ጌታቸው ረዳ እና ህወሓት በጽኑ የተፈተኑበት ሁለት ዓመታት ፍጻሜ?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከቀደምት የህወሓት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች ጋር ለወራት ፍጥጫ ውስጥ የቆዩት አቶ ጌታቸው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት ጊዜያቸው በድንገት አብቅቷል።
ከሦስት ሳምንታት በፊት በሊቀመንበሩ ደብረ ፂዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን መቀለን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የአስተዳደር ተቋማትን በኃይል ሲቆጣጠር ነበር አቶ ጌታቸው ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት።
አቶ ጌታቸው ወደ አዲስ አበባ ያመሩት በትግራይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ከምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ጋር ለመወያየት እንደነበር እና ጉዳያቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ መቀለ እንደሚመለሱ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን አቶ ጌታቸው ይህንን ካሉ ሦስት ሳምንታት ያለፉ ሲሆን፣ ለሕክምና ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች አምርተው ከሰነበቱ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነታቸው ማብቃቱን የሚያመለክት መልዕክት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ በትግርኛ ቋንቋ ተሠራጭቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነትን ባስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ በማመስገን የኃላፊነት ጊዜያቸው መጠናቀቁን የሚጠቁም መልዕክት አስፍረዋል።

የፎቶው ባለመብት, PM Abiy
ጌታቸው እና የግድያ ሙከራ
በአቶ ጌታቸው ጊዜያዊ አስተዳደር ደስተኛ ያልነበረው በደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ ባለፉት ወራት በአስተዳሩ ላይ የሚያሳድረውን ጫና እያበረታ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ በበርካታ የትግራይ አካባቢዎች የሚገኙ የአስተዳደር ተቋማትን በኃይል ተቆጣጥሯል።
ይህ ሁኔታም በታጠቁ ኃይሎች የታገዘ በመሆኑ በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ግጭት ይፈጠራል የሚል ስጋት አስከትሎ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት የአቶ ጌታቸው ደኅንነትም አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበረ ራሳቸው ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ከተለያዩ የዩቲብ ቻናሎች ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ በትግራይ ውስጥ ውጥረቱ በተባባሰበት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ሲነሱ ጥቃት ሊፈጸምባቸው እንደነበር ተናግረዋል።
በእርሳቸው ላይ ግድያ ከመፈጸም ጋር የሚመሳሰሉ ዕቅዶች እንደበሩ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፣ ወደ መቀለው አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ በሚያቀኑበት ጊዜ ኬላ ላይ የነበረ ታጣቂ እንዳያልፉ የመከልከል ሙከራ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም መሳሪያ በተጠመደበት መኪና እስከ አየር ማረፊያው ድረስ ክትትል እንደተደረገባቸው እና በአየር ማረፊያው ጥበቃ በፌደራል ፖሊሶች እንዲቆሙ መደረጋቸውን እና ክትትሉም አውሮፕላን ውስጥ እስኪገቡ ድረስ እንደነበር ገልጸዋል።
ጌታቸው እና ህወሓት
አቶ ጌታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ቀደምት እና ጉልህ ተጽዕኖ ከነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ በሆነው ህወሓት ውስጥ ከዕድሜ እና በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ካላቸው ሚና አንጻር እንግዳ ናቸው።
ጌታቸው ከሌሎቹ የህወሓት ዋነኛ መሪዎች በተለየ ወታደራዊውን መንግሥት ለመጣል በተደረገው የትጥቅ እንቅስቃሴ ውስጥ አልተሳተፉም።
ግማሽ ክፍለ ዘመን ባስቆጠረው ህወሓት ውስጥ አቶ ጌታቸው ያላቸው ተሳትፎ ሃያ ዓመት አይሞላም።
ነገር ግን ባለፉት አስር ዓመታት በድርጅቱ ውስጥ ያገኙት ተቀባይነት እና ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።
ጥብቅ በሆነው የህወሓት የአመራር መሰላል ላይ ተረማምደው በአጭር ጊዜ ምክትል ሊቀመንበር ለመሆን ችለዋል።
አቶ ጌታቸው ከህወሓት ሊቀመንበር መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በተለያዩ የፌደራል መንግሥቱ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመሥራት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አማካሪነት እስከ ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር የሥልጣን ደረጃ ላይ በአጭር ጊዜ ለመድረስ ችለዋል።
ህወሓት ወሳኝ በነበረበት እና አገሪቱን ለ27 ዓመታት የመራው ኢህአዴግ እየተዳከመ ሕዝባዊ አመጽ ሲንጠው በውስጡ የተቀሰቀሰው ለውጥ ህወሓትን ገሸሽ አደረገው።
በፌደራል መንግሥቱ የሥልጣን መንበር ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበራቸው የህወሓት አመራሮች ወደ መቀለ ሲያመሩ አቶ ጌታቸውም ወደዚያው አቅንተዋል።
ጌታቸው እና ጦርነቱ
የህወሓት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች መቀመጫቸውን መቀለ ላይ አድርገው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ውዝግብ ውስጥ ሆነው ከቆዩ በኋላ የፈነዳው አውዳሚው የሁለት ዓመት ጦርነት፣ ከሌሎቹ አመራሮች በተለየ ጦርነት የማያውቁትን አቶ ጌታቸውን ወደ በረሃ እንዲወርዱ አስገድዷቸዋል።
የዓለምን ትኩረት ስቦ በነበረው በዚህ ጦርነት ወቅት፣ ጌታቸው ከየትኛውም የህወሓት አመራር በበለጠ በተደጋጋሚ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ ትኩረትን አግኝተዋል።
በዚህም ዓላማ እና ግባቸውን በትግርኛ፣ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ በማስረዳት የህወሓት ዋነኛው ፊት ሆነው ቆይተዋል።
በጦርነቱ ወቅት በአሜሪካ እና በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በምሥጢር እና በግልጽ በተካሄዱ ንግግሮች ላይ አቶ ጌታቸው ረዳ አንደኛው ተሳታፊም ነበሩ።
ጂቡቲ እና ሲሼልስ በምሥጢር፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ላይ ደግሞ በይፋ በተደረጉ ንግግሮች እና ድርድሮች ላይ ጌታቸው ቁልፍ ሰው መሆናቸው ይነገራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጌታቸው እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ
ፕሪቶሪያ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ሲወሰን፣ የፌደራል መንግሥቱ በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጊዜያዊ መንግሥቱን ፕሬዝደንት በመሰየም በኩል ወሳኝ ሚና አላቸው።
ከጦርነቱ በፊት የነበረው በህወሓት የበላይነት የተያዘው የክልሉ አስተዳደር እንዲፈርስ በመወሰኑ እንደ አዲስ በሚወቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ የህወሓት ጉምቱ መሪዎች ቁልፍ ቦታዎችን ለመያዝ ቢሞክሩም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ይሁንታ ማግኘት አልቻሉም።
በዚህም ምክንያት ለቀናት የቆየ ስብሰባ አድርገው አቶ ጌታቸውን በዕጩነት አቅርበው ተቀባይነት ለማግኘት ቢችሉም ቀደምት የድርጅቱ መሪዎች ደስተኛ አልነበሩም።
በዚህም ሳቢያ ከመጀመሪያው አንስቶ በነባር የህወሓት አመራሮች እና በአቶ ጌታቸው መካከል የነበረው ግንኙነት ቀስ በቀስ እየተበላሸ ሄዷል።
በዚህም ምክንያት ከባድ ፈተና እንደሚገጥማቸው እንደተረዱ ከቀናት በፊት ዱባይ ውስጥ ለአንድ ድረገጽ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ አመልክተዋል።
አቶ ጌታቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩን መሪነት ሲረከቡ ከአምስቱ የህወሓት መሪዎች መካከል የትጥቅ ትግሉ ተሳታፊ ሆነው በድርጅቱ ውስጥ ባለማለፋቸው ተባብሮ መሥራቱ የማይቻል ባይሆንም ከባድ እንደሚሆን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
ይህ ስጋታቸው በወራት ውስጥ እውን እየሆነ ከዋነኞቹ የህወሓት መሪዎች ፈተናዎች እንደገጠሟቸው በመግለጽ የፓርቲ መሪዎቻቸው "በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ ሻጥር በመፈጸም" እንዲሁም በክህደት እና ለሌሎች [ለፌደራል መንግሥቱ] በመሥራት ይከሷቸው እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህ ምክንያትም አቶ ጌታቸው የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር ከክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ውጪ ባሉ ቦታዎች ሚና እንዳይኖረው ሥልጣኑን የሚጋፉ ተግባራት በፓርቲያቸው አመራሮች እንሚፈጸሙ ከአንድ ዓመት በፊት መግለጻቸው ይታወሳል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም አቶ ጌታቸው በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የአካባቢ አመራሮችንም አስከማባረር ደርሰው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጌታቸው እና የፕሬዝዳንትነት ጣጣ
በአቶ ጌታቸው የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ከተመሠረተ እና በክልሉ ውስጥ መዋቅሩን ለማጠናከር በሚጥርበት ጊዜ በርካታ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል።
ከእነዚህም መካከል በጦርነቱ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ተዋጊዎች ተገቢው እንክብካቤ አልተደረገልንም በሚል በተደጋጋሚ አደባባይ ወጥተዋል።
ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ የመንግሥት መዋቅር በተዳከመባት ትግራይ ውስጥ የወንጀል ድርጊቶች መበራከት፣ ሕገወጥ የማዕድን ማውጣት እና የዘረፋ ድርጊቶች መስፋፋት የሕዝቡ ስጋት ሆኖ አሁን ድረስ ዘልቋል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በህወሓት መሪዎች መካከል ያለው አለመግባባት እና ውዝግብ ከዕለት ዕለት ሲጠናከር በሊቀመንበሩ ደብረጽዮን እና በምክትላቸው በጌታቸው መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ በግልጽ መወነጃጀል ተከስቷል።
በተለይ ሕጋዊ ዕውቅና ያላገኘው የህወሓት 15ኛ ጉባኤ መካሄዱን ተከትሎ አቶ ጌታቸው እና ሌሎች አመራሮች ከድርጅቱ ከተባረሩ በኋላ፣ በአቶ ጌታቸው ላይ የሚሰነዘሩት ክሶች ተጠናክረዋል።
ባንዳ፣ ተላላኪ እንዲሁም ከሃዲ የሚሉ ቅጽሎች በተደጋጋሚ በሚወጡ የህወሓት መግለጫዎች ላይ በተደጋጋሚ ይሰሙ ነበር።












