ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል በዩክሬን ላይ መተኮሷ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ ዛሬ [ሐሙስ] ጠዋት ላይ ከደቡባዊ ከተማዋ አስትራክሃን አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤል (አይሲቢኤም) የተባለውን ረጅም ርቀት ሚሳዔል መተኮሷን የዩክሬን አየር ኃይል አስታወቀ።
አየር ኃይሉ እንዳለው በተለያዩ ዓይነት ሚሳዔሎች በተፈፀመው ጥቃት ዲኒፕሮ ክልል ዒላማ ተደርጋለች።
የክልሉ ኃላፊ በተፈፀመው በዚህ ጥቃት የደረሰው ጉዳት በውል ባይታወቅም ቢያንስ 15 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። ከተጎዱት መካከል የ16 እና የ17 ዓመት ታዳጊዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰው ዘጠኝ ሰዎች በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ፤ ነገር ግን ስላሉበት ሁኔታ አለመታወቁን የክልሉ ኃላፊ ሴሪይ ሊይሳክ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ሩሲያ ዛሬ ጠዋት ላይ በዲኒፕሮ በፈፀመችው የሚሳኤል ጥቃት የደረሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ምሥሎች የደረሱት ቢሆንም ጉዳቱን ያደረሰው የትኛው የሚሳዔል ዓይነት እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
የዩክሬን ድንገተኛ አገልግሎትም በእሳት የተያያዙ የመኖሪያ ሕንጻዎች እና የወደመ የአካል ጉዳተኞች የማገገሚያ ማዕከልን የሚያሳዩ ምሥሎችን አጋርቷል።
የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪም አገራቸው 'በአዲስ የሩሲያ ሮኬት' መጠቃቷን እና ጥቃቱ የተፈፀመበት መሣሪያ አይሲቢኤም የተባለው የባልስቲክ ሚሳዔል ዓይነት ባህርይ እንዳለው ገልጸዋል።
ሆኖም ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ወደ ዩክሬን የተተኮሰው ሚሳዔል ባሊስቲክ ሚሳዔል እንጂ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል አይደለም ማለታቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
ሩሲያ በባልስቲክ ሚሳዔል ጥቃት ፈፅማለች ስለመባሏ የተጠየቁት የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ አስተያየታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይም ስለጥቃቱ የሰጠው መረጃ የለም።
ሩሲያ ጥቃቱን መፈፀሟ ከተረጋገጠ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈፀመችበት ጊዜ ጀምሮ በአይሲቢኤም ጥቃት ስትፈፅም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, State Emergency Service of Ukraine
ከሁለት ዓመት በላይ ጊዜ ያስቆጠረው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት እየተባባሰ የመጣው የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዩክሬን የአሜሪካንን የረጅም ርቀት ሚሳዔሎች ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ዒላማዎችን እንድትመታ ከፈቀዱ ከቀናት በኋላ ነው።
አሜሪካ የአቋም ለውጥ ያደረገችው ተመራጩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ሊገቡ ሁለት ወራት በቀራቸው ጊዜ ነው።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ‘በአንድ ቀን ጦርነቱን እንደሚቋጩ’ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ የሁለቱ አገራት ጦርነት አልባት ያገኛል የሚል በጎ ተስፋ ተሰንቆ ነበር።
አሲቢኤም ሚሳዔል በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ ዒላማዎችን መምታት የሚችል ነው።
የአጭር ርቀት፣ የመካከለኛ ርቀት፣ ከመካከለኛ ከፍ ያለ እና ረጅም ርቀት የተባሉ አራት ዓይነት የባልስቲክ ሚሳዔሎች ያሉ ሲሆን፣ አይሲቢኤም ከረጅም ርቀት የባሊስቲክ ሚሳዔል ዓይነቶች የሚመደብ ነው።
ከ5500 ኪሎ ሜትሮች ርቀት በላይ መወንጨፍ የሚችል ሲሆን፣ በዓለም ላይ ያለ ማንኛውንም ቦታ መምታት ይችላል።
የዩክሬን ጦር በበኩሉ በጥቃቱ ወቅት ስድስት ኬኤች-101 ክሩዝ ሚሳዔሎችን መትቶ መጣሉን ገልጿል።
ይህ የሆነው ዋሽንግተን እንደ ኤቲኤሲኤምኤስ ያሉ ረጅም ርቀት ሚሳዔሎችን ዩክሬን እንድትጠቀምበት ከፈቀደች ከቀናት በኋላ ነው። ዩክሬንም የሩሲያን ወታደራዊ ሰፈሮች ለመምታት ይህንን ሚሳዔል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ መጠቀሟ ተዘግቧል።
በሌላ በኩል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አየር ኃይሉ ዩናይትድ ኪንግደም ሠራሽ ሁለት ክሩዝ ሚሳኤሎችን ተኩሶ መጣሉን አስታውቋል። ሆኖም ሚኒስቴሩ ይህ የሆነው መቼ እና የት እንደሆነ አልጠቀሰም።
በተያያዘ ዜናም የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ ሃንጋሪ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ የአየር መከላከያ ሥርዓት እንደምትተክል ገልጻለች።
የሃንጋሪ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እየተባባሳ በመጣው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከዩክሬን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ የአየር ጥቃት መከላከያ እንደምትተክል አስታውቋል።
ፖላንድም ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት በፈፀመችበት ወቅት የአየር ክልሏን ለመጠበቅ የራሷን ተዋጊ ጄቶች እና የኔቶን አውሮፕላንን አሰማርታለች።












