ሠራዊቷ ከሶማሊያው አዲሱ የሰላም ተልዕኮ ውጪ ነው የተባለችው ኢትዮጵያ አልሻባብን በማዳከም እንደምትቀጥልበት አስታወቀች

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አርማ

የፎቶው ባለመብት, Ministry Of foreign Affairs

በሶማሊያ ከሚሰማራው አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውጪ መደረጓ የተገለጸው ኢትዮጵያ አልሻባብን በማዳከም ተግባር እንደምትቀጥልበት አስታወቀች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ኢትዮጵያ የሶማሊያውን ታጣቂ ቡድን አልሻባብን ለማሽመድመድ ለዘመናት ያደረገችው ዘመቻ እንደሚቀጥል የተናገሩት ሐሙስ ኅዳር 5/2017 ዓ.ም. ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።

አምባሳደሩ “አልሻባብ ብሔራዊ ደኅንነታችን ላይ ስጋት የማይሆንበት ደረጃ እስኪደርስ እንዲሁም እስካሁን የተመዘገቡ ድሎች እንዳይቀለበሱ አልሻባብን ለማዳከም የተሰሩ ወሳኝ ሥራዎች በማንኛውም መንገድ ይቀጥላሉ” ብለዋል።

የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል አሰማርታ የምትገኘው ኢትዮጵያ ሠራዊቷ በሶማሊያ ከሚሰማራው አዲሱ ተልዕኮ ውጪ መደረጉን ከሰሞኑ የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

በመጪው ጥር የተሰጠው ውክልና የሚጠናቀቀውን የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ (አትሚስ) የተባለውን የሰላም አስከባሪ ኃይልን በመተካት፣ ቦታውን በሚረከበው የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ (አውሰም) ውስጥ የኢትዮጵያ ጦር እንደማይካተት ሶማሊያ ይፋ አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ሠራዊት በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ እንዳይካተት መደረጉን አስመልክቶ የመንግሥታቸው አቋም ምን እንደሆነ ከጋዜጠኞች የተጠየቁት ቃል አቀባዩ ቀጥተኛ ምላሽ ባይሰጡም ኢትዮጵያ ቡድኑን የማዳከም ተግባሯን ትቀጥልበታለች ብለዋል።

ሆኖም ከዚህ ቀደም ከአትሚስ በኋላ በሚሰማራው ኃይል የኢትዮጵያ ሠራዊት አይካተትም መባሉን አስመልክቶ ቢቢሲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀድሞ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላን በጠየቃቸው ወቅት “ለእኛ ቀላል ነው ኃይላችንን ስበን ‘በፈር ዞን’ [የጦር መጠባበቂያ ቀጣና] እንፈጥራለን” ብለው ነበር።

ነገር ግን ለኢትዮጵያ የሚያሰጋ ነገር ካለ አገሪቷ እጇን አጣጥፋ እንደማትቀመጥ ገልጸው“ለእኛ የብሔራዊ ደኅንነት የሚያሰጋ ከሆነ የማንንም ፍቃድ የምንጠብቅበት ነገር አይደለም፤ የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ቃል አቀባዩ ለቢቢሲ በወቅቱ መናገራቸው ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አምባሳደር ነቢያት በዛሬው [ሐሙስ] መግለጫቸው ኢትዮጵያ ለቀጣናው ያደረገችውን አስተዋጽኦን ለጋዜጠኞች የተናገሩ ሲሆን “አሸባሪው አልሻባብ በቀጣናው የጋረጠውን ስጋት በመግታት ረገድ ኢትዮጵያ እየተጫወተችው ያለው ቁልፍ ሚናን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያውቀው እና የሚገነዘበው ነው” ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ይህንን ቢሉም ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ሠራዊት የሶማሊያ ስምሪት የአልሻባብን እንቅስቃሴ እንዲጨምር ያደረገ ነው ሲል የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ መውቀሱ ይታወሳል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአገሪቱ ወታደሮቻቸውን ካሰማሩ አምስት አገራት በተለየ የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ በማተኮር “ያለፉ የኢትዮጵያ ሠራዊት ስምሪቶች የአል ሻባብ እንቅስቃሴ እንዲጨምር ያደረገ እና ጥቂት መሻሻል ያመጣ ነው” በማለት የተቸ ሲሆን፣ በዚህም ቀጣይ የሰላም አስከባሪ ስምሪት ከሶማሊያ የፀጥታ እና የልማት ግቦች ጋር በማጣጣም ስልታዊ ምርጫ ማካሄድ አስፈላጊ ነው ማለቱ ይታወሳል።

ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባ የባሕር ጠረፍ ስምምነት ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ቁርሾ ውስጥ የገባችውን ሶማሊያን አስመልክቶም አምባሳደር ነቢያት “ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የማይነጣጠሉ ጎረቤት አገራት እንደመሆናቸው መጠን ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ራዕይዋን በቀጣይነት ቀጠናዊ ውህደትን በሚያጠናክር መልኩ ተግባራዊ ታደርጋለች” ብለዋል።

ከሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት ምክንያት ሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሰላም ተልዕኮው ጊዜው ሳይጠናቅቅ እንዲወጡ በመግለጫዎች ማስታወቋ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ስምምነት አዲሱ ተልዕኮ ከሚወሰንበት፣ ከሰኔ መጨረሻ በፊት ካልሰረዘች በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ስር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሑሴን አሊ ከዚህ ቀደም ገልጸው ነበር።

ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።

የሶማሊያ መንግሥት ዜና ወኪል (ሶና) እና የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ከሰሞኑ እንደገዘቡት የሶማሊያው የመከላከያ ሚኒስትር አብዲካዲር ሞሐመድ ኑር የኢትዮጵያ ሠራዊት ከቀጣዩ ተልዕኮ ውጪ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት በሶማሊያ በሚሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውስጥ “የኢትዮጵያ ኃይሎች ተሳታፊ እንደማይሆኑ እናረጋግጣለን” በማለት ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።

ለዚህ የሶማሊያ ውሳኔ ምክንያቱም “ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን በመጣሷ” መሆኑን በማመልከት፣ በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ ሠራዊታቸውን የሚያሰማሩ አገራት ዝርዝርም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ግብፅ በሶማሊያ ለሚሰማራው አዲስ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ወታደሮች ለማዋጣት ያቀረበችውን ሃሳብ የአፍሪካ ኅብረት በበጎ እንደሚቀበለው ማስታወቁ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በዚህ ስፍራ የባሕር ኃይል ሰፈር እንደምታቋቁም እና በምትኩም ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች መባሉን ተከትሎ እንደ ግዛቷ አካል የምታያት ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።