ብሪትኒ ስፒርስ ትውልደ ኢራናዊውን ወጣት አገባች

ብሪትኒ ስፒርስ እና ሳም አስገሃሪ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ብሪትኒ ስፒርስ እና ሳም አስገሃሪ

ከአባቷ ጋር በፍርድ ቤት ስትወዛገብ የቆየችው እውቋ ሙዚቀኛ ብሪትኒ ስፒርስ ከእጮኛዋን ሳም አስገሃሪ ጋር ትዳር መሠረተች።

የ40 ዓመቷ ብሪትኒ ከ28 ዓመቱ ወጣት ትውልደ ኢራናዊ ጋር ሐሙስ ዕለት በሎስ አንጀለስ ከተማ በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ጋብቻ መፈጸሟ ተዘግቧል።

ብሪትኒ ትዳር የመሠረተችው ብዙ ካወዛገበው ከወላጅ አባቷ ቁጥጥር ሥር መውጣት ከቻላች ከሰባት ወራት በኋላ ነው።

የብሪትኒን ገንዘብ ጨምሮ ሌሎችም ውሳኔዎቿን አባቷ ጄሚ ላለፉት 13 ዓመታት ተቆጣጥረው ቆይተው ነበር። ከረዥም የፍርድ ቤት ትግል በኋላ ግን ብሪትኒ ከአባቷ የበላይ ጠባቂነት መውጣት ችላለች።

በአሜሪካ ሕግ አንድ ሰው በጉዳዮቹ ውሳኔ ማሳለፍ የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ሲገባ፣ በፍርድ ቤት ጠባቂ እንዲመደብለት ይወሰናል።

በዚህ አሠራር መሠረት የብሪትኒ የበላይ ጠባቂ የነበሩት አባቷ ነበሩ። ከዚህ ቁጥጥር ነጻ የወጣችበትን ቀን "በሕይወቴ እጅግ የተደሰትኩበት" ስትል ብሪትኒ ገልጸው ነበር።

ብሪትኒ በወላጅ አባቷ የበላይ ተቆጣጣሪነት ስር በቆየችባቸው ጊዜያት “ትዳር መመሠረት እና ልጅ መውለድ አልችልም” ስትል ተናግራ ነበር።

ብሪትኒ እና አስገሃሪ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/BBC

የምስሉ መግለጫ, ብሪትኒ እና አስገሃሪ

የብሪትኒ እና የሳም የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የብሪትኒ የቀድሞ ባለቤት በሠርግ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሳይጋበዝ ለመግባት ጥረት ካደረገ በኋላ በፖሊስ ተይዟል።

ጄሰን አሌክሳንደር የተባለው ግለሰብ እአአ 2004 ላይ ከብሪትኒ ስፒርስ ጋር ለ55 ሰዓታት ብቻ በትዳር ቆይቷል።

ብሪትኒ ከዓመታት በፊት አብሮ አደጓን ጄሰን አሌክሳንደርን በላስ ቬጋስ ካገባችው በኋላ የሙዚቀኛዋ ጠበቆች ብሪትኒ ጋብቻ ለመፈጸም ውሳኔ ማሳለፍ የማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ሆና ትዳር በመመስረቷ ትዳሩ መፍረስ አለባት በማለታቸው ትዳሩ በሰዓታት ውስጥ እንዲፈርስ ተደርጎ ነበር።

የቀድሞ የትዳር አጋሯ ባልተጠራው የሠርግ ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘቱን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ባልተገለጹ ወንጀሎች ከዚህ ቀደም በፖሊስ ይፈለግ እንደነበረ ተነግሯል።

የብሪትኒ የአሁኑ የትዳር ተጣማሪዋ ሳም አስገሃሪን ከእአአ 2016 ጀምሮ ታውቀዋለች። አስገሃሪ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለቢቢሲ ቃለ መጠይቅ በሰጠበት ወቅት፤ ከብሪትኒ ጋር የመጋባት እና ልጆች የመውለድ እቅድ የነበረው ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር ብሏል።

ሳም አስገሃሪ ለብሪትኒ ሦስተኛ ባል ይሆናል። ብሪትኒ ከጄሰን አሌክሳንደር በኋላ ከእአአ 2004 እስከ 2007 ድረስ ከሙዚቀኛው ኬቪን ፌደርላይን ጋር በትዳር ቆይታለች።