ ሞስኮ ኪዬቭን በመውረሯ የተጣለ ነው።
ይሁንና የነዳጅና ጋዝ ዋጋ በዓለም ገበያ መመንደግ የሩሲያ ትርፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአያሌው ጨምሯል ማለት ነው።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከወጣት ባለሃብቶችና የኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር በነበራቸው ውይይት እንደተናገሩት “በዓለም የጋዝና የነዳጅ አቅርቦት ምርት ቀነሰ ማለት ዋጋው ተመነደገ ማለት ነው" ሲሉ ከማዕቀቡ ወዲህ ገቢ እንዴት ሊጭምር እንደቻለ አስረድተዋል።
ይህ የፑቲን ሐሳብ በአሜሪካ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣንም የተረጋገጠ ነበር።
ትናንት ሐሙስ የአሜሪካ የኃይልና ተያያዥ ጉዳዮች ከፍተኛ ልዑክ የሆኑት አሞስ ሆሽቴይን ሴኔት ቀርበው በነበረ ጊዜ በሕዝብ እንደራሴዎች ዘንድ አንድ ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር።
ይኸውም በዓለም የነዳጅ አቅርቦት በመቀነሱ ሩሲያ ትርፏ ጨምሯል ወይ ተብለው ሲጠየቁ “ይህ የምክደው ጉዳይ አይደለም’ ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከወጣት ባለሃብቶች ጋር የነበራቸው ውይይት 350ኛውን የሩሲያ አጼ ታላቁ ፒተርን ልደትን በማስመልከት በተዘጋጀ አውደ ርዕይ ተገኝተው በነበረ ጊዜ ነው።
ይህ የ18ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ከስዊድን ጋር ጦርነት የገጠመ ሲሆን ይህም ፑቲን ነገሩን ከዩክሬን ወረራ ጋር ለማስተሳሰር ዕድል ሰጥቷቸዋል።
“አጼ ፒተር ከስዊድን ጋር ባደረገው ጦርነት አንዳች ግዛት የወሰደ ይመስላችኋል፤ አስመለሰ እንጂ አልወሰደም’ ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም፥ ‘ዛሬም ቢሆን የኛ የሆነውን መመለስና መጠናከር ነው የሚኖርብን’ ብለዋል።












