ሶማሊያ የኢትዮጵያ ሠራዊት በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውስጥ እንደማይካተት አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, AMISOM
የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ሠራዊት ከአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውጪ መሆኑን በይፋ አስታወቁ።
ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ሶማሊያ ውስጥ ሰላም ሲያስከብር የቆየው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቱ እንዲወጣ እንደሚፈልግ የሶማሊያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ለዚህ የሶማሊያ ውሳኔ ዋነኛ ምክንያቱ ኢትዮጵያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት እንዲሁም የአገርነት ዕውቅናን ለመስጠት ስምምነት ላይ መድረሷ ነው።
ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመጣስ ሲከሱ የከረሙት የአገሪቱ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ከፍተኛ የሶማሊያ ባለሥልጣናት ባለፉት ወራት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከግዛታቸው እንዲወጡ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በመጪው ጥር የተሰጠው ውክልና የሚጠናቀቀውን የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ (አትሚስ) የተባለውን የሰላም አስከባሪ ኃይልን በመተካት፣ ቦታውን በሚረከበው የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ (አውሰም) ውስጥ የኢትዮጵያ ጦር እንማይካተት ሶማሊያ ይፋ አድርጋለች።
የሶማሊያ መንግሥት ዜና ወኪል (ሶና) እና የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደገዘቡት የሶማሊያው የመከላከያ ሚኒስትር አብዱካዲር ሞሐመድ ኑር የኢትዮጵያ ሠራዊት ከቀጣዩ ተልዕኮ ውጪ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት በሶማሊያ በሚሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውስጥ “የኢትዮጵያ ኃይሎች ተሳታፊ እንደማይሆኑ እናረጋግጣለን” በማለት ሚኒስትሩ ሞቃዲሾ ውስጥ ቅዳሜ ዕለት ተናግረዋል።
ለዚህ የሶማሊያ ውሳኔ ምክንያቱም “ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን በመጣሷ” መሆኑን በማመልከት፣ በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ ሠራዊታቸውን የሚያሰማሩ አገራት ዝርዝርም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሶማሊያ ውስጥ ለዓመታት ተሰማርተው የቆዩት ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ቀንድ እና የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ወታደሮች ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለው ከሚባለው አልሻባብ ጋር ሲዋጉ እና የሶማሊያን መንግሥት ሲጠብቁ መቆየታቸው ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ሦስት ሺህ እንዲሁም ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት ደግሞ ወደ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ አሰማርታ እንደምትገኝ ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, atmis
የሶማሊያው የመከላከያ ሚኒስትር በቴሌቪዥን በቀረበ ቃለ ምልልስ ላይ በሶማሊያ ውስጥ ወታደሮች ካሏቸው አገራት መካከል “እስካሁን እንደምናውቀው በአዲሱ [የአፍሪካ ኅብረት] ተልዕኮ ውስጥ የማትሳተፈው አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት” ሲሉ የመንግሥታቸውን ውሳኔ አሳውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በደረሰችው ስምምነት መሠረት ውዝግብ ውስጥ በገቡት ሁለቱ አገራት መካከል ያለው አለመግባባት እየተካረረ ሲሆን፣ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ፍጥጫ ውስጥ የቆየችው ግብፅ በሶማሊያ በኩል ጣልቃ መግባቷ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረትን ፈጥሯል።
ግብፅ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት በመቃወም ከሶማሊያ ጎን እንደምትቆም ከመግለጽ ባሻገር፣ ሁለቱ አገራት የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ተፈራርመው ባለፉት ወራት በባሕር እና በአየር የግብፅ የጦር መሳሪያ ድጋፎች ወደ ሶማሊያ መግባታቸው ይታወቃል።
በተጨማሪም ግብፅ በሶማሊያ ውስጥ በሚሰማራው የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ ወታደሮቿን ለማካተት ፍላጎት እንዳለት ገልጻ በሶማሊያ ተቀባይነት እንዳገኘ ሲዘገብ ቆይቷል። ይህ ሁኔታ የደኅንነት ስጋት እንሚደቅንባት እና በቀጣናው አለመረጋጋትን እንደሚፈጥ በመግለጽ ኢትዮጵያ ተቃውሞዋን አሰምታለች።
በአዲሱ የአፍሪካ ተልዕኮ ውስጥ ወታደሮቿን ለማሰማራት ፈቃደኛ የሆነቸው እና ሂደቱ ስጋት የፈጠረባት ኢትዮጵያ ተልዕኮው የአካባቢው አገራት እና በሶማሊያ ለተሰማራው ኃይል ወታደሮችን ያዋጡ አገራትን “ተገቢ ስጋት ከግንዛቤ ያስገባ መሆን አለበት” በማለት ማሳሰቧ ይታወሳል።
ሶማሊያ አሁን በይፋ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውጪ መሆኑን ከመግለጿ ከሳምንታት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቀጣይ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ስምሪት ውስጥ ሶማሊያ የየትኞቹ አገራት ወታደሮች መካተት እንዳለባቸው እንደምትወስን ገልጾ ነበር።
ይህም ወታደሮች የሚያዋጡ አገራትን በተመለከተ የሚሰጠው ውሳኔ “ከሶማሊያ ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነቷ ከማስከበር ጋር የተጣጣመ ሊሆን ይገባል” ሲል ቀጣይ የሶማሊያ መንግሥት ውሳኔም ጠቁሞ ነበር።
የሶማሊያው የመከላከያ ሚኒስትር አብዱካዲር ሞሐመድ ኑር ከመጪው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ጀምሮ ለአራት ዓመታት በሚቆየው አዲሱ ተልዕኮ ውስጥ የሚካተቱ አገራትን ለመጋበዝ መንግሥታቸው ሂደቱን ይፋ እንሚያደርግም ገልጸዋል።
“ጊዜው ሲደርስ ከቀደሙት አገራት መካከል በአዲሱ ተልዕኮ ውስጥ የሚሳተፉ እና የማይካተቱ አገራትን እንዲሁም አዲስ የሚገቡ መንግሥታትን እናሳውቃለን” ብለዋል።
በቀደመው እና በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ መካከል “ጉልህ ልዩነት” እደሚኖር ያመለከቱት የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ ይህም የሚሰማሩ ወታደሮች ቁጥር እንደሚቀንስ እንዲሁም የሚሰማሩባቸው ቦታዎችም ውስን እንሚሆኑ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ ሠራዊታቸውን አሰማርተው የሚገኙት አገራት ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ቡሩንዲ እና ኡጋንዳ ናቸው።















