ትግራይ በኮማንድ ፖስት እንደምትመራ እና ከስድስት ወር በኋላ ምርጫ እንደሚካሄድ ተነገረ

አቶ ጌታቸው ረዳ
የምስሉ መግለጫ, አቶ ጌታቸው ረዳ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የህወሓት መሪዎች መቀለን ጨምሮ ከበርካታ የትግራይ ከተሞች ለቅቀው ከወጡ በኋላ ክልሉ በፌደራል መንግሥቱ ኮማንድ ፖስት ሥር እንደሚቆይ እና በትግራይ ምርጫ እንደሚካሄድ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ።

የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት እና በአሁኑ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ይህንን የተናገሩት ቲቢኤስ ከተባለ መገናኛ ብዙኃን ጋር በትግርኛ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ትግራይ በጊዜያዊ አስተዳደር ስትመራ የቆየች ሲሆን፤ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ወዲህ ደግሞ የህወሓት መሪዎች ጊዜያዊ አስተዳደሩን አስወግደው ከጦርነቱ በፊት የነበረውን አስተዳደር ወደ ሥልጣን መመለሳቸው ይታወሳል።

በዚህም ሳቢያ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መሪዎች መካከል ለስድስት ወራት የቆየው ፍጥጫ ወደ ጦርነት ተሸጋግሮ የመከላከያ ሠራዊት እና አጋሩ የትግራይ ሰላም ኃይሎች አብዛኛውን የትግራይ አካባቢዎች እየተቆጣጠሩ ነው።

አቶ ጌታቸው ይመሠረታል ያሉት ክልሉን የሚያስተደድረው ኮማንድ ፖስት (የዕዝ ማዕከል) ዋነኛ ኃላፊነት "ትግራይን በሕግ የምትመራ ማድረግ፣ ደኅንነትን ማስከበር፣ እና ክልሉን መልሰው የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ማከናወን ነው" ብለዋል።

የክልሉን ፀጥታም የፌደራል መንግሥቱ የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ሰላም ኃይሎች በጋራ የሚስከብሩ ሲሆን፣ እነዚህ ኃይሎች በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንደሚገባም ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው በተጨማሪም ከአማራ ክልል ጋር የይገባናል ውዝግብ ካለበት የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደየቤታቸው እንደሚመለሱም አስታውቀዋል።

አቶ ጌታቸው፣ ከዚህ በኋላ የትግራይ ክልል በፌደራል መንግሥቱ በሚቋቋም ኮማንድ ፖስት እንደሚመራ እና ከስድስት ወራት በኋላ በክልሉ ምርጫ ተደርጎ በሕዝብ የሚመረጥ አስተዳደር ሥልጣን እንደሚረከብ አመልክተዋል።

በአገሪቱ ምርጫዎችን በሚያስተዳድረው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተደረጉ ሁለት አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ሳይካሄዱበት በቀረው በትግራይ ክልል ከስድስት ወራት በኋላ የሚካሄደውን ምርጫ ቦርዱ እንደሚመራው አቶ ጌታቸው ጠቅሰዋል።

አቶ ጌታቸው ዳግም በትግራይ ለተቀሰቀሰው ጦርነት ተጠያቂ ናቸው ከሚሏቸው የህወሓት መሪዎች እና በወንጀል ድርጊት ከሚጠየቁት በስተቀር የህወሓት አባላት በትግራይ መልሶ ግንባታ ውስጥ ሊሳተፉ ይችለሉ ብለዋል።

የህወሓት መሪዎች በአሁኑ ጊዜ ከኤርትራ ጋር በሚዋሰነው የመረብ ወንዝ አቅራቢያ እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ጌታቸው፤ ከዚህ በኋላ ዳግም ወደ ክልሉ አመራርነት እንደማይመጡ የተናግረዋል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት ትግራይን ከአፋር እና ከአማራ ክልሎች ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ጦርነት መቀስቀሱ አይዘነጋም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ጌታቸው እና አጋሮቻቸው ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው ሥልጣናቸውን በመልቀቅ ወደ አዲስ አበባ ካቀኑ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ዛሬ እሑድ ጥቅምት 01/2019 ዓ. ም. ወደ መቀለ መግባታቸው ተዘግቧል።

ጦርነቱ ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሳምንታት አቋርጦት የነበረውን የመቀለ በረራ ዛሬ እሑድ ሲጀምር አቶ ጌታቸውን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት እና የትግራይ ሰላም ኃይሎች መሪዎች በመጀመሪያው ጉዞ ወደ መቀለ መግባታቸው ተዘግቧል።