"ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከዩኬ ወደ ሩዋንዳ መላክ ዓለም አቀፍ ሕግን ይጻረራል" ተመድ

ጥገኝነት ጠያቂዎች

የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሩዋንዳ መላክ ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጻረር ገለጸ።

"የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ የመመልከት ኃላፊነትን ወደ ሌላ አገር ማዘዋወር ተቀባይነት የለውም" ብሏል።

የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ዕቅዳቸው ዓለም አቀፍ ሕግን እንደማይጥስ ተናግረዋል።

የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ውሳኔውን በተመለከተ በተለይም ከወጪ ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ቢሮሩትም ፖሊስ ሊቀረጽ እንደሆነ ተገልጿል።

ለአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፕሪቲ ፔታል የቀረቡ የቢቢሲ ምንጭ "ወደ አገሪቷ በሕገ ወጥ መንገድ የሚገቡ ሰዎችን መቀነስ ወጪ ይቀንሳል" ብለዋል።

ዩኬ ለዚህ ዕቅድ የመደበችው 120 ሚሊዮን ፓውንድ ነው።

ከጥር 1 ጀምሮ ወደ ዩኬ በሕገ ወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉ ሰዎች ወደ ሩዋንዳ የሚላኩበት አሠራር ነው።

ሩዋንዳ ሆነው የጥገኝነት ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ዩኬ ወስናለች።

ወደ ሩዋንዳ የሚወሰዱት የመጀመሪያዎቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች ከሳምንታት በኋላ በረራ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

በመጀመሪያ የሚላኩት በአነስተኛ ጀልባ ወደ ዩኬ የገቡ ያላገቡ ወንዶች ናቸው።

ከ160 በላይ የተራድኦ ድርጅቶች እና የመብት ተሟጋቾች ዩኬ ውሳኔውን እንድትቀለብስ ጠይቀዋል።

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና ወግ አጥባቂዎችም የዩኬን ውሳኔ ኮንነዋል።

የዩኤንኤችሲአር ተባባሪ ዋና ጸሐፊ ጂሊያን ትሪግስ፣ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ የመመልከት ኃላፊነትን ወደ ሌላ ወገን ማስተላለፍ ተገቢ አይደለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቀድሞ የአውስትራሊያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ፕሬዝዳንት የነበሩት ጂሊያን፣ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ ለመመልከት ከዚህ የተሻለ መንገድ አለ ብለዋል።

አውስትራሊያ እአአ ከ2001 ጀምሮ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ እስከምትመረምር ከከተማ ውጭ የማቆየት አሠራር ዘርግታለች።

ማቆያዎች ከደረጃ በታች ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ አሠራሩን የተባበሩት መንግሥታት እና የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም ኮንነውታል።

አውስትራሊያ ለዚህ አሠራር 811 ሚሊዮን ዶላር ከ2021 እስከ 2022 አውጥታለች።

ከዚህ ቀደም እስራኤል ኤርትራውያን እና ሱዳናውያን ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ አስባ እንደነበር የገለጹት ጂሊያን "ከአገሪቱ ወጥተው ሂደቱን በድጋሚ ለመጀመር ተገደዋል። ይህም አካሄዱ ለረዥም ጊዜ እንደማይሆን ማሳያ ነው" ብለዋል።

በርካታ የሕግ ባለሙያዎች የዩኬ ዕቅድ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን ጨምሮ የተለያዩ ከሕግ ጋር የተያያዙ ጥያዎች እንደሚጠብቁት እያስጠነቀቁ ነው።

በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ጥገኝነት ጠያቂዎችን አደጋ ሊደርስባቸው ወደሚችልበት አገር መላክ ክልክል ነው።

አምና ዩኬ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ባደረገችው ንግግር በሩዋንዳ "ከሕግ ውጭ የሆነ ግድያ፣ የሰዎች መሰወር፣ እንግልት እንዲሁም የፖለቲካ እና ሲቪል መብት እጦት ያሳስበኛል" ማለቷ አይዘነጋም።

ሆኖም ግን የዩኬ የፍትሕና ስደት ሚኒስትር ቶም ፐርስግሎቭ ሩዋንዳ ባለፉት 30 ዓመታት ለውጥ እየታየባት እንደመጣና ተራማጅ አገር እንደሆነችም ይናገራሉ።

ዩኬ በአነስተኛ ጀልባ ወደ አገሯ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር የመቀነስ ዕቅድ አላት። ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ሐሳብም የዚህ አካል ነው።

ይህ ዕቅድ ይፋ በተደረገበት ቀን በ14 ጀልባዎች 562 ሰዎች ወደ ዩኬ ጉዞ አድርገዋል።

አምና 28,526 ሰዎች ባሕር አቋርጠው ገብተዋል።