‘የኢትዮጵያ ሠራዊት ስምሪት የአል ሻባብ እንቅስቃሴ እንዲጨምር አድርጓል’ - ሶማሊያ

የፎቶው ባለመብት, AP
ባለፉት ጊዜያት በሶማሊያ ውስጥ ለሰላም ማስከበር የተደረገው የኢትዮጵያ ሠራዊት ስምሪት የአል ሻባብ እንቅስቃሴ እንዲጨምር አድርጓል ሲል የሶማሊያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ወቀሰ።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ከግዛቷ እንዲወጡ ስትጠይቅ የቆየችው ሶማሊያ ከጥቂት ወራት በኋላ የሚያበቃውን የሰላም አስከባሪ ተልዕኮን ተከትሎ በምትኩ በሚሰማራው ኃይል ውስጥ የየትኛው አገር ወታደሮች እንደሚሳተፉ የምትመርጠው ራሷ መሆኗን ገልጻለች።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ በአገሪቱ ወታደሮቻቸውን ካሰማሩ አምስት አገራት በተለየ የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ በማተኮር ተልዕኮው የአል ሻባብ እንቅስቃሴ ከፍ እንዲል ከማድረግ ባሻገር ያስገኘው ለውጥ ውስን ነው ብሏል።
በዚህም የተለያዩ ምክንያቶችን ያስቀመጠው የሶማሊያ መንግሥት በቀጣይ በተተኪነት በአገሩ የሚሠማሩትን ሰላም አስከባሪዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲካተቱ እንደማይፈለግ ባወጣው መግለጫ ላይ ፍንጭ ሰጥቷል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀጣይ በሶማሊያ ከሚሰማራው የአፍሪካ ኅብረት አረጋጊ ተልዕኮ አንጻር የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የኢትዮጵያ ሚና በሚል ረቡዕ አመሻሽ ባወጣው መግለጫ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ጠቅሷል።
በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሶማሊያ የተሰማሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲወጡ ባለፉት ወራት የሶማሊያ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።
በመጪው ጥር የሚጠናቀቀውን የሰላም አስከባሪውን ውክልና ተከትሎ በሚተካው አዲስ ተልዕኮ ውስጥ አገራት የሚኖራቸውን ተሳትፎ በተመለከተ የሶማሊያ መንግሥት የበላይ በመሆን በአገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ በማተኮር የተልዕኮውን ሚና እንደሚመራ አሳውቋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በቅርቡ የተናጠል እርምጃ መውሰዷን በመጥቀስ ለአብነትም ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚቃረን ነው በማለት ዋነኛው ትኩረቱ ኢትዮጵያ ላይ መሆኑን አመልክቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ ኢትዮጵያ “ከሰሜናዊ ግዛት ጋር የደረሰችው ሕገወጥ ስምምነት፣ ሉዓላዊነታችንን የሚጥስ እና ለሰላም ማስከበሩ ተግባር አስፈላጊ የሆነውን መተማመን የሚሸረሽር ነው” ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Villa Somalia
በተጨማሪም “ያለፉ የኢትዮጵያ ሠራዊት ስምሪቶች የአል ሻባብ እንቅስቃሴ እንዲጨምር ያደረገ እና ጥቂት መሻሻል ያመጣ ነው” በማለት የተቸ ሲሆን፣ በዚህም በቀጣይ የሰላም አስከባሪዎች ስምሪት ከሶማሊያ የፀጥታ እና የልማት ግቦች ጋር በማጣጣም ስልታዊ ምርጫ ማካሄድ አስፈላጊ ነው ብሏል።
በዚህም በቀጣይ ምዕራፍ በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪዎች ስምሪት “ሶማሊያ እንደ ሉዓላዊ አገር የየትኞቹ አገራት ወታደሮች መካተት እንዳለባቸው የመወሰን ሥልጣን አላት” ብሏል።
ይህም ወታደሮች የሚያዋጡ አገራትን በተመለከተ የሚሰጠው ውሳኔ “ከሶማሊያ ብሔራዊ ጥቅምን እና ሉዓላዊነቷን ከማስከበር ጋር የተጣጣመ ሊሆን ይገባል” ሲል ቀጣይ ሊሆን የሚችለውን ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊያ በር ለማግኘት ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟን ተከትሎ ስምምነቱ ሉዓላዊነቷን የሚጋፋ ድርጊት መሆኑን በመግለጽ ሶማሊያ ስትቃወመው ቆይታለች።
በተጨማሪም 20 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በሶማሊያ ተሰማርተው የአገሪቱን መንግሥት ሲጠብቁ እና ሲደግፉ የቆዩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከግዛታቸው እንዲወጡ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ አዲሱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስምሪት የአካባቢውን አገራት እና ወታደሮች ያሰማሩ አገራትን “ስጋት ከግምት ማስገባት አለበት” በማለት ማሳሰቧ ይታወሳል።
አሁን የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው በቀጣይ በሚኖረው የሰላም አስከባሪ ስምሪት ውስጥ ኢትዮጵያ ሚና እንዲኖራት የሶማሊያ መንግሥት እንደማይፈለግ አመልክቷል።
በሶማሊያ ከተሰማሩ ሰላም አስከባሪዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የምታበረክተው ኢትዮጵያ፣ ስምሪቱን የሚያስተባብረው የአፍሪካ ኅብረት እና ድጋፍ የሚሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስካሁን በዚህ ዙሪያ ያሉት ነገር የለም።
ይህ የሶማሊያ መግለጫ የወጣው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከኢትዮጵያ በስተቀር በሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ያላቸውን ኬንያን፣ ኡጋንዳን፣ ቡሩንዲን እና ጂቡቲን ከጎበኙ በኋላ ነው።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ውስጥ ቢያንስ ሦስት ሺህ የሚሆኑት ወታደሮቿን በአፍሪካ ኅብረት በኩል ለሰላም ማስከበር ያሰማራች ሲሆን፣ ከአምስት አስከ ሰባት ሺህ የሚሆኑ ወታደሮች ደግሞ በሁለቱ አገራት ስምምነት በተለያዩ የሶማሊያ ግዛቶች ውስጥ ይገኛሉ።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የደኅንነት ባለሙያዎች እና ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያ ሠራዊት ለቆ የሚወጣ ከሆነ የሶማሊያ ኃይሎች የሚፈጠረውን ክፍተት የመሙላት አቅም ስለማይኖራቸው የበለጠ አለመረጋጋት ሊከሰት ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን መግለጻቸውን ዘግቦ ነበር።















