ደቡብ አፍሪካ በሺዎች ለሚቆጠሩ 'ህገ-ወጥ' ማዕድን አውጭዎች የሚደርሰውን ምግብ እና ውሃ አቋረጠች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የምግብ እና የውሃ አቅርቦት በማቋረጥ ህገወጥ ማዕድን አውጪዎችን ለማሰር ቢንቀሳቀስም ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከምድር በታች መደበቃቸው ታውቋል።
ማዕድን ቆፋሪዎች በሰሜናዊ ምዕራብ ስቲልፎንቴን ግዛት ውስጥ በሚገኝ የማዕድን ጉድጓድ ለአንድ ወር ገደማ ቆይተዋል።
አንዳንዶቹ እንደ ሌሶቶ እና ሞዛምቢክ ካሉ አገራት የመጡ ሰነድ አልባ ስደተኞች በመሆናቸው ልንባረር እንችላለን በሚል ስጋት ከባለሥልጣናት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አልሆኑም።
ሕገወጥ ማዕድን አውጪዎች “ዛማ ዛማ” (በዙሉ ቋንቋ “ዕድልን መጠቀም” ማለት ነው) በመባል የሚጠሩ ሲሆን በማዕድን በበለጸገችው አገር በተተዉ የማዕድን ማውጫዎች ውስጥ ይሠራሉ። ህገ ወጥ ማዕድን ማውጣት የደቡብ አፍሪካ መንግስትን በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለኪሳራ ይዳርገዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የደቡብ አፍሪካ ማዕድን ማውጫዎች ተዘግተው ሠራተኞቻቸው ተባረዋል።
የማዕድን ቆፋሪዎቹ እና ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ከድህነት ለማምለጥ ማዕድኑን እያወጡ ለጥቁር ገበያ ይሸጣሉ።
አንዳንዶች ከመሬት በታች ወራትን ያሳልፋሉ። ለማዕድን አውጪዎቹ ምግብ፣ ሲጋራ እና የበሰለ ምግብ የሚሸጡ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችም አሉ።
የአካባቢው ነዋሪዎች የማዕድን ቆፋሪዎቹን እንዲረዳ ለመንግስት ባለሥልጣናት ተኣጽኖ ቢያቀርቡም ፈቃደኛ አልሆኑም።
"እኛ እናስገድዳቸዋል። እነሱም ይወጣሉ። ለወንጀለኞች እርዳታ አንልክም። ወንጀለኞች ድጋፍ ሳይሆን ክስ ነው የሚያስፈልጋቸው" ሲሉ የፕሬዝዳንቱ ሚንስትር ኩምቡድዞ ንትሻቭኒ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።
ጉድጓዶች ውስጥ ያሉት አንዳንድ ማዕድን ቆፋሪዎች የታጠቁ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ፖሊሶች ወደ ማዕድን ማውጫው ለመግባት እያመነቱ ነው።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኮርፖሬሽኖችን ከሚከታተለው ቤንችማርክስ ፋውንዴሽን ባልደረባ ቡሲ ታባን በበኩላቸው የተወሰኑት የወንጀል ቡድኖች ወይም "ምልምሎች" ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም ተናግረዋል።
ምንም አይነት አቅርቦት ከሌለ በማዕድን ጉድጓዶች ውስጥ ያለው ሁኔታ አስከፊ ነው ተብሏል።
"ከዚህ በኋላ የህገወጥ ማዕድን ማውጫዎች ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የሰብአዊ ቀውስ ሆኗል" ሲሉ ታባኒ ተናግረዋል።
የማህበረሰቡ መሪ ቴምቢሌ ቦትማን ሐሙስ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ በጎ ፈቃደኞች ከማዕድን ማውጫው ውስጥ አስከሬን ለማውጣት ገመድ እና የደህንነት ቀበቶ ተጠቅመዋል።
"የበሰበሰው የአስከሬን ጠረን በጎ ፈቃደኞቹን ለጭንቀት ዳርጓቸዋል" ብለዋል።
ግለሰቡ እንዴት እንደሞተ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ባለሥልጣናቱ ምግብ እና ውሃ እንዳይገባ ቢከለክሉም የአካባቢው ነዋሪዎች አንዳንድ ቁሳቁሶችን በገመድ እንዲልኩ በጊዜያዊነት ፈቅደዋል።
ቦትማን አክለውም ከማዕድን አውጪዎቹ ጋር በወረቀት ማስታወሻዎች ይነጋገሩ እንደነበር ተናግረዋል።
ፖሊሶች ማዕድን አውጪዎቹ እንዲወጡ ለማድረግ ሲል የማዕድን ጉድጓዱን መግቢያ እና መውጫዎችን ዘግቷል።
ይህ የቫላ ኡምጎዲ ወይም "ጉድጓዱን ዝጋ" የሚባለው ህገወጥ ማዕድን ማውጣትን ለመግታት የሚደረግ ስልት አካል ነው።
አምስት ማዕድን አውጪዎች ረቡዕ ዕለት በገመድ ተጎትተው ወጥተዋል። ሁሉም ዝለው እና ደካክመው ነበር ተብሏል። የሕክምና ባለሙያዎች ካዩዋቸው በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ባለፈው ሳምንት አንድ ሺህ ገደማ ማዕድን አውጪዎች ወጥተው ታስረዋል።
ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከጉድጎድ ወጥተው የሕክምና እርዳታ የማይፈልጉትን በቁጥጥር ስር ለማዋል አሁንም በቦታው ተሰማርተው ይገኛሉ።
"ፖሊስ እንደሚለው ቀላል አይደለም። አንዳንዶቹ ለህይወታቸው እየፈሩ ነው" ብለዋል ታባን።
ብዙ ማዕድን አውጪዎች ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ በሚል ደህንነታቸው ባልተጠበቁ ጉድጓዶች ውስጥ ወራትን ያሳልፋሉ።
“ለአብዛኛዎቹ የዕለት ምግባቸውን ለማግኘት ብቸኛው የሚያውቁት ሥራ ነው” ብለዋል ታባን።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአካባቢው ነዋሪዎችም ከማዕድን ማውጫው እንዲወጡ ለማሳመን ሞክረዋል።
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ኤሚሊ ፎትሶአ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት “እነዚያ ሰዎች መውጣት አለባቸው። ምክንያቱም እዚያ ወንድሞች፣ ልጆች እና አባቶች አሉን። ልጆቻችን እየታገሉ ነው።”
የደቡብ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የማዕድን አውጪዎችን ምግብ እና ውሃ በመከልከሉ ፖሊስ ላይ ምርመራ እከፍታለሁ ብሏል።
የመንግስት ተግባር በህይወት የመኖር መብት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋትም አለው።
የሚኒስትር ንትሻቭሄኒ አስተያየት ከደቡብ አፍሪካውያን የተለያዩ አስተያየቶችን እንዲሰነዝሩ ምክንያት ሆኗል። አንዳንዶች የመንግስትን አካሄድ አድንቀዋል።
"ይህንን ወድጄዋለሁ። በመጨረሻም መንግሥታችን ከእነዚህ ከባድ ጉዳዮች ላይ እየሸሸ አይደለም። ቆራጥነት ይህችን አገር ይጠቅማል" ሲል አንድ ግለሰብ ኤክስ ላይ አስፍሯል።
ሌሎች ደግሞ ተግባሩን ኢሰብዓዊ እንደሆነ ገልጸዋል።
"በእኔ እይታ የሚኒስትሩ ንግግር አሳፋሪ እና አደገኛ የጥላቻ ንግግር ነው" ሲል ሌላ ግለሰብ ጽፏል።
ሌላ ግለሰብ ደግሞ "ወንጀለኞች ቢሆኑም ግን መብት አላቸው" ሲል አስፍሯል።
ህገ ወጥ ማዕድን ማውጣት በብዙ የደቡብ አፍሪካ የማዕድን ማውጫ ከተሞች ትርፋማ ንግድ ነው።
ባለፉት አስር ወራት ወደ 400 የሚጠጉ ሽጉጦች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥይቶች፣ አልማዞች እና ገንዘቦች ከህገ ወጥ ማዕድን አውጪዎች ተወርሰዋል።
የተጠናከረው የፖሊስ እና ወታደራዊ ዘመቻ ከባድ የአካባቢ ተጽዕኖ ያለውን ተግባር ለማስቆም ያለመ እንቅስቃሴ አካል ነው።












