ሩሲያ ዩክሬንን በሚሳኤል ከመታች በኋላ ፑቲን ምዕራባውያንን አስጠነቀቁ

በሚሳኤል የተመታ ሕንጻ

የፎቶው ባለመብት, State Emergency Service of Ukraine

ሩሲያ በምሥራቅ ዩክሬን በሚገኘው ድኒፕሮ ከተማ ጥቃት ያደረሰችው “በአዲስ የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል” መሆኑን የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ።

ኦሬሽኒክ በመባል የሚታወቀው ሚሳኤል የተተኮሰው ዩክሬን የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደምን መሣሪያ በመጠቀም ሩሲያ ውስጥ ጥቃት በማድረሷ ነው ብለዋል።

መሣሪያቸው በዩክሬን ጥቅም ላይ እንዲውል የፈቀዱ አገራትን ወታደራዊ መቀመጫዎች ሩሲያ እንደምትመታም ፑቲን ተናግረዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ፣ ሩሲያ አዲስ ሚሳኤል መጠቀሟ “የጦርነቱን መስፋትና የጭካኔውን መጠን” ያሳያል ብለዋል።

“ሩሲያ የሰላም ፍላጎት እንደሌላት ተጨማሪ ማሳያ ነው። ፑቲን ጦርነቱን እያስረዘመ ብቻ ሳይሆን ሰላም የሚፈልጉ ሰዎች ፊት ላይ ምራቅ እየተፋ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ሚሳኤሉ አህጉር አቋራጭ እንደሆነ ዘለንስኪ ቢናገሩም ምዕራባውያን አገራት ጥርጣሬ አላቸው።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል “ሙከራ ላይ ያለ መካከለኛ ርቀት የሚወነጨፍ ሚሳኤል ተተኩሷል” ብሏል።

ሩሲያ የዚህ ዓይነት መሣሪያ ጥቂት እንዳላትና ጦርነቱን እንደማይለውጥም ተገልጿል።

የፔንታጎን ምክንትል ፕረስ ሴክረተሪ ሳብሪና ሲንግ እንዳሉት ሚሳኤሉ ከመተኮሱ በፊት በኒውክሌር አደጋ ቀናሽ ስብስብ አማካይነት ለአሜሪካ መረጃ ተሰጥቷል።

ፑቲን ኒውክሌር ያልሆነ የባለስቲክ ሚሳኤል አይነት “ለሙከራ ተተኩሶ ዒላማውን መቷል” ብለዋል።

ይህንን መሣሪያ መመርመር እንደማይቻልና በሰከንድ ከ2.5 እስከ 3 ኪሎሜትር ተጉዞ ዒላማ እንደሚመታ አክለዋል።

‘ሩሲ’ በተባለው ቲንክ ታንክ የወታደራዊ ሳይንስ ኃላፊው ማቲው ሳቪል እንዳሉት፣ መሣሪያው ‘ኢስካንደርስ’ ከተባለውና እስካሁን በግጭቱ ጥቅም ላይ ከዋለው መሣሪያ የበለጠ ርቀት መጓዝ የሚችል ነው።

ፑቲን የሚጠቀሙበት መካከለኛ ርቀት የሚጓዝ ባለስቲክ ሚሳኤል ከ3,000 እስከ 5,500 ኪሎሜትር ይጓዛል።

ይህ መሣሪያ በውጊያ ካለው ሚና ይልቅ ሩሲያ ስለቀየረችው የኒውክሌር መሣሪያ አጠቃቀም ሕግ የሚያስተላልፈው መልዕክት እንደሚጎላ ባለሙያው ተናግረዋል።

ሩሲያ የተለያየ ርቀት የሚጓዙ የተለያዩ መሣሪያዎች እንዳሏት ማሳያ ነው ተብሏል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን የአሜሪካን ሚሳኤል ተጠቅማ ሩስያ ውስጥ ዒላማ እንድትመታ መፍቀዳቸው ይታወሳል። የሰሜን ኮርያ ጦር ከሩሲያ ጎን በመሰለፉ ምዕራባውያን የወሰዱት እርምጃ ነው ተብሏል።

ዩክሬም የዩኬን መሣሪያ ተጠቅማ ሩሲያ ላይ ጥቃት አድርሳለች።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከሁለት ወራት በኋላ ሥልጣነ መንበሩን ሲረከቡ ጦርነቱን በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚያቆሙ መናገራቸው አይዘነጋም።

የሩሲያ ጦር በምሥራቅ ዩክሬን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አስፋፍቶ ቀጥሏል።