ሶማሊላንድ በግብጽ ጦር መሰማራት የቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ ሲወድቅ በዝምታ አልመለከትም አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነችው ሶማሊላንድ የግብጽ ጦር በሶማሊያ ተሰማርቶ የቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ ሲወድቅ በዝምታ አልመለከትም አለች።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በቅርቡ የግብጽ ጦር በሶማሊያ እንዲሰማራ መደረጉ ለሶማሊያ እና ለአጠቃላዩ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ደኅንነት አሳሳቢ ነው ብሏል።
ሶማሊላንድ ይህን ያለችው ከጥቂት ቀናት በፊት የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች ሶማሊያ መድረሳቸውን ተከትሎ ከኢትዮጵያ በኩል ተመሳሳይ አቋም ከተንጸባረቀ በኋላ ነው።
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው “ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም” ማለቱ ይታወሳል።
የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነሐሴ 22/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “የሶማሊያ መንግሥት ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ማለቱ ይታወሳል።
የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች በሶማሊያ መዲና በሚገኘው አየር ማረፊያ ከመታየታቸው ከሳምንታት በፊት ካይሮ እና ሞቃዲሾ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ነው።
ማህብራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት በወጡ ተንቃሳቃሽ ምስሎች የግብጽ ዓርማ ያለባቸው ሁለት ሲ-130 የተባሉ ወታደራዊ ዕቃ አጓጓዥ አውሮፕላኖች በሞቃዲሹ አየር ማረፊያ ታይተዋል።
የባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ የንግድ መተላለፊያ ወደብ ለማግኘት እና የባሕር ኃይሏን ለማጠናከር ካላት ፍላጎት የተነሳ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈረሟ ከሞቃዲሾ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ ከትቷት ቆይቷል።
ሞቃዲሾ የአዲስ አበባ እና ሐርጌሳ ስምምነት ሉዓላዊነቴን እና የግዛት አንድነቴን የሚጥስ ነው ስትል ጠንከር ያለ ተቃውሞ ስታሰማ ቆይታለች።
ግብጽ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ትብብር ስምምነት ከመፈራረሟ በተጨማሪ ካይሮ ሠራዊቷን ለሰላም ማስከበር የኢትዮጵያ ጎረቤት ወደ ሆነችው ሶማሊያ ለመላክ ጥያቄዋን በይፋ አቅርባለች።
የአፍሪካ ኅብረት እንዲሁ ግብፅ ጦር ሠራዊቷን ለሰላም ማስከበር ሥራ ወደ ሶማሊያ ለመላክ ያቀረበችውን ጥያቄ በበጎ እንደሚቀበለው አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ግን የአፍሪካ ህብረት ሽግግር ተልዕኮን የሚተካው የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱን ይህም ለአዲስ አበባ አሳሳቢ እንደሆነ ይገልጻል።
በሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን በሶማሊያ እንድታሰማራ ከተጠየቀችበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል ጦሯን አሰማርታ ትገኛለች።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከቀርብ ጊዜያወት ወዲህ የመከላከያ ሰራዊት መልካም ስምና ዝናን እንዲሁም መስዋዕትነት የሚያጠለሹ መግለጫዎች ወጥተዋል ሲልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ተችቷል።
“ሶማሊላንድ የግብጽ ጦር በሶማሊያ መሰማራትን ትቃወማለች”
የግብጽ ጦር በሶማሊያ መስፈርን በመቃወም የሶማሊላንድ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የካይሮ ጦር በአፍሪካ ቀንድ መገኘትን አጥብቆ ተቃውሟል።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ትናንት ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ “በየትኛውም ምክንያት የውጪ ኃይልን በጎረቤት አገር ሶማሊያ ማሰማራት፤ ቀጠናው መረጋጋት እንዳይኖረው ሊያደርግ ይችላል፣ የሰላም ማስከበር ጥረቱን ይጎዳል እንዲሁም ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ውጥረት ይፈጥራል” ብሏል።
“በአፍሪካ ቀንድ እንደምትገኝ ሉዓላዊት እና ዴሞክራሲያዊት አገር ልክ እንደ ሌሎች ጎረቤት አገራት የሕዝባችንን እና የቀጠናውን መረጋጋት እና ደኅንነት የሚያውክ የውጪ ኃይል መሰማራትን ሙሉ በሙሉ አንቀበልም” ይላል መግለጫው።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ “የግብጽን አደገኛ እንቅስቃሴ” ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ እንዲያወግዘው ጨምሮ ጠይቋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ብዙ ያወዛገበውን የባሕር በር ስምምነት የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙ በቀናት ልዩነት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከግብፁ አቻቸው አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ጋር በስልክ ከመነጋገራቸው በተጨማሪ ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ ወደ ካይሮ አቅንተዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ካይሮ ባቀኑ ወቅት ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ዝርዝሩ ይፋ ያልተደረገ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።
በስምምነቱ መሠረት ግብጽ የሶማሊያን የመከላከያ እና የደኅንነት አቅምን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተጨማሪ ድጋፎችን፣ ስልጠናዎችን እንደምታደርግ እና በሁለቱ አገራት መካከል የመረጃ ልውውጥ እንደሚኖር ተገልጿል።
በወቅቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ስምምነቱ “ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ሰላምን ለማጎልበት አስፈላጊ ነው” ካሉ በኋላ ግብፅ ለአገራቸው ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለምትሰጠው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ነበር።
ከወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈረም በኋላ የግብጽ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ኤል ሲሲ አገራቸው የሶማሊያን በግዛቷ ላይ ያላትን አንድነት እና ሉዓላዊነትን እንደምትደግፍ እንዲሁም በውስጥ ጉዳይዋ ላይ የሚኖርን ማንኛውንም ጣልቃ ገብነት እንደምትቃወም በድጋሚ አረጋግጠዋል ብለዋል።















