የእንግሊዙ ሊቀ ጳጳስ ዩኬ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ማቀዷን ኮነኑ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
መንግሥት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሩዋንዳ ለመላክ የያዘው እቅድ " ከአምላክ ስራ ጋር የሚቃረን ነው፤ ፈሪሃ አምላክ አይደለም" ሲሉ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ተናገሩ።
ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ስብከት የክርስቶስ ትንሳኤ ኃላፊነታችንን የምንቀንስበት አይደለም" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሊቀ ጳጳሱ በዩክሬን በሚካሄደው ጦርነት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በኑሮ ውድነት ላይ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
መንግሥት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ለማቀዱ "የሰዎችን ሕይወት ከሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ለመጠበቅ ለውጥ ያስፈልጋል" ሲል በምክንያት ያስረዳል።
ይሁን እንጂ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ዩኬ የሚገቡ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ለማቅረብ እና ጉዳያቸውን ለማስፈፀም ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር መላክን የሚያካትተው የ120 ሚሊየን ፓውንድ እቅድ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።
ከ160 በላይ የሚሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ዘመቻ የሚያካሂዱ ቡድኖች በዚህ ሳምንት ይፋ የተደረገውን እቅድ "ጭካኔ የተሞላበት ነው" ሲሉ ሚኒስትሮች ሃሳባቸውን እንዲሰርዙ አሳስበዋል።
በተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በአንዳንድ ወግ አጥባቂዎችም በኩልም እቅዱ ትችት ቀርቦበታል።
በካንትርበሪ ካቴድራል ሊቀ ጳጳስ ዌልቢ " ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ውጭ አገር ለመላክ መታሰቡ ላይ ከባድ የሥነ ምግባር ጥያቄዎች" እንዳሉ ይናገራሉ።
"ዝርዝሩ ለፖለቲካ ነው፤ መርሁ ግን በአምላክ ፍርድ ላይ መመርኮዝ አለበት፤ እንደዚህ መሆን ግን አይችልም" ብለዋል።
" ኃላፊነታችንን መሸከም ስላልቻልን ክርስቲያናዊ እሴቶች ላይ የተመሰረተች አገር እንደ አገር ያለንን አገራዊ ኃላፊነት መወጣት አልቻልንም። ይህም ለውድቀታችንና ለሃጢያታችን ኃላፊነት ከወሰደው እግዚአብሔር ባህርይ ጋር ተቃራኒ ነው" ብለዋል ሊቀ ጳጳሱ።
የአገር ውስጥ መሥሪያ ቤቱ ሊቀ ጳጳሱ በእቅዱ ላይ ለሰነዘሩት ትችት ምላሽ ዩኬ የተቸገሩትን በመደገፍ ኩሩ ታሪክ እንዳላት በመግለጽ እና የጥገኝነት ጥያቄዎችን በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች " ደህንንቱ በተጠበቀና ሕጋዊ በሆነ መንገድ" የተሻለ ሕይወት መስጠታቸውን አስታውሷል።
ነገር ግን "ዓለም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የስደት ችግር ገጥሟታል እና ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ለመከላከል እና የተበላሸውን ዓለም አቀፍ የጥገኝነት ሥርዓት ለማስተካከል ለውጥ ያስፈልጋል" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የአገር ውስጥ መሥሪያ ቤቱ አክሎም ሩዋንዳ " ደህንነቱ የተጠበቀ" እንደሆነች እና የጥገኝንት ጥያቄዎችን ተቀብላ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ሕጎች መሠረት እንደምታስተናግድ ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሩዋንዳ መላክ ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጻረር መግለጹ ይታወቃል።












