የዘረኝነት ተጽእኖ በተለያየ መልኩ በሰዎች ጤና ላይ የሚያስከትለው ከባድ ቀውስ

ሕክምና ውስጥ በዘር ላይ የተመሰረተ መድልዎ አለ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ላየል ሊቨርፑል ትባላለች።

የባዮሜዲካል ተመራማሪ ሆና ስትሠራ ቆይታለች። አሁን ላይም የሳይንስ ጋዜጠኛ በመሆን እያገለገለች ነው።

በሳይንስ እና በሕክምናው ዘርፍ ላይ ያለው የዘር መድልዎ የሰዎችን ጤና እንደሚጎዳ የሚያስረዳ አዲስ መጽሐፍም ጽፋለች።

መጽሐፏ ‘ሲስተማቲክ፡ ሃው ሬሲዝም ኢዝ ሜኪንግ አስ ኢል’ ይሰኛል። በተገለሉ ማኅበረሰቦች እና በነጮች መካከል ያለውን የጤና ልዩነት እና የሚስተካከሉባቸው መንገዶች ላይ ያተኩራል።

ላየል ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ ያነሳሳት ጉዳይ የራሷ የሕይወት ተሞክሮ እንደሆነ ትናገራለች።

ላየል ሊቨርፑል ፊቷ እና እጆቿ ላይ ትንንሽ የቆዳ ቀለም መቀየር ማስተዋል የጀመረችው ታዳጊ ሆና ኔዘርላንድስ በምትኖርበት ወቅት ነበር።

ሐኪም ቤት በምትሄድበት ጊዜም የሚታዘዝላት ፀረ ባክቴሪያ (አንቲባዮቲክ) እና ፀረ ፈንገስ መድኃኒቶች ነበር፤ ነገር ግን ምንም ውጤት አላመጣም። በዚህም ምክንያት ያጋጠማት ህመም ያልተለመደ እና ሊታከም የማይችል እንደሆነ ገመተች።

ይህ በኔዘርላንድ ሆስፒታል የተመላለሰችበት ህመም ምንነቱ የታወቀው በዩናይትድ ኪንግደም ነበር። በዩኬ አንድ ጥቁር የቆዳ ሐኪም ባገኘችበት ወቅት በአንድ ጊዜ ችግሯ 'ኤክሴማ' የተባለው የቆዳ ህመም መሆኑ የተነገራት።

በሽታዋ ከዚህ ቀደም ሳይታወቅላት የቆየውም አብዛኞቹ ነጮች የሆኑ ሌሎች ዶክተሮቿ በሽታው በቀላሉ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ላይ እንዴት እንደሚታይ ስለማያውቁ እና የተሳሳተ ምርመራ ስለሚያደርጉ እንደሆነ ጥቁሩ ሐኪሟ ሐሳቡን አካፍሏታል።

ላየል የዘር መድልዎ በጤና ላይ ስለሚያደርሰው ቀውስ እንደ እሷ የሳይንስ ፀሐፊ ከሆነው ዴቪድ ሮብሰን ጋር ቆይታ አድርጋለች።

መጽሐፉን ለመጻፍ ምን አነሳሳሽ?

በቅርቡ ነው እናት ሆንኩት። ዩኬ ውስጥ እንደ እኔ ያሉ ጥቁር ሴቶች በእርግዝና እና በወሊድ ጊዜ የመሞት ዕድላቸው ከነጭ ሴቶች በአራት እጥፍ ይበልጣል። በሌሎች በርካታ ቦታዎችም ተመሳሳይ አሀዛዊ መረጃዎች አሉ። እንደ ሳይንስ ጋዜጠኛ እና የሕክምና ዕውቀት እንዳለው ሰው ይህንን ለማየት ወሰንኩኝ።

ስለዚህ ጉዳይ ብዙ የማውቅ ይመስለኝ ነበር። ባገኘሁት ነገር ግን በጣም ደነገጥኩኝ። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በብዙ አገራት የተገለሉ ማኅበረሰቦች ከወሊድ በተጨማሪ እንደተላላፊ በሽታዎች፣ የልብ እና የደም ቧንቧ በሽታዎች፣ ካንሰር፣ የአእምሮ ጤና እና በመሳሰሉት እጅግ የከፋ የጤና ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ተረድቻለሁ። ዘረኝነትን እንደ የሕዝብ ጤና ቀውስ እገልጸዋለሁ። ይህም የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶቻችንን ፍትሃዊ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን ውጤታማ ያልሆነም ያደርገዋል። ጊዜ፣ ገንዘብ እና ሃብት ያባክናል።

የሳይንስ ጋዜጠኛዋ ላየል ሊቨርፑል

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, የሳይንስ ጋዜጠኛዋ ላየል ሊቨርፑል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሕክምና ተማሪዎች በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ሥነ ሕይወታዊ (ባዮሎጂካል) ልዩነቶች ስለመኖራቸው ፍጹም የተሳሳተ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ጥናቶች ተጠቅሰዋል። ከእነዚህ የተሳሳቱ አመለካከቶች መካከል አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀሺልን?

በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ የጥቁር ሰዎች ቆዳ ከነጭ ሰዎች የበለጠ ወፍራም ነው ወይም ነርቮቻቸው በቶሎ አይጎዱም፤ ስለዚህም ጥቁር ሰዎች በተለየ መንገድ ህመም ይሰማቸዋል የሚለውን ተመልክቻለው። በአሜሪካ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሕክምና ተማሪዎች እነዚህን አንዳንድ የተሳሳቱ ሃሳቦች ያምኑ ነበር።

ይህ አንድ ምሳሌ ብቻ ነው። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ሃሳቦች ወደ ሕክምና መመሪያ ተተርጉመዋል። ለምሳሌ የጥቁር ሰዎች ኩላሊት ከነጮች በተለየ ሁኔታ ይሠራል የሚለውን ሃሳብ መነሻ በማድረግ በበሽተኛው ማንነት ላይ ተመሥርቶ የኩላሊት ምርመራ ማድረግ የተለመደ ነበር።

ይህ ከአንዲት ትንሽ ጥናት የመጣ ይመስላል። ከዚያም በሌሎች ጥናቶች ይጠቀስና በመጨረሻም ወደ መመሪያዎች ውስጥ ይካተታል። ይህ አሉታዊ የጤና መዘዝ እንዳለው የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ።

ስለዚህ ጉዳይ በመጀመሪያ ለሳይንስ መጽሔቱ 'ኒው ሳይንቲስት' ዘገብኩኝ። የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና እና እንክብካቤ ተቋምን ካነጋገርኩ በኋላም የዘር አጠቃቀምን ለማስወገድ በሚል መመሪያቸውን አሻሽለዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃም ለውጦችን እያየን ነው።

ከሳንባ ምርመራ ጋር በተያያዘም ያለውን በዘር ላይ የተመሠረተ አካሄድ ማየት እንችላለን። ይህ የጥቁር ሕዝቦች ሳንባ ደካማ ነው የሚል ሀሳብ ካላቸው እና በባርነት መገዛታቸው ይጠቅማቸዋል ከሚለው ከሳሙኤል ካርትራይት ከተባለ የአሜሪካ ሐኪም እና ባሪያ አሳዳሪ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ በሆነ መልኩ በሕክምናው ውስጥም ተካቷል።

ስለዚህ ጉዳይ በ2021 ሪፖርት ሳደርግ፣ የሳንባ አቅምን ስንለካ ዘርን ማየት እንዳለብን የሚጠቁሙ ዓለም አቀፍ መመሪያዎች ነበሩ። ባለፈው ዓመት የመጽሐፉን የመጨረሻ ዕትም አርትኦት ስሠራ፣ የአሜሪካ ቶራሲክ ሶሳይቲ እና የአውሮፓ ሪስፓራቶሪ ሶሳይቲ የዘርን ጉዳይ ከመመሪያቸው እንዳስወገዱ አወቅኩ። ዘር ማኅበረሰባዊ መሠረት ያለው እንጂ በባዮሎጂ መሠረት እንደሌለው በግልጽ ተናግረዋል። ይህ ቀደም ብሎ ቢደረግ በጣም ጥሩ ነበር። ሆኖም መለወጡ እና ውይይቶቹ በመኖራቸው ደስተኛ ነኝ።

ዘር በአእምሮ ጤና አጠባበቅ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል?

በደንብ መታየት ያለባቸው ብዙ እኩል የማይታዩ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ጥቁሮች ለአእምሮ ሕክምና ሲባል ከፍላጎታቸው ውጭ የመታሰር ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ እናያለን። አሜሪካ ውስጥ የአእምሮ ጤና ችግር ያጋጠማቸው ጥቁር ወንዶች ከነጮች አንጻር በፖሊስ የመገደል ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ጥናቱ እንደሚያመለክተው ከሆነ ይህ ሊሆን የቻለው ጥቁር ሰዎች የበለጠ አስጊ ወይም አደገኛ ናቸው በሚል ግንዛቤ ነው።

ዘረኝነት በምርመራዎች ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ጭንቀት በተገለሉ ማኅበረሰቦች ዘንድ በቂ ምርመራም ሆነ ሕክምና ያልተደረገለት ሲሆን፣ የአስተሳሰብ መዛባት (ስኪዞፍሪንያ) ደግሞ አንዳንድ ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ ባሉ ጥቁር ሰዎች ላይ ከመጠን በላይ በመመርመር ይታወቃል።

ስለዚህ የሕክምና ባለሙያዎች ጥቁሮችን በሚመለከቱበት መንገድ እና በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አንዳንድ የተዛቡ ግንዛቤዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ችግር ነው።

በብዙ አገሮች የሚገኙ ጥቁሮችም የዘረኝነት ልምዳቸው እና በደኅንነታቸው ላይ የሚያስከትላቸው ተጽዕኖዎች በአእምሮ ሐኪሞች በቁም ነገር እንዳልተወሰዱ ይሰማቸዋል። ይህ ደግሞ ሰዎች ለችግር ሲጋለጡ እና ድጋፍ በሚፈልጉበት ጊዜ ስላጋጠሟቸው ችግሮች በመናገር ድጋፍ የሚያገኙበትን ፍላጎት ሊቀንሰው ይችላል።

ዩኬ ውስጥ ጥቁር ሴቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የመሞት ዕድላቸው ከነጮች አንጻር አራት አጥፍ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዩኬ ውስጥ ጥቁር ሴቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የመሞት ዕድላቸው ከነጮች አንጻር አራት አጥፍ ነው

የአእምሯችን ሁኔታ በአካላዊ ጤንነታችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በዘረኝነት እና እንደ ልብ እና አልዛይመር ባሉ በሽታዎች መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

የልብ በሽታ በዓለም ላይ ዋነኛው ገዳይ እና ትልቁ የሕዝብ ጤና ችግር ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ዘረኝነት እዚህም ላይ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ጥቁሮች የመስረቅ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው በሚሉት አመለካከቶች የተነሳ ሱቅ ውስጥ ገብተህ ክትትል ይደረግብኝ ይሆን? የሚሉ የዕለት ተዕለት ጭንቀቶች የልብ ምትን ከፍ እንዲል እና መጨናነቅን ይፈጥራሉ።

ዘረኝነትን በሕይወት ዘመን በሙሉ መጋፈጥ በነርቭ እና በልብ ሥርዓት ላይ ሥር የሰደደ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ለምሳሌ በአሜሪካ ያሉ ጥቁሮች በከፍተኛ የደም ግፊት የመያዛቸው ዕድል ትልቅ በመሆኑ፤ ለልብ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ሥር የሰደደ ጭንቀት እና የስሜት ቀውስ ከዕድሜ ጋር ለተያያዘ የግንዛቤ ማሽቆልቆል እና ከመርሳት ችግር ጋርም ሊገናኝ ይችላል።

ተስፋስ አለ?

መጽሐፉን በምጽፍበት ወቅት እነዚህ ጉዳዮች የሚያስጨንቋቸው እና ችግሮቹን ለመፍታት እየሠሩ ያሉ ብዙ ሰዎችን አግኝቻለሁ። ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም ለጥቁር እናቶች ጤና የሚሠራ 'ፋይቭ ኤክስ ሞር' የሚባል ድርጅት አለ።

43 በመቶ ጥቁሮች እና ከጥቁር እና ከነጭ የተገኙ ሴቶች በወሊድ እንክብካቤ ወቅት መድልዎ እንደደረሰባቸው የሚያሳይ ጥናት አከናውነዋል። እርጉዝ የሆኑ ጥቁር ሴቶች በጤና አጠባበቅ ሁኔታ ላይ ለእራሳቸው እንዴት መሟገት እንደሚችሉ ምክሮችን አቅርበዋል።

በዚህ ጉዳይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ እና ሁሉም ሰዎች የወሊድ አገልግሎት ሲያገኙ ምቾት እንዲሰማቸው ማድረግ ለሚፈልጉ የጤና አጠባበቅ ሠራተኞች ሥልጠናም ሰጥተዋል።

ብዙ ሳይንቲስቶች ከሕክምና ምርምራቸው ላይ አድልዎን ለማስወገድ ጠንክረው እየሠሩ ነው። ዶክተሮች በውይይታችን መጀመሪያ ላይ የተነጋገርናቸውን የዘር መድሎዎች እና ዘርን መሠረት ያደረጉ የሕክምና ዘዴዎችን መዋጋት ጀምረዋል። በሕክምና ውስጥ የበለጠ የተስፋፋ ሆኖ ማየት ብፈልግም በግለሰብ ደረጃ እየተመለከትነው መሆኑ አስደናቂ ነው።