በወሮበሎች የሚጠበቀው ከምድር በታች የሚገኘው የደቡብ አፍሪካ የወርቅ ማውጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ንዱሚሶ እና ሌሎች 600 ወንዶች በወሮበሎች በምትጠበቀው “ከተማ” ነው የሚኖሩት። ከተማዋ ገበያዎች አሏት፤ አልኮል የሚሸጡባቸው ቤቶችም ሞልተዋል።
ንዱሚሶ ከአንድ ትልቅ የማዕድን ቆፋሪ ኩባንያ ከተባረረ በኋላ ነው በተለምዶ “ዛማ-ዛማ” በመባል የሚታወቀውን ዓለም የተቀላቀለው።
ይህ ዓለም የሕገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች ዓለም ነው።
ማዕድን ወዳለበት ቦታ ይመጣና ቁፋሮውን ያደርጋል። ይህን የሚያደርገው በየሦስት ወሩ ነው። ወርቅም ይሁን ሌላ ማዕድን ካገኘ በድብቅ [ብላክ ማርኬት] ይሸጠዋል። ከዚህ ሽያጭ የሚያገኘው ገቢ ዳጎስ ያለ ነው። ነገር ግን አደጋውም የዚያኑ ያህል የከፋ ነው።
“ይህ ዓለም ጭካኔ የተሞላበት ነው። በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል” ሲል የ52 ዓመቱ ንዱሚሶ ለቢቢሲ ይናገራል። ስሙ ለደኅንነቱ ሲባል ተቀይሯል።
በአንደኛው የተቆፈረ ጉድጓድ አስከሬኖች እና አፅሞች ሞልተዋል። ይህ ቦታ የዛማ-ዛማ መቃብር ይባላል።
ነገር ግን እንደምንም ብለው ሕይወታቸውን ላተረፉ እንደ ንዱሚሶ ላሉ ሰዎች ይህ የማዕድን ቁፋሮ ሥራ ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ነው።
ቤተሰቡ ጆሃንስበርግ እሱ በገዛላቸው ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት። እሱ ግን ቀኑን ሙሉ ወገቡ እስኪሰበር ሲቆፍር ውሎ ከአሸዋ የተሠራ መደብ ላይ ነው የሚያርፈው።
ቤቱን የገዛው በ130 ሺህ ራንድ ነው። 7 ሺህ ዶላር ገደማ ማለት ነው። ሲገዛው ቤቱ አንድ መኝታ ብቻ ነበረው። አሁን አስፋፍቶት ሦስት መኝታ ከፍሎችን ጨምሮበታል።
ንዱሚሶ ላለፉት 8 ዓመታት በሕገ-ወጥ መንገድ የማዕድን ቁፋሮ ሲሠራ ቆይቷል። ሦስቱን ልጆቹን ከፍሎ አስተምሯል። ከሦስቱ አንዱ አሁን ዩኒቨርሲቲ ገብቷል።
“ለሚስቴ እና ለልጆቼ የሚያስፈልጋቸውን የማቀርበው እኔ ነኝ። ሌላ የማውቀው ነገር የለም” ይላል። ለበርካታ ዓመታት ሕጋዊ ሥራ ፈልጓ ሳይሳካለት ቀርቷል። አሁን የሚሠራው መኪና ከመስረቅ አሊያም ዘራፊ ከመሆን ይሻላል ይላል።
አሁን የሚሠራበት ቦታ ከጆሃንስበርግ ከተማ 145 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ ስቲልፎንቴን በምትባል ሥፍራ ናት።
ይህች ሥፍራ ከሰሞኑ መነጋገሪያ ሆናለች። አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን በዚህች ከተማ ከመሬት በታች ኑሮ ቀልሰው የሚኖሩ ሕገ-ወጥ ቆፋሪዎች ምግብ እና ውሃ እንዳያገኙ በማድረግ “እናስወጣቸዋለን” ማለታቸው ነው መነጋገሪያ የሆነው።
ፖሊስ ቦታው ከመሬት በታች 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው ይላል። አንድ የመብት ተሟጋች ቡድን የመንግሥት ውሳኔ ተቃውሞ ባቀረበው ክስ መሠረት ፍርድ ቤት ምግብ እና መጠጥ እንዲያገኙ ወስኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ንዱሚሶ ባለፈው ወር ወደ መሬት የወጣው። ዕድለኛ ሆኖ አሁን ያለው ግርግር አምልጦታል። ተመልሶ ከመግባቱ በፊት አሁን ያለውን ሁኔታ እያጤኔ ይገኛል።
መንግሥቱ ይህ ሕገ-ወጥ ቁፋሮ በታጠቁ ወሮበሎች እጅ ወድቋል በሚል ከሰሞኑ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ጀምሯል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ የማዕድን ቁፋሮው ቦታ “ወንጀል የተፈፀመበት ሥፍራ” መስሏል ብለው ነገር ግን ፖሊስ ከቆፋሪዎቹ ጋር እየተደራደረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
“የፀጥታ ሰዎች ያላቸው መረጃ እንደሚያሳየው አንዳንዶቹ ቆፋሪዎች የጦር መሣሪያ ሳይታጠቁ አይቀሩም። እነዚ ሕገ-ወጥ ማዕድን ቆፋሪዎች በታጠቁ ወሮበሎች እንደሚተዳደሩ ግልፅ ነው” ብለዋል።
ንዱሚሶ እና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን እና የጎረቤት ሀገር ሌሶቶ ዜጎች በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሠሩት የደቡብ አፍሪካ የማዕድን መስክ ባለፉት ሦስት አስርታት መቀዛቀዙን ተከትሎ ነው።
መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው ቤንችማርክ ፋውንዴሽን የጥናት ባለሙያ የሆኑት ዴቪድ ቫን ቪክ በሀገሪቱ 6 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ተጀምረው የተረሱ የማዕድን መቆፈሪያዎች አሉ ይላሉ።
“ምንም እንኳ በሰፊው ለሚያመርት ኩባንያ አትራፊ ባይሆኑም በትንሹ ለሚቆፍሩ ግን እጅግ አትራፊ ናቸው” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ንዱሚሶ የቁፋሮ ማሽን ባለሙያ ሆኖ ሲሠራ በወር የሚያገኘው 220 ዶላር አካባቢ ነበር። በአውሮፓውያኑ 1996 ነው ከወርቅ ቁፋሮ ኩባንያው የተቀነሰው።
ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት ሥራ ሲያፈላልግ ከቆየ በኋላ ነው ሕገ-ወጥ የማዕድን ቆፋሪ ለመሆን የወሰንኩት ይላል።
ቫን ቪክ እንደሚሉት በደቡብ አፍሪካዋ ጋውቴንግ ግዛት ብቻ 36 ሺህ የሚሆኑ ሕገ-ወጥ ማዕድን ቆፋሪዎች አሉ። ጋውቴንግ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት ትባላለች። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ወርቅ የተገኘው በዚህች ግዛት ነው።
“ዛማ ዛማዎች ለወራት ምንም ዓይነት ማዕድን ሳያገኙ ሊቆዩ ይችላሉ። ምግብ እና መጠጥ የሚያገኙት ከውጭ ነው። በጣም ከባድ ሕይወት ነው።”
አብዛኛዎቹ ቆፋሪዎች የጦር መሣሪያ ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት። ይህን የሚያደርጉት ከተቀናቃኝ ወሮበሎች ራሳቸውን ለመጠበቅ ነው።
ንዱሚሶ አነስተኛ ሽጉጥ እንዳለው ለቢቢሲ ይናገራል። ከዚህ በተጨማሪ ለጥበቃ በየወሩ 8 ዶላር የሚከፍላቸው የታጠቁ ቡድኖች አሉ። በተለይ ደግሞ የሌሶቶ ወሮበሎች እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ እና ጨካኝ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
ንዱሚሶ ትላልቅ ድንጋዮችን ለማፍረስ ድማሚት [ዳይናማይት] ይጠቀማል። አነስ ላሉ ቁፋሮዎች ደግሞ ዶማ እና ሌሎች መቆፈሪያዎችን ይጠቀማል።
ከሚያገኘው ማዕድን አብዛኛውን ለቡድኑ መሪ ነው የሚሰጠው። ለዚህ ሥራው በየሁለት ሳምንቱ ቢያንስ 1100 ዶላር ያገኛል። ከዚህ የቆጠበውን የተወሰነ ወርቅ ደግሞ በጥቁር ገበያ በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ያገኛል።
ዕድለኛ መሆኑን በመግለጽ ታፍነው ተወስደው ያለፈቃዳቸው እንደ ባርያ እንደሚቆፍሩ እና ለሚያወጡት ወርቅ ምንም ዓይነት ክፍያ የማይሰጣቸው እንዳሉ ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ንዱሚሶ ለሦስት ወራት ያህል ከሠራ በኋላ ወደ ከተማ ሄዶ ቤተሰቦቹን ይጎበኛል፤ ያወጣውን ወርቅ ይሸጣል። ለሁለት ሳምንታት ያክል ከቆየ በኋላ ተመልሶ ወደ ጉድጓዱ ይገባል።
“አልጋ ላይ መተኛት፤ ቤት ውስጥ የተሠራ ምግብ መብላት ያምረኛል። ንፁህ አየር መተንፈስ ይናፍቀኛል። ጨለማ ውስጥ ቆይቼ ስወጣ ብርሃኑ ስለሚከብደኝ ዓይነ-ስውር የሆንኩ ነው የሚመስለኝ።”
ከመሬት በታች ብዙ ጊዜ በማሳለፉ ቆዳው መንጣት ሲጀምር ሚስቱ ሆስፒታል እንደወሰደችው ያስታውሳል።
ንዱሚሶ ውጭ ሲወጣም አያርፍም። ያወጣውን ወርቅ አሳጥቦ ለገበያ ማቅረብ አለበት። ያወጣውን ወርቅ በግራም 55 ዶላር ነው የሚሸጠው። ገበያ ላይ አንድ ግራም 77 ዶላር ነው። ወርቅ የሚገዛው ደንበኛ አለው። ገዢው ነጭ ከመሆኑ ውጪ ብዙም መረጃ የለውም።
በዓመት በአማካይ ቢያንስ ከ15 እስከ 22 ሺህ ዶላር ይሠራል። በሕጋዊ መልክ ተቀጥሮ ሲሠራ ይከፈለው የነበረው በዓመት 2700 ዶላር ገደማ ነበር።
የወሮበሎች ቡድን መሪዎች በጣም ብዙ ገንዘብ እንደሚያገኙ ያውቃል። ነገር ግን ትክክለኛ መጠኑን ማወቅ አልቻለም።
መንግሥት ወርቅ በሕገ-ወጥ የሚገዙትን ባለሀብቶች ዒላማ ማድርግ ሲገባው ሕገ-ወጥ ቆፋሪዎች ላይ ትኩረት አድርጓል የሚል ወቀሳ ይደርስበታል።
ከመሬት በታች ያለው “ከተማ” ሁሉም ነገር አለው። ምግብ እና መጠጥ ይሸጣል። ትምባሆ፣ ባትሪ ድንጋይ እና ባትሪ እንዲሁም ሌሎች ለቁፋሮ የሚሆኑ ቁሳቁሰዎች አሉት።
ንዱሚሶ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችም ጭምር ከምድር በታች እንደሚመጡ ይናገራል። ሴቶቹ በወሮበሎች ቡድን መሪዎች አማካይነት ነው የሚመጡት።
ወደታች ሲዘልቁ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶችም እንዳሉ ንዱሚሶ ያስረዳል። ወደ ቀኝ፣ ወደ ግራ እንዲሁም ወደ ዛማ ዛማ መካነ መቃብር።
“አንዳንድ ሰዎች በተቀናቃኝ ቡድኖች ይገደላሉ። ሌሎች ደግሞ ድንጋይ ተደርምሶባቸው የሞቱ ናቸው። አንድ ወርቁን ተዘርፎ ግንባሩን በጥይት ተመትቶ የሞተ ጓደኛ ነበረኝ” ይላል።
እርግጥ ሕይወት ከምድር በታች ባሉ የማዕድን ቁፋሮ ሥፍራዎች ጭካኔ የተሞላበት ነው። ንዱሚሶ እና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ቆፋሪዎች ግን ይህን ተጋፍጠው ነው ገንዘብ የሚያገኙት።
ሌላኛው አማራጭ የሥራ አጥ ቁጥር 30 በመቶ በደረሰባት ሀገር ደሀ ሆኖ ኖሮ ደሀ ሆኖ መሞት ነው ይላሉ።















