ኢትዮጵያ በልዩ መልዕክተኛ ደረጃ ለነበረው የሐርጌሳ ቆንስላ አምባሳደር ሾመች

የፎቶው ባለመብት, Presidency of Republic of Somaliland
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር ነው በተባለ መንገድ በልዩ መልዕክተኛ ደረጃ ለነበረው የሐርጌሳ ቆንስላ አምባሳደር ሾመች።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ ለሚገኘው ቆንስላ ጄነራል ጽህፈት ቤት የነበራት ልዩ መልዕክተኛ እንጂ አምባሳደር አልነበረም።
አምባሳደር ተሾመ ሹንዴ ሐሚቶ ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም. የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አቅርበዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩት ልዩ መልዕክተኛ በአምሳደር መተካታቸው በአዲስ አበባ እና ሐርጌሳ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት የበለጠ ያጠናክራል ተብሏል።
በሶማሊላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሹመት የተሰማው በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት አይሎ ግብጽን ወደ ቀጠናው ካመጣ በኋላ ነው።
ሶማሊያ የግዛቷ አንድ አካል አድርጋ የምትቆጥራት ሶማሊላንድ፤ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችው ስምምነት ሉዓላዊነቴን እና የግዛት አንድነቴን የሚጥስ ነው በማለት ስምምነቱን አጥብቃ ስትቃወም ቆይታ ጉዳዩ በቀጠናው ወዳሉ አገራት ጨምር ውስዳለች።
በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ውጥረት ውስጥ ከገባቸው ግብጽ ጋር ወታደራዊ ስምምነት መፈራረሟ ጭምር ይታወሳል።
ይህን ወታደራዊ ስምምነት ተከትሎ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መንግሥታትን ባስቆጣ እርምጃ በሶማሊያ መንግሥት ይሁንታ የግብጽ ጦር ሞቃዲሾ ገብቷል።
ከቆንስላ ወደ ኤምባሲ
በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ተከትሎ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሶማሊያ በሐርጌሳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ እንዲዘጋ ትዕዛዝ አስተላልፋ ነበር።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በተቃራኒው በሐርጌሳ የነበሩትን ልዩ መልዕክተኛ ደሊል ከድር በአምባሳደር ተሾመ ሹንዴ ተክታለች።
አዲሱ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ወደ አምባሳደርነት ደረጃ ከፍ ያሉት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በሰኔ ወር ለ24 ዲፕሎማቶች የባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና አምባሳደርነት ሹመት በሰጡበት ወቅት ነው።
የቀድሞው የሶማሊላንድ ልዩ መልዕክተኛ ደሊል ከድርም በተመሳሳይ የሙሉ ባለስልጣን አምባሳደርነት ሹመት አግኝተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሐርጌሳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ወደ ኤምባሲ ደረጃ ከፍ እንዲል ከውሳኔ መደረሱን የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ከዚህ ቀደም መናገራቸው ይታወሳል።
ሶማሊላንድ 33ኛ የነጻነት በዓሏን ግንቦት 10/2016 ዓ.ም. ባከበረች ወቅት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ በአገራቸው የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ወደ ኤምባሲ ማደጉን መናገራቸውን የሶማሊላንድ የመረጃ፣ የባህል እና የብሔራዊ መመሪያ ሚኒስትር አሊ ሐሰን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ግንኙነታቸው የሚያጠናከሩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ያሉት ከሶማሊያ ጋር ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ በሚገኝበት ወቅት ነው።
ሶማሊያ ከጥቂት ወራት በፊት በአዲስ አበባ የሚገኘውን አምባሳደሯን ለምክክር ጠርታ በሞቃዲሾ የሚገኙትን የኢትዮጵያ አምባሳደር ከአገር ማባረሯ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪም ሶማሊያ በሶማሊላንድ መዲና ሐርጌሳ እና እንዲሁም በፑንትላንድ መዲና ጋሮዌ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላዎችን በ7 ቀናት እንዲዘጉ ትዕዛዝ አስተላልፋ ነበር።
ይሁን እንጂ ሁለቱም ተቋማት ሳይዘጉ ቆይተው ይልቁንም በሐርጌሳ የሚገኘው ቆንስላ ወደ ኤምባሲ ማደረጉ ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ አዲስ አምባሳደር ወደ ሐርጌሳ መላኳ “በሁለቱ አገራት” መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን የሶማሊላንድ ምክትል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ርሆዳ ኤልሚ በኤክስ ገጻቸው አስፈረዋል።












