ኮንሰርቱን የሰረዘው ጀስቲን ቢበር ፊቱ ፓራላይዝድ እንደሆነ ተናገረ

የፎቶው ባለመብት, INSTAGRAM/JUSTIN BIEBER
ባለፈው ሳምንት ሊያካሂድ የነበረውን ኮንሰርት የሰረዘው የ28 ዓመቱ ድምጻዊ ጀስቲን ቢበር፣ ከፊል ፊቱ ፓራላይዝድ እንደሆነ ተናግሯል።
ኢንስታግራም ላይ በለቀቀው ቪድዮ “እንደምታዩት ይህኛው ዓይኔ አልገለጥ ብሏል። በዚህኛው የፊቴ ክፍል ፈገግ ማለት አልችልም። ያኛው የፊቴ ክፍል ደግሞ ሙሉ በሙሉ ፓራላይዝድ ሆኗል” ብሏል።
ድምጻዊው የገጠመው ራምዚ ሀንት የተባለ ሕመም ነው።
ሕመሙ ጆሮ አቅራቢያ የሚገኙ የፊት ነርቮችን ያጠቃል።
‘ጀስቲስ ወርልድ ቱር’ በሚል በተለያዩ አገራት ኮንሰርት እያቀረበ የነበረው ጀስቲን፣ ላለፈው ሳምንት ታቅደው ከነበሩ ኮንሰርቶቹ ሦስቱን ሰርዞ፣ ለሌላ ጊዜ አሸጋግሯቸዋል።
ትውልደ ካናዳዊው ጀስቲን ቢበር፣ በቀኝ የፊቱ ክፍል በገጠመው የነርቭ ጉዳት ምክንያት ኮንሰርቶቹን እንደሰረዘ ገልጾ፣ ሲሻለው ወደ ኮንሰርቶቹ እንደሚመለስ ለአድናቂዎቹ ቃል ገብቷል።
ኢንስታግራም ላይ ላሉት 240 ሚሊዮን ተከታዮቹ፣ የሕመሙን ክብደት ለማሳየት ቪድዮ ለቋል።
“እንደምታዩት የገጠመኝ ሕመም ከባድ ነው። ባልታመም ደስ ይለኝ ነበር። ሰውነቴ እንድረጋጋ እየነገረኝ ሳይሆን አይቀርም። እንደምትረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ለጊዜ ትንሽ እረፍት መውሰድ አለብኝ” ብሏል።
የፊት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመሥራት ለማገገም እየጣረ እንደሆነም ተናግሯል።
ባለፈው ሳምንት ዋሽንግተን ዲሲ እና ቶሮንቶ ኮንሰርት ሊያቀርብ አስቦ ነበር።
ባይታመም ኖሮ በቀጣይ ሳምንት ኒው ዮርክ እና ሎስ አንጀለስም ኮንሰርቶች ያካሂድ ነበር።
ራምዚ ሀንት የሰውነት መቆጣት የሚያስከትል ሕመም ሲሆን፣ ፊትን ፓራላይዝ የሚያደርግና የመስማት ችሎታን የሚቀንስም ነው።
ሕመሙ መጥፋት የሚችል ቢሆንም፣ ዘላቂ ጉዳት የሚሆንበትም ዕድል አለው።
ከ60 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ አንድ ዓይን አልገለጥ እንዲል ከማድረግ ባሻገር፣ ዕይታን ሊጋርድም ይችላል።












