ትራምፕ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ክስ ቀረበባቸው

የቀድሞ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከሰሱ።

ትራምፕ ከአንድ ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የካፒቶል ሂል አመጽን አቀነባብረዋል ተብለዋል።

ይህ የቀድሞ ፕሬዝደንት ላይ የቀረበው ክስ የተሰማው ኮንግረሱ የካፒቶል ሂል ሁከትን መመርመር በመጀመረበት ጊዜ ነው።

ከአንድ ዓመት በፊት ታኅሣሥ 28/2013 ዓ.ም. የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች የባይደን ምርጫ አሸናፊነትን ለማረጋገጥ ተሰብስበው ባሉበት ወቅት የትራምፕ ደጋፊዎች ወደ ምክር ቤቱ በኃይል ጥሰው መግባታቸው ይታወሳል።

ይህን ሁከት የሚመረምረው ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ሪፐብሊካኗ ሊዝ ቼኒ፤ ትራምፕ የዚህ ጥቃት ዋና አቀጣጣይ ናቸው ብለዋል።

ዴሞክራቱ ቢኔ ቶምፕሰን ደግሞ ሁከቱ የአሜሪካንን ዴሞክራሲ አደጋ ላይ ጥሏል ሲሉ ተናግረዋል።

ከአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተወጣጣው ኮሚቴ ሁከቱን በተመለከተ ለአንድ ዓመት ያህል ምርመራ ካደረገ በኋላ፤ ለትራምፕ ቅርብ የሆኑ ሰዎችን ያነጋገረበትን የቪዲዮ ቅጂ አሳይቷል።

ለዕይታ ከቀረቡት መካከል በትራምፕ አስተዳደር ወቅት የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የነበሩት ቢል ባር የሰጡት ቃል ይገኘበታል።

የቀድሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ትራምፕ በምርጫ እንደተሸነፉ እና ምርጫው ተጭበርብሯል ማለታቸው ስህተት መሆኑን ነግሬያቸዋለሁ ሲሉ ተደምጠዋል።

የቀድሞ ፕሬዝደንት ትራምፕ የተሸነፉበትን የምርጫ ውጤት እንደማይቀበሉ ገልጸው ምንም አይነት ማረጋገጫ ሳያቀርቡ ምርጫው የተጭበረበረ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

“ሥልጣን ላይ ያለው አካል በማስረጃ ባልተረጋገጡ፤ በራሱ አመለካከት ሥልጣን ላይ የሚቆይበት ዓለም ላይ አይደለንም” ብለዋል የቀድሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ።

በኮሚቴው የተጀመረው ምርመራ የትራምፕ ሴት ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ የሰጠችውንም ቃል በተንቀሳቃሽ ምስል አስደግፎ አቅርቧል።

ኢቫንካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የትራምፕ መከራከሪያን ማጣጣላቸውን “ተቀብያለሁ” ብላለች።

ምክር ቤቱ መርመራውን ጀምሮ በዚህ ወር ለማካሄድ ካቀዳቸው ስድስት ምስክሮችን የመስማት ሂደትን ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ዶናልድ ትራምፕ ምርመራው “ፖለቲካዊ ማጭበርበር ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚሳተፉ በአንድ ስብሰባ ላይ የተናገሩ ሲሆን፣ ያለፈው ምርጫ ተጭበርብሯል በማለት በመረጃ ያልተደገፈ ክሳቸውን አሁንም ማሰመታቸውን ቀጥለዋል።

ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ የቀረበውን ሃሳብ ሪፐብሊካኖች ውድቅ ካደረጉት በኋላ፣ አሁን ምርመራውን የሚያካሂደው የአሜሪካ ምክር ቤት ኮሚቴ በዴሞክራቶች የሚመራ ሲሆን ሁለት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት አሉት።

መርማሪ ኮሚቴው የትራምፕ ደጋፊዎች በካፒቶል ሂል ላይ የፈጸሙትን ወረራ ብቻ ሳይሆን የ2020ን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት “ለመቀልበስ የተቀናጀና ዘርፈ ብዙ” የተባለውን ሙከራ በአጠቃላይ ይመረምራል።