አንጎልን ከጥቅም ውጪ ከሚያደርገው ገዳይ የአሜባ በሽታ የተረፈው ታዳጊ

አፍናን እና ወላጅ አባቱ ሲዲቂ

የፎቶው ባለመብት, MK Siddiqui

የምስሉ መግለጫ, አፍናን እና ወላጅ አባቱ ሲዲቂ

ሕንዳዊው ታዳጊ አንጎልን ከጥቅም ውጪ በማድረግ ከሚገድለው የአሜባ በሽታ አባቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባዩት መረጃ አማካይነት ተርፏል።

በዚህ በሽታ ከተያዙ ሰዎች መካከል እጅግ ጥቂቶቹ በሕይወት ቢተርፉም፣ የአብዛኛዎቹ ሰዎች ዕጣ ፈንታ ግን ሞት ነው።

አፍናን ጃስሚን የተባለው የ14 ዓመት ወጣት ሕይወቱ የተረፈችው ወላጅ አባቱ ስለበሽታው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተመለከቱት ነገር አማካይነት ነው።

አፍናን በዚህ አንጎልን ከጥቅም ወጪ በማድረግ ለሞት ለሚዳርገው የአሜባ በሽታ የተጋለጠው በአካባቢው ባለው አንድ የኩሬ ውሃ ውስጥ ለዋና በገባ ወቅት ነበር።

የታዳጊው ሐኪሞች ናኤግሌሪያ ፎሌሪ የተባለው አሜባ ወደ ታዳጊው ሰውነት የገባው ከተበከለ ውሃ ነው የሚል ግምት አላቸው።

በአሜባ በሚከሰተው ፕራይሜሪ አሚዮቢክ ሜኒንጂኦሴፍሊስ በተባለው በሽታ ከሚያዙ ሰዎች 97 በመቶ የሚሆኑት ሕይወታቸው ያልፋል።

እንደ የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ከሆነ ከአውሮፓውያኑ 1971 እስከ 2023 ባሉ ዓመታት በአሜሪካ፣ በሜክሲኮ፣ በአውስራሊያ እና በፓኪስታን በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጦ በሕይወት የተረፉ ሰዎች ቁጥር ስምንት ብቻ ነው።

ከእነዚህ ባሻገር በበሽታው የተያዙ በርካታ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።

በሕይወት የተረፉት እነዚህ ስምንት ሰዎች አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር የበሽታው ምልክት መታየበት በጀመረ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ አምስት ቀናት ባሉት ጊዜያት ወደ ጤና ተቋም ማምራታቸው ነበር።

ሲዲሲ ለእነዚህ ሰዎች በሕይወት መትረፍ የበሽታው ምልክቶች ተለይተው በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም መሄዳቸው ቁልፍ ጉዳይ ነው ይላሉ።

በበሽታው የተጠቃ ሰው አብዛኛውን ጊዜ ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል ራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ ማቅለሽለሽ፣ ሚዛን መሳት፣ መንዘፍዘፍ እና ቅዠት ይጠቀሳሉ።

አፍናን ለውሃ ዋና በመደሩ ወዳለው ኩሬ ካመራ ከአምስት ቀናት በኋላ ነበር የበሽታውን ምልክቶች ማሳየት ጀመረው።

ባልተለመደ ሁኔታ ሰውነቱ መንዘፍዘፍ እና ከባድ የራስ ምታት እንዳለው ለወላጆቹ ይናገር ነበር።

ወላጆቹም ልጃቸውን ሐኪም ጋር ወሰዱት። ነገር ግን ሊሻለው አልቻለም።

እንደ መታደል ሆኖ የአፍናን አባት ሲዲቂ ከዚህ ቀደም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተመለከቱትን ነገር ልጃቸው ላይ ከሚያዩት መልክት ጋር አገናኙት።

በግብርና ሥር የሚተዳደሩት የ46 ዓመቱ አባት፣ ከጥቂት ቀናት በፊት በአካባቢያቸው ኒፓህ በተባለ ቫይረስ ስለሞተ ልጅ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አንብበው ነበር።

“በኢንፌክሽን ምክንያት የሰውነት መንዘፍዘፍ (ሲዠር) እንደሚከሰት አነበብኩ። ልጄ ይህን ምልክት ሲያሳይ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ወሰድኩት” ይላሉ።

ነገር ግን ይህ የሰውነት መንዘፍዘፍ ሳይቆም ሲቀር ወደ ሌላ ሆስፒታል ይዘውት ሄዱ።

አሜባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አፍናንን የመረመሩት ዶ/ር አብዱል ራኡፍ ነበሩ። ዶ/ር አብዱል “የበሽታው ምንነት በ24 ሰዓታት ውስጥ ተለይቷል” ካሉ በኋላ የታዳጊው አባት ልጁ በኩሬ ውስጥ ስለመዋኘቱ መናገሩ በጣም ጠቃሚ መረጃ ነበር ብለዋል።

ይህ አሜባ ወደ ሰው ልጅ ሰውነት የሚገባው በአፍንጫ በኩል ነው። ወደ አፍንጫ ከገባ በኋላ ወደ አንጎል ዘልቆ ይሄዳል።

“ይህ ጥገኛ ተህዋስ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ የተለያዩ ኬሚካሎችን በማመንጨት አንጎልን ከጥቅም ውጪ ያደርጋል” በማለት ዶ/ር ራኡፍ ይናገራሉ።

ለበሽታው ተጋልጠው ተህዋሱ ወደ ሰውነታቸው ከገባ ሰዎች ሁሉም ሊባል በሚያስችል ደረጃ አንጎላቸው ውስጥ በሚፈጠር ፈሳሽ ነገር ሕይወታቸው ያልፋል።

ሐኪሙ እንደሚሉት ይህ አሜባ አብዛኛውን ጊዜ የሚገኘው ጨዋማ ባልሆነ እና ሙቀት ባለው ውሃ ውስጥ ነው።

“ሰዎች ዘለው ውሃ ውስጥ ከመግባት መቆጠብ አለባቸው። አሜባ ሰውነት ውስጥ ሊገባ ይችላል። ውሃው የተበከለ ከሆነ አሜባው በቀላሉ በአፍንጫ በኩል ወደ ሰውነት ይገባል” ይላሉ።

አፍናን ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ህብለሰረሰሩ (ነርቭ) ላይ አንቲማይክሮቢአል መድኃኒት መርፌ መወጋትን የሚጨመር ሕክምና ከተደረገለት በኋላ በሕይወት ተርፏል።

“በመጀመሪያው ቀን ታዳጊው እራሱን ስቶ ነበር። ከሦስት ቀናት ሕክምና በኋላ ለውጣት ማሳየት ጀመረ” ይላሉ ሐኪሙ።

ከአንድ ሳምንት በኋላ በተደረገለት ምርመራ በታዳጊው ሰውነት ውስጥ አሜባው እንደሌለ ማረጋገጥ ተችሏል።

አፍናን እና ዶ/ር ራኡፍ

የፎቶው ባለመብት, Baby Memorial hospital

የምስሉ መግለጫ, አፍናን እና ዶ/ር ራኡፍ

በመዋኛ ገንዳዎች ክሎሪን ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው የሚሉት ዶ/ር ራኡፍ፤ ቁጥጥር በሚደረግባቸው ገንዳዎች ውስጥ እንኳ ሰዎች ሲዋኙ ምንጊዜም ከአንገታቸው በላይ ያለውን የሰውነት ክፍላቸውን ከውሃ በላይ ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ።

ምንም እንኳ አፍናን ሕክምና ተደርጎለት ተሽሎት ከሆስፒታል ቢወጣም፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሕንድ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ብሏል።

አፍናን በሚኖርበት ኬራላ ግዛት እንኳ በዚህ ዓመት 6 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል። ሦስቱ ሕይወታቸው አልፏል።

“በሆስፒታላችን ሁለት ሰዎች ከሞቱ በኋላ ሕብረተሰቡ ስለ በሽታው መረጃው እንዲኖረው መንግሥት የቅስቀሳ ሥራ እንዲያከናውን አስደርገን ነበር” ይላሉ ዶ/ር ራኡፍ።

ሕብረተሰቡ ስለበሸታው መረጃው እንዲኖረው በተደረገ በቅስቀሳ ነው የአፍናን አባት ሲዲቂ መረጃው ደርሷቸው ሳይረፍድ ልጃቸውን ወደ ጤና ተቋም ያመጡት።

በዚህ አደገኛ በሽታ ታይዞ ሕይወቱ የተረፈው አፍናን፤ የሕክምና ትምህርት ተምሮ በነርሲንግ ዲግሪ እንዲኖረው እንደሚፈልግ ገልጿል።

“ነርሶች ታካሚዎችን ለመርዳት ብዙ እንደሚደክሙ ለዶክተሩ ተናግሯል” ሲሉ ሲዲቂ ይናገራሉ።