ሱዳን ከግብጽ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ የማዕድን ቆፋሪዎች ተገደሉ

የሱዳን የባህል ልብስ ለብሰው ወርቅ የሚፈልጉ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ, በሰሜናዊ ሱዳን ባህላዊ የወርቅ አውጪዎች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሱዳን ድንበር አካባቢ በወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ላይ የአየር ጥቃት ተፈጽሞ ቢያንስ 72 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን በአካባቢው የሚንቀሳቀስ አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን አስታወቀ።

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም መቀመጫውን ያደረገው 'ኤመርጀንሲ ሎየርስ' ቅዳሜ ዕለት በሱዳን ናይል ግዛት ውስጥ በሚገኝ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ስፍራ በወርቅ ቁፋሮ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በጦር አውሮፕላን ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል ብሏል።

ስለ ጥቃቱ የግብፅ መንግሥትም ሆነ የሱዳን ባለሥልጣናት እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡም።

ካይሮ ቀደም ሲል በደቡባዊ ድንበሯ ላይ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል በሚል የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች ላይ ጥቃቶች ትፈጽማለች የሚል ክስ ቀርቦባታል።

'ኤመርጀንሲ ሎየርስ' የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ቀደም ሲል ተፈጽመዋል ያላቸውን ጥቃቶች ጠቅሶ፣ እነዚህ ጥቃቶች የሱዳንን ሉዓላዊ ግዛት መጣስ ብቻ ሳይሆን መንግሥት በክልሉ ላይ ያለው ቁጥጥር ማነሱንም ያሳያሉ ብሏል።

እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ "ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎችን ሆን ተብሎ ማጥቃት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን እና የመኖር መብትን ይጥሳል" ብሏል። አክሎም "እነዚህ ድርጊቶች የጦር ወንጀሎችን ሊያካትቱ ይችላሉ" ብሏል።

ከጥቃቱ በኋላ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።

መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው ሱዳን ትሪቡን የተባለው ጋዜጣ የሟቾች ቁጥር 'በኤመርጀንሲ ሎየርስ' ሪፖርት ከተጠቀሰው እጅግ የላቀ ሊሆን እንደሚችል ዘግቧል።

ቅዳሜ ዕለት ከተፈጸመው ጥቃት በሕይወት የተረፈ አንድ ግለሰብ ብዙ ሰዎች መቁሰላቸውን እንደነገረው ጋዜጣው በዘገባው አካትቷል።

የዐይን እማኞች ጥቃቱ የተፈጸመው በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር 6:00 አካባቢ መሆኑን ገልጸው፣ አውሮፕላኑ በቀጥታ በማዕድን ቆፋሪዎች ካምፖች ላይ ከአምስት በላይ ሚሳኤሎችን በመተኮስ አውድሟል።

አክለውም የወርቅ ጉድጓዶች ውስጣቸው ሰዎች እንዳሉ በላያቸው ላይ መደርመሳቸውን የዐይን እማኞችን ጠቅሶ ጋዜጣው ዘግቧል።

ሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ በሰኔ ወር ላይ የግብፅ መንግሥት በተመሳሳይ ክልል ውስጥ በሚገኙ የማዕድን ማውጫ ቦታዎች ላይ ድሮኖችን እና መድፎችን ተጠቅሞ በርካታ ሰዎችን ገድሏል ሲል ዘግቧል።

ጋዜጣው አክሎም የግብፅ የድንበር ጠባቂዎች አልፎ አልፎ የማዕድን ማውጫ መሣሪያዎችን ያቃጥላሉ፣ ጊዜያዊ መጠለያዎችን ያወድማሉ እንዲሁም የማዕድን ሠራተኞቹን ለመበተን በቀጥታ ወደ ሰው ጥይቶችን ይተኩሳሉ ሲል በዘገባው ላይ አካትቷል።

ከጥቂት ቀናት በኋላ የግብፅ የድንበር ኤጀንሲ ሕገወጥ ፍልሰትን፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን እና ሕገወጥ የማዕድን ቁፋሮዎችን ለማስቆም በድንበሩ ላይ ሰፊ የጸጥታ ዘመቻ መጀመራቸውን አስታውቋል።

በተመሳሳይ ጊዜ የሱዳን ባለሥልጣናት በርካታ ሰዎችን እንደገደለ የሚነገርለትን ጥቃት በተመለከተ ምርመራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በግብጽ አና በሱዳን ድንበር መካከል ላለው ውጥረት የወርቅ ማዕድን ዋና ምክንያት ነው።