በአፋር ክልል በምግብ እጥረት ተጎድው ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ህፃናት ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፋር ክልል በምግብ እጥረት ምክንያት ተጎድተው ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ህጻናት ቁጥር መጨመሩ ተገለፀ።
የዱብቲ ጀኔራል ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሁሴን አደም ቀደም ብሎ ወደ ሆስፒታሉ በምግብ እጥረት ተጎድተው ይገቡ የነበሩ ህጻናት ቁጥር ከሰሞኑ በሦስት እጥፍ መጨመሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአንድ ወር በፊት በነበረው ሁኔታ በምግብ እጥረት ተጎድተው የሚመጡ ህፃናት በሳምንት አምስት ያህል የሚደርስ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት እስከ ሶስት እጥፍ መጨመሩን ያስረዳሉ።
አብዛኞቹ ህፃናትም የተፈናቀሉ ሲሆኑ በምግብ እጥረትም ተጎድተውና ለተለያዩ በሽታዎችም ተጋልጠው ሆስፒታል እንደሚደርሱ ይናገራሉ።
አብዛኛውን ጊዜ በሳንባ ምች፣ በተቅማጥና በሌሎች በሽታዎች ተይዘው እንዲሁም የሰውነታቸውም ኃይል በከፍተኛ ሁኔታም በደከመበት ሁኔታ ነው ወደ ሆስፒታሉ እየመጡ ያሉት።
ለምግብ እጥረት በተጋለጡ ህፃናትና በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ በሚገቡ ግለሰቦች ምክንያትም ሆስፒታሉ መጨናነቁንና እንዲሁም የአልጋና የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት ማጋጠሙንም ስራ አስኪያጁ ያስራዳሉ።
በሰሜን በኩል ኪልበትረሱ ባለው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ቁስለኛ ታካሚ በመኖሩ ከፍተኛ ችግሮች ገጥመዋል። ዶክተር ሁሴን እንደሚሉት ቀድሞውኑም ሆስፒታሉ የራሱ ክፍተቶች የነበሩበት ሲሆን አሁን በጦርነቱ ምክንያት የነበሩ ችግሮች መባባሳቸውን እንዲሁም አዳዲስ ተግዳሮች ገጥመውታል።
ታካሚዎች የሚቆዩበት ቦታ ለሌሎች አገልግሎቶች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቦታዎችን በጦርነቱ ለቆሰሉ ታካሚዎች ማዋልና የጤና ባለሙያዎችን ማሰማራት እንዲሁም ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን ያቆሙበት ወቅትም እንደነበር አስረድተዋል።
ሆስፒታሉ ይሰጠው የነበረውን የእናቶችና ህፃናት ህክምና በተለይም የማዋለድ አገልግሎት የጤና ባለሙያና የህክምና እቃ በመላክ በአካባቢው ወደሚገኙ የጤና ጣቢያ እየሰጡ ነበር። ድንገተኛ ያልሆኑ የህክምና አገልግሎቶችንም ለማቋረጥ ተገድደው እንደነበር ገልጸዋል።
በአሁኑም ወቅት ይህ ሁኔታ በተወሰነ መልኩ እንዳለና በስብሰባ አዳራሽና ቤተ መፃህፍት አልጋ በማፈላለግ የህክምና አገልግሎትንም ይሰጡ እንደነበር ገልጸዋል። አብዛኛው ቁስለኛም ሲቪል ዜጎች እንደሆኑም የሚናገሩት ዶክተር ሁሴን በከባድ መሳሪያ በደረሰ ድብደባ ምክንያት በተነሳ ቃጠሎ ሙሉ ሰውነታቸው የተቃጠለ ህፃናት ይገኙበታል ብለዋል።
አንዳንድ የሰውነት ክፍላቸውን፣ እጃቸውንና እግራቸውን ያጡም እንደሚገኙበት አስረድተዋል። በፍንዳታም እንዲሁም በከባድ መሳሪያ የተጎዱ አዛውንትም ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በጦርነቱ ወቅት የተጎዱ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር በአምስት ቀናት ውስጥ እስከ መቶ የሚሆኑ ታካሚዎች ያስተናግዱ እንደነበረና በአንድ ወር ውስጥም እስከ 900 የሚደርሱ ቁስለኞችን ያከሙበት ወቅት እንደነበርም አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።
አስራ ሰባት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሃት ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ያወጁ ሲሆን ይህም ለሰላም በር ሊከፈትና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት ወደሚያስችል ውይይት እንደሚችል ተስፋ ያደርጋሉ።












