በዓለማችን ሁለተኛው ገዳይ ስለሆነው ስትሮክ ምን ያህል እናውቃለን?

የፎቶው ባለመብት, BSIP
የበሽታ ደግ የለውም። ስትሮክ ግን የክፉ ክፉ ነው። ያለአንዳች ምልክት ድንገት ሊጥል ይችላል። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ስትሮክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለተኛው ገዳይ በሽታ ነው።
ድርጅቱ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 15 ሚሊዮን ሰዎች በስትሮክ እንደሚያዙም አሳውቋል። 5 ሚሊዮን ሰዎች በዚሁ ሰበብ እንሚሞቱና ሌሎች 5 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ለቋሚ የአካል ጉዳት እንደሚዳረጉም አመላክቷል። ይህ ማለት ግን በስትሮክ መያዝ የዓለም ፍጻሜ ነው ማለት አይደለም። ስትሮክ ሊድን ይችላል።
ስትሮክ ምንድን ነው?
ከጠቅላላ ሰውነት 2 በመቶ ብቻ የሚመዝነው አእምሮ በሰውነት ውስጥ ካለው ጠቅላላ የደም አቅርቦት ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን ይወስዳል። በዚህም የደም ዝውውር አማካኝነት አእምሮ ኦክስጅን እና አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን ያገኛል። ይህ ሂደት ለአፍታም ቢሆን እንዲቋረጥበት አያስፈልግም። ደም ሲቋረጥ የአእምሮ ተግባርም አብሮ ቀጥ ይላል።
በተለያዩ ምክንያቶች ድንገት ደም ወደ አእምሮ መሄዱን ሲያቆም ስትሮክ ይከሰታል። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ብስራት ደመቀ የደም ስር መጥበብ፣ ሙሉ በሙሉ መዘጋት ወይም በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ ወደ አእምሮ የሚሄደው ደም እንዲስተጓጎል ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።
የስትሮክ አይነቶች
- 'ሚኒ ስትሮክ': ለአጭር ጊዜ የሚቆይ እና ሊድን የሚችል የስትሮክ አይነት
- የደም መፍሰስ ስትሮክ: በአእምሮ ውስጥ የሚያጋጥም ድንገተኛ ደም መፍሰስ የሚያስከትለው ስትሮክ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ከሚከሰተው ስትሮክ 15 በመቶን ይይዛል።
- የደም ስር መዘጋት ስትሮክ: ወደ አእምሮ ደም የሚወስድ ወይም የሚወስዱ ደም ስሮች መዘጋት ምክንያት የሚመጣ ሲሆን ለ85 በመቶ የስትሮክ መከሰት ምክንያት ናቸው።
"አንጎላችን ከሌላው የሰውነት ክፍል የሚለየው ምንድ ነው? - ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ራሳቸው ይዘውት የሚቆዩት ግሉኮስ አለ። ስለዚህ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ደም ለተወሰነ ጊዜ ቢቋረጥ ያንን መጠቀም ይችላሉ። አእምሯችን ግን እንደዚህ የሚይዘው ነገር የለም" ይላሉ ዶክተሯ።
ስለዚህ አንጎላችን ቀጣይነት ያለው የደም ዝውውር ይፈልጋል። ይህ የደም ዝውውር ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ቢቋረጥ ጉዳት ያመጣል፣ ነገር ገረነረ የድም ዝውውሩ ወዲያው ከተመለሰ ጉዳቱ ሊያገግም እንደሚችል እና 'ሚኒ ስትሮክ' እንደሚባል አስረድተዋል።
ሆኖም የደም ዝውውር ለረጅም ጊዜ ["ለረጅም ጊዜ ማለት ለደቂቃዎች ማለት ነው"] ሲቋረጥ ቋሚ የሆነ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
85 በመቶ የሚሆነው ስትሮክ መነሻው ወደ አንጎል የሚሄድ ደም ስር ወይም የሚሄዱ ደም ስሮች መዘጋት [Ischemic stroke] ሲሆን የተቀረው ደግሞ በአንጎል ውስጥ የደም መፍሰስ [Hemorrhagic stroke] ነው።

የፎቶው ባለመብት, SPL
ለስትሮክ የሚያጋልጠን ምንድን ነው?
እንደ ዶክተር ብስራት ገለጻ ስትሮክ መከላከል በሚቻል እና በማይቻል ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። እነዚህ ምክንያቶች የደም ቧንቧ እንዲዘጋ ወይም ደም በጭንቅላት ውስጥ እንዲፈስ እና ስትሮክ እንዲከሰት ሊያደርጉ ይችላሉ።
የደም ግፊት፣ ስኳር፣ በደም ውስጥ የስብ መከማቸት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት፣ የልብ ምት ችግር መከላከል የምንችላቸው ለስትሮክ የሚያጋልጡን ነገሮች እና ልማዶች ናቸው።
በቤተሰብ ውስጥ በስትሮክ የተያዘ ሰው መኖር እና የእድሜ መጨመር [በተለይ ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ] ለስትሮክ የሚያጋልጡ እና አስቀድሞ ለመከላከል አስቸጋሪ የሆኑ ምክንያቶች ናቸው።
ዶክተር ብስራት ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ለስትሮክ ተጋላጭ መሆናቸውን ያብራሩ ሲሆን፣ የእርግዝና መቆጣጠሪያ እንክብሎች በበሽታው ለመያዝ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል።
እነዚህ ለስትሮክ የሚያጋልጡ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች ወይም እንደ ሲጋራ ማጨስ ያሉ ልማዶች ወይም ጤናማ ያልሆነ ውፍረት የደም መርጋትን በማስከተል ድንገት የደም ስር እንዲዘጋ ምክንያት ይሆናሉ።
አንጎል ውስጥ ደም እንዲፈስና ስትሮክ እንዲከስት ዋነኛው ምክንያት "የደም ግፊት ነው" የሚሉት ዶክተር ብስራት የጭንቅላት ውስጥ ዕጢ፣ በደም ማቅጠኛ መድኃኒት ወይም በሌላ ምክንያት የደም መቅጠን፣ ጭንቅላት ላይ የሚደርስ አደጋ፣ እና እንደ ኮኬይን ያሉ አደንዛዥ እጾች ለደም መፍሰስ ስትሮክ ሊያጋልጡ ይችላሉ።
በሌላ በኩል ጭንቅላት ውስጥ ያሉ የደም ስሮች ተፈጥሯዊ ሁኔታ ለስትሮክ መከሰት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።
ለስትሮክ ሊያጋልጡ የሚችሉ ምክንያቶች፦
- ደም ግፊትና የስኳር ህመም
- ከልብ ጋር የተያያዙ ችግሮች
- የስብ ክምችትና ከመጠን ያለፈ ውፍረት
- ሲጋራ እና አድንዛዥ ዕጾች
- የእርግዝና መቆጣጠሪያ እንክብሎች
- የጭንቅላት ዕጢ
- የደም መቅጠን
- ጭንቅላት ላይ የሚደርስ አደጋ
ዶክተር ብስራት ክብደት መጨመር ለስትሮክ አንዱ አጋላጭ ምክንያት መሆኑን ሲያስረዱ "የአመጋገብ ችግር ስኳር ያመጣል፣ ግፊት ያመጣል። ሌላው የሚያመጣው ነገር ደግሞ ስትሮክ ይሆናል" ይላሉ።
ጮማና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች ማዘውተር በደም ስር ውስጥ ስብ እንዲከማች እና የደም ስሮች እንዲዘጉ ወይም እንዲጠቡ በማድረግ ስትሮክ እንዲከሰት ሰበብ ይሆናል።
"የስብ ክምችት ሊጨምር የሚችል የአኗኗር ዘይቤ ሲኖረን ደም ስራችን እየጠበበ ይሄዳል ማለት ነው። ጥበቱ ከፍተኛ በሆነ ቁጥር ጉዳቱም ከፍተኛ ይሆናል። የስብ ክምችቱ በራሱ ጥበት ያመጣል። ሁለተኛ ደም እንዲረጋ ያደርጋል" ሲሉ ዶክተሯ አብራርተዋል።
"ከዚያ ውጪ ጨው፣ ጣፋጭ ነገር መቀነስ፣ ሲጋራ በተቻለ መጠን አለማጨስ" ተጋላጭነትን እንደሚቀንስም ጠቅሰዋል።
የደም ግፊታቸውን ለረጅም ጊዜ ሳይቆጣጠሩ የቆዩ ሰዎች ለስትሮክ የመጋለጣቸው ዕድላቸው ሰፊ ነው።
በተጨማሪም በቤተሰብ ውስጥ የስትሮክ ችግር ያጋጣማቸው ሰዎች ካሉ "አልፎ አልፎ" የደም ማቅጠኛ የሚወስዱ ደግሞ "ቶሎ ቶሎ" በህክምና ተቋም ምርመራ ማድረግ በሽታውን ለመከላከል ይረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስትሮክ ምልክቶች አሉት?
ስትሮክ ያለምንም ቅድመ ምልክት ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚ አለ። ሆኖም እንደ ዶክተር ብስራት ገለጻ ጉዳቱ እንደደረሰበት የአንጎል ክፍል እና መጠን የሚወሰን ነው።
ለምሳሌ ጉዳቱ የሰውነትን ሚዛን የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ላይ ከደረሰ ሰዎች ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ይቸገራሉ። የሰውነት መስነፍ/አለመታዘዝ፣ ለመናገር መቸገር፣ ለማስታወስ መቸገር፣ የዕይታ ችግር፣ ከፊል የፊት ክፍል መዛባት ወይም አለመታዘዝ፣ ከባድ የራስ ምታት፣ መደንዘዝ እና የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ ከሆነ ራስን እስከመሳት ሊደርስ ይችላል።
የስትሮክ ምልክቶች
- የሰውነት ሚዛንን ለመጠበቅ መቸገር
- የሰውነት መስነፍ/አለመታዘዝ
- ቃላትን ለማውጣት መቸገር
- ለማስታወስ መቸገር
- የፊት አንደኛው ክፍል መዘነፍ/አለመታዘዝ
- ከባድ የራስ ምታት
- መደንዘዝ
ስትሮክ ይድናል?
የዚህ ጥያቄ መልስ "እንደጉዳቱ መጠን። እንዳስከተለው ጉዳት ይወሰናል" ይላሉ - ዶ/ር ብስራት። በተለይ ከደም መፍሰስ ጋር የሚያያዛው ስትሮክ ወዲያው ሞትን ሊያስከትል ይችላል።
ሆኖም "ያ ጉዳት የደረሰበት የአንጎል ክፍል ትንሽ ከሆነ። በዋናነት ሰዎች ወደ ህክምና ቦታ የሚሄዱ ከሆነና ጉዳቱን መቀነስ ከተቻለ በጊዜ ሂደት ወደ ነበረበት ቦታ የመመለስ ሁኔታ ሊኖር ይችላል።...እኛ የሚያስቸግረን ምንድን ነው ብዙ ሰው የሚመጣው ዘግይቶ ነው። በሁለት ሦስት ሰዓት ውስጥ ቢመጣ...እኛ አገር የሚገኙ መድኃኒቶች አሉ ይህንን ጉዳት ማቆም የሚችሉ" ስትል ታስረዳለች።
በስትሮክ ዳግም የመጠቃት አጋጣሚ መኖሩንም የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቷ ዶክተር ብስራት ይናገራሉ። የደም መርጋትን ለመከላከል የሚሰጡ መድኃኒቶችን በአግባቡ አለመጠቀም ስትሮክ ድጋሚ የሚመጣበት አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል።
ከስትሮክ እና ከሌሎች በሽታዎች ራስን የመጠበቂያ ወሳኙ መንገድ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል መሆኑን የሚመክሩት ዶክተር ብስራት፣ ቋሚና የታሰበበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የብዙ በሽታ መፍትሄ መሆኑን ይገልጻሉ።
"እንቅስቃሴ ማድረግ ማለት ግዴታ ጂም ገብቶ መስራት አይደልም። ቢያንስ በሳምንት ሦስት ቀን በትንሹ ለሰላሳ ደቂቃ የሚሆን እንቅስቃሰሴ ማድረግ" ይቻላል።
ስብጥሩን የጠበቀ ምግብ መመገብ፣ አትክልት እና ፍራፍሬን ማዘውተር፣ ሱሶችን ማስወገድ እና ቅባታማ ምግቦችን መቀነስ በርከታ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
በስትሮክ የተያዙ ሰዎች ምን ያድርጉ?
ዶክተር ብስራት የስትሮክ ምልክቶችን የሚያዩ ሰዎች ቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት፣ ወደ ህክምና ተቋም በታቻለ ፍጥነት ማምራት ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ጉዳቱ በደረሰ "እስከ አራት ሰዓት የሚመጡ ከሆነ ጉዳቱን በደንብ መቀነስ ይችላል።"
በተጨማሪም ችግሩ ካጋጠመ በኋላ ደግም እንዳይከሰት አስፈላጊ የህክምና ክትትል ማድረግን መክረዋል።
በሌላ በኩል 'ፊዚዮቴራፒ' ስትሮክ ካጋጠመ በኋላ ብዙ ጉዳቶችን ለመቀነስ እንደሚረዳ አብራርተዋል። ከተቻለ በባለሙያ ካልሆነም በቤተብ አባል የሚሰጥ 'ፊዚዮቴራፒ' የሰነፈ ሰውነትን ለማነቃቃት የሚያግዝ ሲሆን፣ የመናገር ችግር የገጠማቸው ሰዎች ደግሞ የንግግር ልምምድ [speech therapy] ማድረግ ከፍተኛ ለውጥን እንዲያዩ ያደርጋቸዋል።
"ስትሮክ አጋጠመ ከተባለ እንደመጨረሻ የማየት፣ ተስፋ የመቁረጥ እና ምንም ማድረግ እንደማይቻል መቁጠር አለ። ብዙ ነገሮችን መቀየር ይችላል። ግን የምንቀይረው ወዲያው ሳይሆን በረጅም ጊዜ ነው።
"መድኃኒቶችን መውሰድ፣ ቴራፒ ማድረግ፣ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል፣ ስኳር፣ ግፊት እና ከልብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ማስተካከልስ አንደኛ በሽታው ተመልሶ እንዳይመጣ ያደርጋል። ሁለተኛ ደግሞ እየባሰ እንዳይሄድ ያደርጋል። በትክክል እነዚህን ነገሮች ያደረጉ ደግሞ ወደ ቀድሞ ቦታቸው የተመለሱ ሰዎችም አሉ። ያ ግን ዓመታትን ይፈጃል" ሲሉ ዶ/ር ብስራት አስረድተዋል።












