የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሲያ በብሬግዚት ሕዝበ ውሳኔ ወቅት እጇን አስገብታለች አሉ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም
የምስሉ መግለጫ, የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም ሩሲያ በብሬግዚት ሕዝበ ውሳኔ ወቅት ጣልቃ መግባቷን እና በፈረንሳይ እና በጀርመን ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች እያካሄደች መሆኗን በመግለጽ አስጠነቀቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ'ዘ ሬስት ኢዝ ፖለቲካ' ፖድካስት እንደተናገሩት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ሲረከቡ እአአ በ2016 በተደረገው ምርጫ ላይ የሩሲያ ጣልቃ ገብነት ሊኖር ስለሚችልበት ሁኔታ ጠይቀው "አዎ፣ እንደዚያ ነበር የሚል ግልጽ መልስ አግኝቻለሁ" ብለዋል።

"በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም ዘግይተን እንደነበርን አስባለሁ፤ የውጭ ኃይሎች የፖለቲካ ሂደቱን ለማደናቀፍ ምን ያህል ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ለዜጎች በቂ መረጃ አላቀረብንም" ሲሉ አክለዋል።

በርንሃም በብሬግዚት ሕዝበ ውሳኔ ወቅት የሞስኮ እንቅስቃሴ በምን ያህል መጠን ወይንም ምን ዓይነት እንደነበር ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

የብሬግዚት ደጋፊ የሆነው ብሪቲሽ ኡንባውንድ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተያየት "የብሪታኒያ ሕዝብ በ2016 የወሰነውን ውሳኔ ሕጋዊነት ዝቅ ለማድረግ የተደረገ ሌላ ከባድ ሙከራ" ብሎታል።

ቡድኑ በዩኬ ምርጫ የውጭ ጣልቃ ገብነት "በግልጽ ተቀባይነት የሌለው" እንደሆነ ቢገልጽም፣ "የሩሲያ ጣልቃ ገብነት በ2016 በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት የለም። መራጮች በቀላሉ ተታልለዋል ብሎ መናገርም አሳፋሪ ነው" ብሏል።

በርንሃም ሰኞ ዕለት ለተመልካቾች ይደርሳል በተባለው በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ፣ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ጀርመንን በጎበኙበት ወቅት ከቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ ጋር ስለ ሩሲያ ጣልቃ ገብነት አንስተው እንደተወያዩ ተናግረዋል።

"ከሩሲያ ወደ ጀርመን የሚሰራጩ የተሳሳቱ እና የተዛቡ መረጃዎች በእርግጥ አሉ" ብለዋል።

በመቀጠልም "እነዚህን ነገሮች አሁን በግልጽ መሰነድ አስፈላጊ ነው፤ በጀርመን እና በፈረንሳይ ያሉ መራጮች ይህ በጠላቶቻችን ማለትም በሩሲያ በኩል እንደሚሰራጭ እንዲረዱ ለማድረግ እችላለሁ ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሲያ የ2016ቱን የብሬግዚት ሕዝብ ውሳኔ ላይ ጫና ለማድረግ እንደፈለገች ለመጀመሪያ ጊዜ ቢናገሩም፣ ክሬምሊን በዩኬ ፖለቲካ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ስለምታደርገው ጥረት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ሲሰጡ ቆይተዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 የፓርላማው የስለላ እና የደኅንነት ኮሚቴ በዩኬ ምርጫዎች እና በሕዝበ ውሳኔ ላይ የሩሲያ ጣልቃ ገብነትን የሚመለከት ሪፖርት አውጥቷል።

ሪፖርቱ ሩሲያ የአውሮፓ ኅብረት ሕዝበ ውሳኔ ውጤቶች ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ሞክራ እንደሆነ ግልጽ የሆነ መደምደሚያ ባይደርስም፤ በተከታታይ መንግሥታት ስጋቱን ሙሉ በሙሉ ለመገምገም ወይም ለማስቀረት ባለመቻላቸው ተችቷል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪፖርቱን አጣጥለው "ሩሲያ ጠል" ሲሉ ጠርተውታል። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ሩሲያ በሌሎች አገሮች ምርጫ ውስጥ ጣልቃ አልገባችም ብለዋል።